1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያዉያን ምን ይዞላቸው መጣ? ተስፋ ወይስ የቀጠለ ስጋት ?

ሰኞ፣ መስከረም 6 2017

ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም ሰባት ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ ወደ ኋላ የምትቀርበት የዘመን ቀመር 2017 ላይ ደርሶ እነሆ 2016 አሮጌ ሆኖ ለአዲሱ ዓመት ተሸጋገረች ። በእርስ በርስ ግጭት ጦርነት ውስጥ ያለችው ሀገር ከአንዱ የግጭት ጦርነት ምዕራፍ ወደ ሌላው እየተሸጋገረች ዓመታቱም ሂያጁ ለመጪው እየለቀቁ ቀጥለዋል።

Young Flower Adey Abeba Blumen Äthiopien
ምስል Yohannes Geberegziabeher

አዲሱ የኢትዮጵያዉያን ዓመት በተስፋ እና ስጋት መካከል

This browser does not support the audio element.

የጊዜ ዑደቱ በሰከንድ መቁጠሪያ ጀምሮ ዓመት ሲደርስ ፤ ቀናት ለሳምንታት ፤ ሳምንታት ለወራት ፤ ወራትም በወቅቶች ተከፋፍለው ወደ ቀጣዩ ዓመት ሲያሻግሩ ለሰው ልጆች የዕድሜ መቁጠሪያ ፤ ዓምናን ለከርሞ ማሻገሪያ ይሆናቸው ዘንድ የተፈጥሮ ህግጋት ድንጋጌ አካል ናቸው ። ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም ሰባት ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ ወደ ኋላ የምትቀርበት የዘመን ቀመር 2017 ላይ ደርሶ እነሆ 2016 አሮጌ ሆኖ ለአዲሱ ዓመት ተሸጋገረች ። በእርስ በርስ ግጭት ጦርነት ውስጥ ያለችው ሀገር ከአንዱ የግጭት ጦርነት ምዕራፍ ወደ ሌላው እየተሸጋገረች ዓመታቱም ሂያጁ ለመጪው እየለቀቁ ቀጥለዋል።  ኢትዮጵያውያን አዲሱን የ2017 ዓመት ሲቀበሉ በምን ስሜት ውስጥ ሆነው ይሆን ? አዲሱ ዓመት ምን ይዞላቸው መጥቶ ይሆን ? አዲስ ተስፋ ወይስ ከካች ዓምና ዓምና  የተሸጋገረው የደህንነት እና የኑሮ ውድነት  ስጋት ? 

አቶ አማረ አሰፋ በደቡብ ወሎ ዞን አልቡኮ ወረዳ  አርሶ አደር ናቸው ። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲሱን ዓመት በአዲስ ስሜት ወግ ተቀብለዋል። እርሳቸው የሚኖሩበት የአማራ ክልልም ሆነ  ወረዳ  በብዙ ግጭት ጦርነት ውስጥ   ማለፉን የሚናገሩት አርሶ አደሩ  እንደ እድል ሆኖ እርሳቸው የሚኖሩበት አካባቢ በአንጻራዊነት የተረጋጋ ነበር  ። በአዲሱ የ2017 እርሳቸው ተስፋ የሚደርጉበት ዋና ጉዳያቸው በክልላቸውም ሆነ በመላ ሀገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ማየት ነው። 

«አዲሱ ዓመት ያው እንግዲህ ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ እግዚአብሄር በኪነ ጥበቡ አድርሶናል ። ተስፋ ነው እንግዲህ ያው ተስፋችን ሰላም ይመጣል ብለን ነው የምንጠብቀው ።  እና መንግስትም በሁሉ በኩል ጥረት እያደረገ ያለበት ሁኔታ እንዳለ እና አንዳንድ ልማቶችን በተለያዩ ከተሞች ስናይ ጥሩ ሰላም ይመጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። »
በአዲሱ ዓመት እንደ ሰው ተስፋ ከማድረግ ለፈጣሪ መስጠቱን የመረጡት ደግሞ የደሴ ከተማ ነዋሪ እና ስማቸውን የማንጠቅስ መምህርት ናቸው ። 

«ያው እንደምታውቁትም እንዳለንበትም የምናየው ተስፋ የለም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ተስፋ ስለማንቆርጥ ያሉትን ያለመግባባቶች በመልካም ፤ የኑሮ ውድነትን በተሻለ መልኩ ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያለው የመንግስት ሰራተኛ ሸምቶ የሚበላበት እንዲሆን ፤ አሁን እንግዲህ የዝናብ ሁኔታ የተሻለ ነው። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ደግሞ ሁለቱም የኛ ስለሆኑ በሰላም ነገሮች የሚፈቱበት እና እያንዳንዱ የክልልም ይሁን የተለያዩ ጥያቄዎች የሚፈቱበት እንዲሆን ነው የኔ ተስፋ እና ምኞት  »

አቶ አማረ አሰፋ በደቡብ ወሎ ዞን አልቡኮ ወረዳ  አርሶ አደር ናቸው ። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲሱን ዓመት በአዲስ ስሜት ወግ ተቀብለዋል። እርሳቸው የሚኖሩበት የአማራ ክልልም ሆነ  ወረዳ  በብዙ ግጭት ጦርነት ውስጥ   ማለፉን ምስል Solomon Muchie /DW

ግጭት የወለደው ቀውስ በአማራ ክልል
በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረው እና ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ ሰዎችን ለሞት፤ ከዚሁ ቁጥር የማይተናነሱትን ለአካል ጉዳት ፣ እንዲሁም  በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት አውድሞ አልፏል። ይህ ብቻም አይደለም፤ ጦርነቱ ያስከተለው ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት በቅርብ ዓመታት ዓለማችን ካስተናገደቻቸው የከፉ የሰብአዊ እልቂቶችን ካስተናገዱ ክስተቶች አንዱ ሆኖ አልፏል። ክስተቱ ምናልባትም በአሃዝ ከተገለጹ ጥፋቶች ባሻገር ዛሬም ድረስ ያልተፈቱ ማህበራዊ ቀውሶችን ከዓመት ዓመት እያሻገረ ወደ አዲሱ 2017 ዓመት ማድረሱ አንዱ እና ተጠቃሽ ነው። በጦርነቱ  ከትግራይ አቢ አዲ ተፈናቅለው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ብርሃነ አዲስ ዓመት ቢመጣም ለእርሳቸው ተስፋ ይዞላቸው አልመጣም ። ለአራት አመታት በተስፋ ሲጠብቁት የነበረው እና ወደ ቤታቸው ለመመለስ የነበራቸው ተስፋ መሟጠጡን ይናገራሉ ።

በትግራይ ክልል ተጀምሮ ወደ አጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረው እና ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ ሰዎችን ለሞት፤ ከዚሁ ቁጥር የማይተናነሱትን ለአካል ጉዳት ፣ እንዲሁም  በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብት አውድሞ አልፏል። ምስል Million Haileselassie/DW

 ህወሓት የትግራይ ክልላዊ መንግሥትን ወነጀለ

« እኔ በበኩሌ ተስፋ የለኝም። ተስፋ የሚባል የለም። ምን መሰለህ እንግዲህ ያው አራተኛ ዓመታችን ነው።  የተፈናቀልነው በጥቅምት ወር 2013 ነው። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ያየነው ምንም አይነት ዉጤት የለም። እንደምታየው አሁን በተለይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተባለው ለስልጣን ሽኩቻ እንጂ ለተፈናቃይ የተባለ ነገር የለም።»
የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት ከህወሓት ጋር በፕሪቶሪያ የደረሰው የሰላም ስምምነት ትግራይ ውስጥ አንጻራዊ ሰላም አስገኝቷል። ነገር ግን ክልሉን ለሌላ የደህንነት ስጋት የዳረገ እና አሁንም ድረስ መፍትሄ ያልተበጀለት የህወሓት አመራር መከፋፈል እና እሰጥ አገባ ለህዝቡ ሌላ ስጋት ይዞበት እንደመጣ ነው የሚነገረው ። የመቀሌ ከተማ ነዋሪው አቶ መረሳ እንደሚሉት አዲሱን ዓመት የተቀበሉት በመሪዎቻቸው መካከል የተፈጠረው መከፋፈል በፈጠረባቸው ስጋት ውስጥ ሆነው ነው።

 ወደ ቀያቸው የተመለሱ የትግራይ ተፈናቃዮች ደስታና መመለሱ የዘገየባቸው ተፈናቃዮች ቅሬታ
 
«መሪዎቻችን ለሁለት ስለተሰነጠቁ ነው የምናዝነው እንጂ አዲሱን ዓመት ሰላም በመዋላችን በጣም ደስተኛ ነን። መከፋፈሉ በጣም አደገኛ ነው። ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ዕድል እና ጥሩ አስተሳሰብ ይዞ ያልመጣ ስለሆነ ለምሳሌ የዕገሌ ጎራ የእገሌ ጎራ የሚባለው ነገር ለትግራይ ህዝብ አንድም የሚጠቅመው ነገር የለም። »
በኢትዮጵያ ለውጥ መጣ ከተባለ ማግስት ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በመንግስት እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ብሎ በሚጠ,ራው ታጣቂ ቡድን መካከል የሚደረገው ጦርነት አሁንም መጣፊያ አልተገኘለትም። የግጭት ጦርነቱ አ,ድማስ እየሰፋ ፣ በሂደት በትጥቅ ከሚደረገው ዉግያ ባሻገር መዲናዋ አዲስ አበባ አቅራቢያ ሳይቀር በዜጎች ላይ የሚፈጸመው ዕገታ ፤ ዝርፊያ እና ግድያ እየተባባሰ  እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። ለወትሮም  በተዳከመ ሃገራዊ ኤኮኖሚ ላይ የተደመረው የዋጋ ግሽበት እና የኑሮ ውድነት የተማረረው ነዋሪው  ጦርነት እና ዕገታ ያስከተለበት የእንቅስቃሴ ገደብ ህይወት ከድጡ ወደ ማጡ እንዳደረገባቸው ነው ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የተናገሩት።
ስማቸውን እንዳይገለጽ የጠየቁን የነቀምቴ ከተማ ነዋሪው አዲሱን ዓመት ለወጉ ያህል ተቀበሉ እንጂ የኑሮ ውድነት በዓሉን እንደ በዓል እንዲቀበሉ እንዳላስቻላቸው ነው የነገሩን።

ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም ሰባት ዓመታት ከመንፈቅ ገደማ ወደ ኋላ የምትቀርበት የዘመን ቀመር 2017 ላይ ደርሶ እነሆ 2016 አሮጌ ሆኖ ለአዲሱ ዓመት ተሸጋገረች ። ምስል Seyoum Getu/DW



« በእርሱ በኩል የሚቀር ምንም ነገር የለም ።  በ,ሰው በኩል ይቀራል ፤ በእና በኩል ይቀራል እንጂ ፤እርሱ በሰላም አሻግሮናል ፤ ሰላም ያለው በቤት ውስጥ ነው። ከዚህ ውጭ እንግዲህ በኑሮ ውድነት በኩል ገበያ ሲታይ ዶሮ መግዛት አልተቻለም ፤ ከብት መግዛት አልተቻለም፤ የሚያርስ ከብት ወደ ስልሳ ስልሳ  አምስት ሺ ነው የተገዛው ለቅርጫ እንኳ መግዛት አልተቻለም ፤ብር እንዳለ ወረቀት ሆኗል፤ በዓል እንግዲህ ለስሙ መጥቷል፤ ተቀብለናል። »


በክልሉ በመንግስት እና በታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ጦርነት እንዳማረራቸው የሚናገሩት እኚሁ የነቀምቴ ነዋሪ ከሚኖሩበት ከተማ  ወደየትኛውም አቅጣጫ ለመንቀሳቀስ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ይናገ,ራሉ ። በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል ሰላም ለማውረድ ሲደረጉ የነበሩ ንግግሮችም አለመስመራቸውም ለሰላማዊ ነዋሪው ተስፋ አስቆራጭ ነው ። እርሳቸውም ቢሆኑ ተ,ስፋቸውን ከሰው ላይ አንስተው  ወደ ፈጣሪ ማዞራቸውን ነው የሚናገሩት ።

 የኦሮሚያ ክልል የሰላም ጥሪ ጉጉትና አስቻይ አውዱ

« ተስፋ የምናደርገው ነገር ከእግዚአብሔር በስተቀር ከጫካም ሆነ ከዚህ ከመንግስት አካባቢም ሆነ ተስፋ የለም። ተስፋ አይኖረንም ። መንግስት የሚለው የህዝቡን ሰላም መጠበ,ቅ ሲገባው ፤ወይ አሸንፎ እነርሱን ማባረር ሲገባው ፤ ወይ ደግሞ ወደ ሰላም ኑ እንመካከራለን ብሎ በእውነት ቢያደርግ ኖሮ ቆንጆ ነበር»
አዲሱ የኢትዮጵያውያን 2017 የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎሽን ብቻ አይደለም ይዞ የመጣው ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጋር የገባችው እሰጥአገባም ከመረገብ ይልቅ ትኩሳቱ ከዕለት ለት እየጋለ ፤ውጥረቱም በዚያው ልክ እያየለ የሄደ መስሏል። ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችው የወደብ ኪራይ ውል ሶማሊያን አ,ስቆጥቷል። ሁነቱ ከኢትዮጵያ ፣ሶማሌ ላንድ እና ሶማሊያ ውጭ ሌሎች የቀጣናው ሃገ,ራትን ተሳትፎ በግልጽ እያሳየ መጥቷል። በቅርቡ ግብጽ የጦር መሳሪያ የጫኑ አውሮፕላኖችን ወደ ሶማሊያ መላኳ  እና በቀጣይም ወታደሮቿን ልታሰፍር እንደምትችል መነገሩ የአ,ፍሪቃ ቀንድ ሌላ  ትኩሳት ውስጥ እንዲገባ አ,ድርጎታል። በ,ዚህ ብቻም አላበቃም፤ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሌ ላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት ተግባራዊ ካደረገች  የኢትዮጵያ አማጽያንን ልታስታጥቅ እንደምትችል አስታውቃለች። የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አህመድ ፊቂ እንዳሉት የኢትዮ ሶማሌላንድ ስምምነት ከተተገበረ «የኢትዮጵያ መንግስትን ለመጣል ከሚታገሉ አማጽያን ጋር ለመገናኘት እንሞክራለን » ማለታቸውን ዓለማቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

የኢትዮጵያ ሶማልያ ዉጥረት አሳሳቢ ነዉ ተባለ


በአዲሱ ዓመት አዲስ ተስፋ ይዘው መሻገራቸውን የሚናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪው አቶ በፍቃዱ እንደሚሉት የኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ችግር ከቀጣናው በላይ የውስጡ ነው ትኩረት ማግኘት ያለበት  ። የውስጥ ችግር ከተፈታ ሌላውን በአንድነት  እንደአመጣጡ መመለስ ይቻላል ባይም ናቸው።እርሳቸው ተስፋ የሚያደርጉበት ደግሞ  የሀገር ውስጥ ግጭት ጦርነት በንግግር ይፈታል የሚል ነው።   
« መንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ነው እያደረገ ያለው ፤ ህብረተሰቡም በተለያየ ቦታ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ እንደከበዳቸው በሰልፍም ሲገልጹ ቆይተዋል። በቅርብ ጊዜ በተለይ በሰሜን ሸዋ አካባቢ እና እነዚህ ነገሮች ሄደው ሄደው ሁለቱም ወገን ወደ ሰላም ሊያመጡ የሚችሉ ገፊ ምክንያቶች ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ» 

አዲሱ የኢትዮጵያውያን 2017 የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ምስቅልቅሎሽን ብቻ አይደለም ይዞ የመጣው ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጋር የገባችው እሰጥአገባም ከመረገብ ይልቅ ትኩሳቱ ከዕለት ለት እየጋለ ፤ውጥረቱም በዚያው ልክ እያየለ የሄደ መስሏል።


በተለያየ አጋጣሚ በ,አራቱም የየሀገሪቱ አቅጣጫዎች የሚሰጡ አስተያየቶች በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ቅድሚያ ይሰ,ጣሉ ፤ በዚያው ልክ  የኤኮኖሚ እና የኑሮ ውድነት ጉዳይ መፍትሄ እንዲበጅለት የሚጠይቀው ድምጽ ቀጥሎ ገዝፎ ይሰማል። 

በአዲስ አበባ ከተማ የኢኮኖሚ ማሻሻያውን የተከተለው የገበያ አለመረጋጋት
በእርግጥ ነው መዲናዋ አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም በተለየ ሁኔታ አምራ እና አሸብርቃ አዲሱን አመት ተቀብላለች ። ይህ ግን የሆነው ዜጎች በ,ሰላም ወጥተው በሰላም የመግባት የደህንነት ስጋት በሚሰማቸው ወቅት እንዲሁም  የዋጋ ግሽበት ያስከተለው ሁለንተናዊ የኑሮ ውድነት ቅጥ ባጣበት ወቅት በመሆኑ የነዋሪውን ስሜት ሳያደበዝዘው እንዳልቀረ ነው የሚነገረው ። 
ኢትዮጵያ በአማራ ክልል በአግባቡ ያልተዘ,ገበበት እና በትክክል እየተካሄደ ስላለው ግጭት ጦርነት እና ስላስከተለው ቀውስ ከገለልተኛ ወገን መረጃ ማግኘት አዳጋች ሆኗል። በተለይ በጎጃም ፣ ጎንደር እና ሰሜን ወሎ አካባቢዎች በየጊዜው በሚደረገው ጦርነት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት አስከፊ አደጋ ላይ ስለመሆኑ ከየአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ ። በ,ኦሮሚያ ክልል በምዕራባዊ ማዕከላዊ እና ደቡባዊ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ያልተቃረጡ ግጭቶች ይሰማሉ ፤ የሰላማዊ ሰዎች እንቅስቃሴም በከፋ ሁኔታ ተስተጓጉሏል።

የወጣቶች የአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ስጋት

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢም አንዴ ፋም አንዴ ጋም እያለ የሚከሰተው ግጭት ለንጹሃን ሞት ምክንያት ሆኗል።, 
የኢትዮጵያ መንግስት የወሰደው የኤኮኖሚ ማሻሻያ አካል የሆነው እና የውጭ ምንዛሬ ተመን ለውጥ የዋጋ ግሽበቱን እና የኑሮ ውድነቱን ማባባሱን ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት ። የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ምሬትም አይሏል። እንደዚያም ሆነው ግን ያነጋገርናቸው አንዳንድ ነዋሪዎች ያልተማጠጠ  ተስፋቸውን ይገልጻሉ ፤ ቢሆንልን የሚሉትንም ሃሳብ ያጋራሉ ።
«ሰላሙ እና መልካም የሚታየውን መልካም ተስፋ ሁሉም ዜና አጠንጥኖ ሆላችን አዎንታዊ ጎኑ ሀገ,ራችን እንድትቀየር ነው የማስበው » « ሁለቱም የእኛው ስለሆኑ በሰላም ነገሮች የሚፈታበት እና እያንዳንዱ የክልልም ይሁን የተለያዩ ጥያቄዎች የሚፈቱበት ዘመን የሚፈቱበት ዘመን እንዲሆን ነው የኔ ተስፋ እና ምኞቴ»
ይህ የብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን ተስፋ እና ምኞት ነው። መንግስት እና ተፋላሚዎች በአዲሱ ዓመት በእርግጥ ተስፋ እና ምኞታቸው ምን ይሆን ? ታምራት ዲንሳ ነኝ አበቃሁ ።
ታምራት ዲንሳ 
ጸሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW