አንድ አውቶብስ ሙሉ መንገደኞች የተሰወሩበት ሰሞነኛው እገታ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 16 2017
ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከገርባ ጉራቻ ከተማ ቅርብ ቦታ ላይ በምትገኘው አደገኛ ስፍራ ተብላ በምትገለጸው አሊዶሮ ተፈጸመ በሚባለው በዚህ የአንድ አውቶብስ ሙሉ ተሳፋሪዎች እገታ እስካሁን የሚታወቀውም ጥቂት ነው። የዞኑ መንግሥት መዋቅርም ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ይላል።
ማሩ ሽፌ ይባላል። የዕቃ ጫኝ ከባድ ተሽከርካሪ ሾፌር ነው። ከአዲስ አበባ በጎጃም በማቋረጥ የንግድ ሸቀጦችን ጭኖ ወደ ጎንደር ወሮታ እና አካባቢው መመላለስ የሰርክ ተግባሩ ነው። እንደወትሮው ሁሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስጋት በነገሰበት በዚሁ የአዲስ አበባ ጎጃም መንገድ ላይ ሸቀጦቹን ጭኖ እሑድ መጋቢት 07 ቀን 2017 ዓ.ም. ማልዶ በመነሳት መንገዱን ይጀምራል። ማሩ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገረው በዕለቱ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ፊቼ እና ገርባ ጉራቻን እንዳለፉ ወትሮም ለአሽከርካሪዎች ፈታኝ ስፍራ ተደርጋ በምትታየው የደገም ወረዳዋ አሊዶሮ ላይ አንድ ነገር ይመለከታል።
የእገታው መፈጸም
«እሑድ ቀን 2፡30 ሰአት ነው። መኪኖች ተከታትለው ሲወጡ እኔ አራተኛው ነበርኩ። ሸቀጥ ጭኜ እየተጓዝኩ ነበር። ግዮን ባስ ኤ-30273 ኢት የሚል ታርጋ ያለው ሰዎችን የጫኔ ባስ ፊትለፊት በጥይት የተመታው አባይ ባስ ጥሶ ሲያልፍ ግዮን ባስን ጎማውን መትተው አስቆሙት። ያንን ስንመለከት እኛ ወደኋላ ነው ለመዞር የወሰነው። ከዚያም ፊቼ አካባቢ ዞረን ቆምን። በዓይኔ የተመለከትኩት ግዮን ባስ ውስጥ የነበሩን ተሳፋሪዎች በሙሉ ፀጉራቸውን ያሳደጉ ታጣቂዎች ሲያስወርዱዋቸው ነበር። በሰዓቱ መኪናውን ጥየው እንዳልሄድ የብዙ ሚሊየን ብር ዕቃ ስለጫንኩ መኪናውን እንዳያቃጥሉት ፈርቼ ወደኋላ ለመዞር ወሰንኩ» ይላል ማሩ።
መንገደኞቹ በሙሉ ወደ አማራ ክልል ደብረማርቆስ ከተማ የሚጓዙ ነበሩ ያሉት የዐይን እማኝ ታጣቂዎች መንገደኞቹ ላይ እገታ የፈጸሙት አራት ተሸከርካሪዎች ተከታትለው በሚሄዱበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል። በወቅቱ እገታውን የፈጸሙ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ቢያደርጉም ታጋቾችን ግን ማስጣል እንዳልተቻለ ነው የዓይን እማኙ የተናገሩት።
«ተሳፋሪዎቹን አውርደው እየገፉ ሲወስዷቸው በቅርብ ርቀት እየተመለከትናቸው ነበር» ያሉን አስተያየት ሰጪው የዓይን እማኝ፤ ተሽከርካሪው ከተመታ በኋላ የፀጥታ ሃይሎች አካባቢው ላይ ዘግይተው ቢደርሱም ታጋቾችን ማስጣል ግን እንዳልተቻላቸው አስረድተዋል። የፊት ጎማውን የተመታው መንገደኞች የታገቱበትን ተሸከርካሪ ግን በዚያው ዕለት እሑድ ማታውን የፀጥታ ሃይሎች ባሉበት ማንሳት መቻሉን ገልጸዋል። ከተሽከርካሪው ውስጥ ሾፈርና ረዳቱን ጨምሮ 58 ሰዎች መወሰዳቸውን እንደሚያውቁ የገለጹት አስተያየት ሰጪው አሽከርካሪ «ታግተው ከተወሰዱት መንገደኞቹ መካከል አንዲት የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ ደውላ 1.5 ሚሊየን ብር መጠየቋና እርዳታ እየተሰባሰበላት» መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አንድ የፈለገ ጊዮን አውቶብስ ሠራተኛ ማንነታቸውን ሳይገልጹ በድርጅቱ ንብረት አውቶብስ ላይ የድርጊቱን መፈጸም ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል።
መንገደኞቹን ያሰለቸው የተደጋገመው እገታ
በዕለቱ ከ50 በላይ መንገደኞች ከታገቱበት አውቶብስ በተጨማሪ በርካታ ተሽከርካሪዎች የታጣቂዎች ጥቃት ኢላማ ነበሩ ያሉት የዐይን እማኞች፤ በዚህ አካባቢ በታጣቂዎች እየታገቱ ገንዘብ መጠየቁ የቆየና መንገደኞችን ስጋት ላይ የጣለ፤ አሽከርካሪዎችን ደግሞ ያሰለቸ ጉዳይ እንደነበርም አስታውሰዋል። አሊዶሮ ተብሎ የሚታወቅ ይህ ስፍራ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ከደባርቅ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተነስተው ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ በርካታ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ100 በላይ ሰዎች በታጣቂዎች የታገቱበት ቦታ ነው።
አሁን ተፈጸመ ስለተባለውና የታጋቾች እጣፈንታ በውል ባልታወቀበት ጉዳይ ላይ ዶይቼ ቬለ አስተያየታቸውን እዲሰጡ የጠየቃቸው ለሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፈለው አደሬ «መረጃውን በማጣራት ላይ ነን» የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
ከእገታው ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ስሙ የሚጠቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎቹ በአካባቢው በስፋት እንደሚንቀሳቀሱ ባያስተባብልም በዚህ አካባቢ ተደጋግሞ ስለሚፈጸመው እገታ ማስተባባያ ሲሰጥ ቆይቷል። ኦነሰ በአሁኑ ከአዲስ አበባ ተነስተው ወደ ደብረማርቆስ በመጓዝ ላይ ሳሉ ደገም ወረዳ ውስጥ ታገቱ ስለተባሉ መንገደኞች ግን በመመርመር ላይ መሆኑን ባለፈው ሳምንት በይፋዊ ማኅበራዊ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ አስታውቋል። የሆነ ሆኖ እስካሁን የተወሰዱበት ስፍራ ያልታወቀው መንገደኞቹ፤ በአካባቢው የተደጋገመው የጸጥታ ችግሩ ሰለባ ስለመሆናቸው ነው የሚነገረው።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ፀሐይ ጫኔ