አዲሱ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ ጥናት
ረቡዕ፣ ሰኔ 24 2018
ይህ የቀረበው የ11 በመቶ የጭማሪ ገደብ በሀገሪቱ ያለውን የዋጋ ግሽበት፣ የሕዝቡን የመግዛት አቅም እንዲሁም ተጨባጭ የሕዝብ ኑሮ ሁኔታ ያገናዘበ እንደሆነ ተገልጿል። ላለፉት ሁለት ዓመታት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይጨምር እገዳ ተጥሎ መቆየቱ የሚታወስ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደርን በተመለከተ የተለያዩ መመሪያዎችንና ውሳኔዎችን አስተላልፈዋል። የመንግሥት ዋነኛ ዓላማ የኑሮ ውድነቱን ጫና መቀነስና ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ያለአግባብ ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይፈናቀሉ መከላከል እንደሆነ ተገልጿል። በአዲሱ መመሪያ መሠረት፣ ማንኛውም አከራይና ተከራይ በየወረደው በሚገኙ የመንግሥት መዋቅሮች ዘንድ በመቅረብ የኪራይ ውላቸውን በሕጋዊ መንገድ ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል ተብሎዋል። ከዚህ ውጭ በሕጋዊ መንገድ ያልተመዘገቡ እና ዕውቅና የሌላቸው የኪራይ ውሎች በሕግ ፊት ፈጽሞ ተቀባይነት እንደማይኖራቸው መንግሥት በጥብቅ አሳስቧል። የአዲስ አበባ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ሀላፊ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ ይህንን በአደባባይ ይህንን ቢሉም መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን አሁንም ፈታኝ መሆኑን ተከራዮች ይናገራሉ።
«በቤት ኪራይ ዋጋ ምክንያት ልጆቼን ባዶ ሚዳ ላይ ከማሳድራቸው ባዶ ሆዳቸውን ባሳድራቸው ይሻላል እያልኩ በስጋት እያበላሁ ሳይሆን እያቀመስኩ ነው የምኖረው መንግሥት አሁን ያለውን የተከራይ እና አከራይ ውል እንዳለ ማቆየቱ እና ማራዘሙ ጥሩ ሆኖ ሳለ ተከራዩ በርግጥ የሚከፍለው ምን ያህል እንደሆነ ቢያጣራ ጥሩ ነው» ስትል የምትናገረው በክራይ ቤት የምትኖረው እህት ናት።
ሌላው ተከራይ «እነሱም የሚኖሩበት ነው እኛም ያመጣናትን ለነሱ ነው የምንሰጠው መተሳሰብ ብንችል መልካም ነው። የቤት ኪራይ የምንችለው ከውጭያችን ከቀነስን ብቻ ነው» ይላሉ።
«የምሠራውም የምኖረውም በኪራይ ነው። እስካሁን ኪራይ ጨምር አልተባልኩም» የሚሉ እድለኛ ተከራይም አሉ። ተከራዮች ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግባቸው ወይም እንግልት ሲደርስባቸው ለየአካባቢው ክፍለ ከተማና ወረዳ ቅሬታ ማቅረብና መጠቆም እንደሚችሉ ተገልጿል።
ይህ በ ኢትዮጵያ መንግሥት፣ በአከራዮች እና በተከራዮች መካከል ያለው የሀሳብ መጋጨት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን፣ አዲሱ የቤት ኪራይ መመሪያ በከተማዋ ያለውን የቤት ኪራይ ገበያና የዜጎችን ኑሮ ምን ያህል ያረጋጋዋል የሚለው ወደፊት የሚታይ ይሆናል።
ሃና ደምሴ
ሸዋዬ ለገሠ
አዜብ ታደሰ