1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አደገኛው የባሕር ላይ ስደትና እልቂት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 10 2015

ባለፉት ስድስት ወራት 12.000 ስደተኞች እና ፍልሰተኞች የአውሮጳ ኅብረት ሃገራት ውስጥ መግባት ተሳክቶላቸዋል ። እነዚህ ሲበዛ እድለኞቹ ናቸው ። በርካቶች በጥልቁ ባሕር ውስጥ የዓሦች ራት ሆነው ቀርተዋል ። ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ሰላሳ ሺህ ግድም የባሕር ላይ ስደተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል ።

Griechenland Schiffsunglück
ምስል HELLENIC COAST GUARD/REUTERS

የጀልባ መስጠም እልቂቱ ብርቱ ሐዘን አስከትሏል

This browser does not support the audio element.

ባለፉት ስድስት ወራት 12.000 ስደተኞች እና ፍልሰተኞች የአውሮጳ ኅብረት ሃገራት ውስጥ መግባት ተሳክቶላቸዋል ። እነዚህ ሲበዛ እድለኞቹ ናቸው ። በርካቶች በጥልቁ ባሕር ውስጥ የዓሦች ራት ሆነው ቀርተዋል ። ባለፉት ሰባት ዓመታት ብቻ ሰላሳ ሺህ ግድም የባሕር ላይ ስደተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል ። እጅግ አደገኛ በሆነው የሜዲትራንያን ባሕር በመናኛ ጀልባዎች የሚያደርጓቸው ጉዞዎች ሁሌም በሞትና በሕይወት ቀጭን ገመድ ላይ የተንጠለጠለ ነው ። ከሰሞኑ ግሪክ የባሕር ጠረፍ አውራቢያ የደረሰው የስደተኞች እልቂት የብዙዎችን ልብ ሰብሯል ። ስደተኞቹ ከሊቢያ ተነስተው ወደ ጣልያን የሚቀዝፉ ነበር ተብሏል ።

750 ስደተኞችን በተጨናነቀ መልኩ አሳፍራ ትቀዝፍ የነበረች አንዲት ዓሳ ማጥመጃ መናኛ ጀልባ ረቡዕ፤ ሰኔ 7 ቀን፣ 2015 ዓ.ም በመስጠሟ ቢያንስ 78 ሰዎች አልቀዋል ። ሌሎቹ የደረሱበት ዐይታወቅም ። ከስደተኞቹ መካከል 100 ግድም ሕጻናት ነበሩበት ተብሏል ። በሕይወት ከተረፉት 140 ስደተኞች መካከል 30ዎቹ ለሕክምና ወደ ሐኪም ቤት ወዲያው ነበር የወሰዱት ። ብዙዎቹም ባዩት አሰቃቂ አደጋ ከአካላዊ ይልቅ የመንፈስ ሥብራት የደረሰባቸው ናቸው ተብሏል ። ከመካከላቸው አንደኛው ትንሽ ልጅ ስለነበረበት እጅግ አስቸጋሪ ምስቅልቅል ሁኔታ የሔሌኒክ የቀይ መስቀል ተቋም አስታማሚ ኤካተሪን ጻታ እንዲህ መለስ ብለው ይቃኛሉ ።

በሕይወት ከተረፉት 140 ስደተኞች መካከል በከፊልምስል STELIOS MISINAS/REUTERS

«አንድ ልጅ በእንባ ተውጦ፦ እናቴን እፈልጋለሁ፤ እናቴን አለኝ ። በእርግጥ አንድ ብርቱ የስነልቦና ሥብራት የገጠመው ትንሽ ልጅ እናቴን ነው የምፈልገው ሲል መስማቱ ለእርሱም ሆነ ለእኛ ጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ነበር ። »

ዙሪያዋ ዝገት የሚታይበት ጀልባ የሰመጠችዉ ደቡብ ምዕራብ ግሪክ ግዛት አጠገብ ከወደብ ከተማዋ ፒሎስ ደቡባዊ አቅጣጫ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነበር ። ያን ሁሉ ስደተኞች ያለመፈናፈኛ ስፍራ አጭቃ የነበረችው ጀልባ ወርድ ርዝመቷ ከ20 በ30 ሜትር የማይበልጥም ነበር ።

ጀልባይቱ የሰመጠችዉ ደቡብ ምዕራብ ግሪክ ግዛት አጠገብ ከወደብ ከተማዋ ኪሮል በስተደቡብ ሲል 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው ። የግሪክ ባለሥልጣናት፦ የ104 ሰዎችን ሕይወት መደጋቸውን ዐሳውቀዋል ። ሆኖም ፔሎፖኔዜ የባሕር ሠርጥ አጠገብ ከባሕሩ 50 ሜትር ጠልቃ ከሰጠመችው ጀልባ በሕይወት የተረፉ ስደተኞችን የማግኘቱ ተስፋ መመናመኑን ሐሙስ ዕለት ባለሥልጣናት ተናግረዋል ።

ስደተኞችን የሚረዳ አንድ ድርጅት በአደጋው ዕለት እንዳስታወቀዉ፦ ጀልባይቱ 750 ስደተኞችን ማሳፈሯን የሚጠቁም የርዳታ ጥሪ ደርሶት ነበር። በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) የአዋቂዎች ጥበቃ ባልደረባ ኤርሲማ ሮውሙናም ይህንኑ አረጋግጠዋል ።

«በተጨናነቀ መልኩ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ለበርካታ ቀናት መጓዛቸውን ተረድተናል ። ፎቶዎቹን ተመልክተናል ። የሆነ ቦታ ላይ እንደውም የጀልባቸው ሞተር ችግር እንደደረሰበት በተጨናነቀ መልኩ የጥሪ መልእክት አስተላልፈዋል ። እነዚህ ከሰዎቹ የሰማናቸው ሁኔታዎች ናቸው።  በአብዛኛው ወንዶች ወደ 750 ግድም ሰዎች ጀልባዋ ላይ ታጭቀው ነበር ። ሆኖም ቁጥራቸው አነስ ያለ የተወሰኑ ሴቶች እና ሕፃናትም እንደነበሩ ሰምተናል ። »

በጀልባ መስጠም አደጋው ቢያንስ 78 ሰዎች አልቀዋል፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ አልተገኙምምስል STELIOS MISINAS/REUTERS

ከሞት የተረፉ ስደተኞች ከካላማታ ወደብ ወደ ማላካሳ የስደተኞች እና ፍልሰተኞች ማረፊያ በአውቶቡሶች ተጭነው መወሰዳቸውን ኤርሲማ ሮውሙና አክለው ተናግረዋል ። ካላማሳ ከተማ ከአቴንስ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ። በዚህች ከተማ ከ7 ዓመት በፊት ስደተኞች እና ፍልሰተኞች ማረፊያ የተሰናዳው በዋናነት ከቱርክ የሚመጡትን ለመቀበያ ነበር ።  140ዎቹ ከመስጠም የተረፉ ስደተኞች ግሪክ ዋና ከተማ አቴንስ ተመዝግበው የስደተኛ ማመልከቻ ማስገባት እንደሚችሉ ኤርሲማ ሮውሙና ብለዋል ።

የሚያሳዝነው ግን በተደጋጋሚ በባሕር ላይ ጉዞ የሕይወት አድን ጥሪ የሚያስተላልፉ ስደተኞችን በጊዜ የሚታደጋቸው መጥፋቱ ነው ። የብዙዎች ልብ የሚነካው ምናልባትም እንዲህ ባለ ከፍተኛ እልቂት ወቅት ይመስላል ። ከሦስት ሳምንት በፊት እንኳ አንዲት ጀልባ ሚኮኖስ ደሴት አቅራቢያ ሰጥማ ዘጠኝ ስደተኞች መሞታቸው ብዙም የመገናኛ ትኩረት ሳያገኝ ቀርቷል ።  በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሕይወት ሳይቀጠፍበት አልቀረም የተባለው የሰሞኑ የጀልባ አደጋ የዓለም መሪዎችን ትኩረትም ስቧል ። የጀርመን መራኄ መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የባሕር ላይ ስደተኞች ጉዳይ ትኩረት ያሻዋል ብለዋል ።

«ሜድትራኒያን ባሕር ላይ ስለደረሰው አደጋ እና ሰጥመው ስለሞቱ በርካታ ሰዎች ሰምተናል ።  እጅግ የሚያሳዝን እና ሰዎች ይህን አደገኛ የስደት መንገድ እንዳይመርጡ ለማረጋገጥ መደረግ ያለበትን ሁሉ እንድናደርግ፤ ብሎም አውሮጳ ውስጥ የፍልሰተኞች ሁኔታን በተመለከተ እርስ በእርስ የምንደጋገፍበት የጋራ ስርዓት መጎልበቱን እንድናረጋግጥ ለሁላችንም በድጋሚ ጥሪ ያስተላለፈ ነው ። »

የግሪክ ሔለኒክ የባሕር ጠረፍ ጠባቂ መርከብምስል Stelios Misinas/REUTERS

በሰጠመችው ጀልባ የነበሩ አብዛኞቹ ስደተኞ ምንጫቸው ከሶሪያ፣ ከግብጽ እና ከፓኪስታን ሳይሆን አይቀርም ተብሏል ። ከሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ጋር በተገናኘ የጀልባዪቱ መሪ ቀዛፊን ጨምሮ ዘጠኝ ግብጻውያን ዐርብ ዕለት በግሪክ የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለዋል ። ግሪክ ከረቡዕ ምሽት እስከ ቅዳሜ ምሽት ሦስት ሰአት ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሐዘን ቀናት አውጃለች ። አደገኛ ስደት፣ ባሕር ላይ እልቂት፣ የሐዘን ቀናት፣ የአንድ ሰሞን የፖሊሲ ጋጋታ ግን እየተመላለስ መደጋገሙ አልቀረም ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW