1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አደራን ተቀብሎ አደራውን የሚያደርሰው ወጣት

ዓርብ፣ ኅዳር 2 2015

ማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ከተለያዩ ሰዎች የተላከለትን ገንዘብ እና አልባሳት በአደራ ተቀብሎ ጎዳና ላይ ወይም በመኖሪያ ቤታቸው ለተቸገሩ አዛውንቶችን ፣ ጎልማሶችን ፣ ወጣቶች አደራውን ሚያደርሰው በምላሹ ደግሞ ሰጭዎቹን የሚያስመርቀው ወጣት «ባለአደራው» ማን ነው?

Äthiopien Baladeraw Logo
ምስል Baladeraw

ባለአደራው ወጣት

This browser does not support the audio element.

የ26 አመት ወጣት ነው። በመዲናችን አዲስ አበባ  ቤተሰቦቹ በተሰማሩበት የንግድ ሥራ ዘርፍ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። በጎዳና ላይ ያሉ አዛውንቶችን ፣ ጎልማሶችን ፣ ወጣቶችን በመርዳት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በተለይም በቲክቶክ እና በፌስ ቡክ ይታወቃል። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚታወቀው ባላደራው በሚል ስያሜ ነው። ታዲያ እርሱም ይህን ስያሜ ያስቀድማል ምክንያቱም  «ብዙዎች የሚያውቁኝ በዚ ስሜ ነው» ይላል።

 
«መጀመሪያ ለሰዎች መርዳት ስጀምር ብር አልነበረም ምሰጣቸው ። ግዜ እና ፍቅር ነበር የምሰጣቸው።  ለሰው ልጅ መጀመሪያ ከገንዘብም ከምንም በላይ ግዜ እና ፍቅር ነው የሚያስፈልገው። እናም ወደ ስራም ስሄድ ከስራም ስመለስ ጎዳና ላይ ቁጭ ብለው የሚለምኑ ከኔ የእድሜ ክልል በላይ ያሉ፣ ታናናሾቼን እንዲሁም እኩዮቼን እመለከት ነበር እና ለነሱ ፍቅር መስጠት አለብኝ ብዬ አሰብኩ»። ከዛ  ምሳ ሰአቱን ከነሱ ጋር ማሳለፍ የጀመረው ባለአደራው። ቀስ በቀስ ምሳቃውን ይዞ ከነሱ ጋር አብሮ ምሳውን እየበላው ግዜ ማሳለፍ ጀመረ ።«የሚያወራቸው ሰው ይፈልጋሉ ከነሱ ጋር ሰአት ሳሳልፍ በጣም ደስተኛ ናቸው»።

ታዲያ ከሱ ቀደም ብሎ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ በቲክ ቶክ ላይ መልክተኛው በሚል ስያሜ ባህር ዳር ከተማ ጎደና ላይ ላሉ እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች  እርዳታ የሚያደርስን መልክተኛው የሚል መጠሪያ ያለውን ልጅ ተመልክቶ  እኔም ለምን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴን  ለጥሩ አልጠቀም በማለት እራሱን ባላደራው የሚል ስያሜ ሰቶ ሰዎችን መርዳት ጀመረ። ባለአደራው ስለ መልክተኛው ሲናገር « በጣም ነው የምወደው፣ በጣም ነው የማከብረው እሱ አይቼ ነው እኔ ወደዚ ስራ የገባውት እሱ ለኔ እንደ ሮል ሞዴሌ ወይም ምሳሌ ነው»ይላል።

መጀመሪያ ላይ  ከራሱ ኪስ እያወጣ ሌሎችን መርዳት ጀመረ። ቀስ እያለም በቲክቶክ እና በፌስ ቡክ የሚለቃቸው ቪዲዩዎችን የተመለከቱ ለጋሾች  ወደሱ መምጣት ጀመሩ። «አድርስልኝ ብለው የላኩልኝ እምነት እንዲኖራቸው ለሰዎች ስሰጥ በቪዲዩ እየቀረፅኩ ነው ምክንያቱም የነሱ ማስረጃ ወይንም ማረጋገጫ ቪዲዩ ብቻ ነው። ስለዚ አድርስ ብለው ለሰጡኝ ሰዎች ማድረሴን እንዲሁም ምርቃታቸውንም እንዲያዩ ነው»ይላል ወጣቱ። ገንዘብ አድርስ ብለው የሰጡትን ሰዎች ስምና የገንዘብ መጠን በቪዲዩ ላይ ያስቀምጣል። ታዲያ ይህንን የሚመለከቱ ሰዎች እምነት ከቀን ወደቀን ከፍ እያለ መጣ።


ከቅርብ ግዜ ወዲህ  የኑሮ ውድነቱን መቋቋም አቅቱዋቸው በእድሜ ጠና ያሉ ሰዎችን በመዲናችን አዲስ አበባ በየጎዳናው ምፅዋት ሲጠይቁ ማየት የተለመደ ሆኗል። በተቃራኒው ደሞ የተቸገረን በመርዳት የመንፈስ ርካታን የሚያገኙ ሰዎችም ተበራክተዋል ። አንድ ሰው ድጋፍ ሲያገኝ የሚያገኘው ደስታ የተለየ እንደሚሆነው ሁሉ ሚሰጠውም ሰው  የሚያገኘው ደስታ ከቃላት በላይ   ነው። ባለአደራው የሰዎችን ደስታ ሳይ የተለየ ነገር ነው ሚፈጥርብኝ «ብዙ ግዜ ይህንን ካደረኩ በኋላ ማታ ማታ ልተኛ ቪዲዩዋቸውን ደጋግሜ  አየዋለው እና ያ ነገር በጣም ያስደስተኛል»።ሲል የሰዎችን ደስታ ማየት ደጋግሜ እንድሰራ ብርታት ሰቶኛል ይላል። 


ለበርካታ ሰዎች አደራ ያደረሰው ባላአደራው በሚሰራው ቪዲዩ ላይ ድምፁን እንጂ መልኩን አያሳይም ለምን ተብሎ ሲጠየቅ ከኔ በላይ የምሰራው ስራ ነው እንዲታወቅ የምፈልገው ይላል ቀጠል አድርጎም  «እኔ ፊቴን ባሳይ መልኬን ባሳይ ሚዲያ ላይ ብወጣ በብዙ ነገሮች ተጠቃሚ ልሆን እችላለሁ። ግን እኔ በሰዎች  መታወቅን አልፈልግም። በእግዚአብሔር ዘንድ በማደርገው ነገር ውዳሴዬ ከንቱ እንዲሆን አልፈልግም። ዋናው ነገር እኔ ሽልማቴን ማግኘት የምፈልገው ከሰዎች ሳይሆን ከእግዚአብሔር ስለሆነ ነው። በነዚ ምስኪኖች ላይ እኔ በፍፁም ታዋቂ መሆንን አልፈልግም»ይላል ታዲያ የሱ ፊት ስለማይታይ አንዳንዶች ለማጭበርበር እድል እንደከፈተላቸው የተናገረው ባለአደራው እስካሁን ግን የተሳካለት የለም ይላል  «ቢሆንም ባለአደራው ነኝ የሚል ሰው ሲያጋጥማችሁ ድምፁን በደንብ ስሙት አለበለዚያ ተቀርፀህ ላክልን በሉት ይላል» አደራ የሚሰጡትም በድምፁ እንደሚያውቁትም ይናገራል። 


ማኅሌት  ፋሲል 
ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW