አዲሱ የሱዳን የህግ ማሻሻያና የቲምቡክቱ የጦር ወንጀል ክስ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14 2012
ለሶስት አስርተ አመታት ሱዳንን ያስተዳደሩት ኦማር አልበሽር በጎርጎሮሳዊው ሚያዚያ 2019ዓ/ም በህዝባዊ አመፅ ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ሰሞኑን በሀገሪቱ የተደረገው የህግ ማሻሻያ እንደ ሁለተኛ አብዮት የሚቆጥሩት ብዙዎች ናቸው።ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው የሱዳን ሉአላዊ ምክር ቤት ያፀደቀው የህግ ማሻሻያ የሴት ልጅ ግርዛትን የሚከለክል፣እናቶች ከልጆቻቸው ጋር ጉዞ ለማድረግ ከወንድ ዘመዶቻቸው ፈቃድ መጠየቅን የሚያስቀር እንዲሁም የዕስልምና ሀይማኖት ተከታይ ላልሆኑ ሰዎች የአልኮል መጠጥ መፍቀድን ማሻሻያው ያጠቃልላል።በሀገሪቱ እስከሞት ያስቀጣ የነበረው የሀይማኖት ክህደት በወንጀልም ከተሻሻሉት ህጎች መካከል ነው።
በአምባገነን አገዛዛቸው የሚወቀሱት ኦማር አልበሽር በተቃውሞ አመፅ ከመንበረ ስልጣናቸው ከተወገዱ ከአንድ አመት በኋላ በሀገሪቱ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀውን ጠንካራ እስላማዊ ፖሊሲዎች እና የሸሪአ ህጎችን የማሻሻሉ ሂደት በዓለም ዙሪያ አድናቆት ተችሮታል፡፡የዶቼ ቬለ የካርቱም ዘጋቢ ሀሰን ኦሲአዳም ማሻሻያው በሀገሪቱ የመጀመሪያ የዲሞክራሲ ርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውንም ያሳያል ይላል።«በእርግጥ ይህ ገና ጅምር ነው።ይህ ርምጃ ሱዳን እንደ ሀገር ለህዝቦቿ መብት ዕውቅና በመስጠት ረገድና ሱዳንን ዲሞክራሲያዊና ሰላም የሰፈነባት ሀገር በማድረግ ረገድ የመጀመሪያ ርምጃ ነው።»
ገለልተኛ ተንታኝ የሆኑት ማጊዲ ኤል-ጊዞሊም የተደረጉት ለውጦች አስፈላጊ መሆናቸውን ይስማማሉ ፣ ነገር ግን የመንግስት እርምጃዎች የሱዳንን ማህበረሰብ የበለጠ ሊከፋፍሉና ሊያምታቱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸው ፡፡የሪፍት ቫሊ የትምህርት ተቋም ባልደረባው ማጊዲ፤ የተደረጉት ለውጦች ተጨባጭ ውጤት ስለማምጣታቸውም ጥርጣሬ አላቸው። መንግስት ማሻሻያውን ያደረገው በወረቀት ላይ ለውጥ ማየት የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስደሰት ነው ብለውም ያስባሉ።ለሀሰን ኦሲአዳም ግን ለውጥና ነፃነት ሲጠይቅ ለነበረው የሱዳን ህዝብ እነዚህ ማሻሻያዎች ትልቅ ርምጃዎች ናቸው። ለሲቪሉም ማህበረሰብ ያላቸው አንድምታ ከፍተኛ ነው የሚል እምነት አለው። «ለሱዳን የተቃውሞ አመፅ መነሻው ምክንያት አንዱና ዋነኛው የነፃነት ጥያቄ ነበር።እንደማስበው በተቃውሞው ወቅትም ይሁን በአልበሽር ጊዜ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይህንን በማቀንቀን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ስለዚህ ይህ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና በሱዳን ለመጣው አብዮት ትልቅ ድል ይመስለኛል።»ማጊዲ ማሻሻያውን ሲተቹ የሀይማኖት ክህደት ወንጀልን ለመሻር የተሰጠው ውሳኔ እንደ አንድ ምሳሌ ሊታይ ይችላል ይላሉ።በሀገሪቱ በሀይማኖት መቀየር ወንጀል የሞት ቅጣት ተፈፃሚ የሆነው ፤አል-በሽር ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት በጎርጎሮሳዊው በ1989 ዓ/ም በአንድ አዛውንት ብቻ መሆኑንም ያስረዳሉ።እንደ እርሳቸው ገለፃ ከዚያ ወዲህ ጉዳዩ የተነሳው በ2014 ዓ/ም ማርያም የሃያ ኢብራሂም ኢሻግ በተባለች ወጣት ላይ ነበር። ማርያም የተከሰሰችውና ፍርድ ቤት የቀረበችው ክርስትናን በመቀበሏ ነበር ። ሆኖም በዓለም አቀፉ እና በአከባቢው ማህበረሰብ ግፊት ምንም አይነት ፍርድ ሳይፈረድባት በመጨረሻም አገሪቱን ለቃ መውጣቷን ያስታውሳሉ፡፡እንዲያውም ይላሉ ኤል-ጊዞሊ ሀይማኖትን የመካድ ወንጀል በሀገሪቱ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን መምቻ መሣሪያ ነበር።ያ ማለት መንግሥት ሰዎች ሃይማኖታቸውን ሲቀይሩ ብዙውን ጊዜ ሲተገበር የማይታይና ጉዳዩ የሆነ ጠርዝ ላይ ያለ ክስተት ነበር ይሉታል።
ጋዜጠኛ ሀሰን እንደሚለው ግን መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብና ከሀገር ውስጥ የሚደርስበትን ግፊት ለመቋቋም ማሻሻያው የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም ።«አሁን ህዝቡን የሚያዳምጥ የሽግግር መንግስት አለ።ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር ውጤታማ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ እነዚህ ሁለት ነገሮች ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። እነዚህን የግለሰብ ነፃነትን የሚረግጡ ህጎች ማሻሻል ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብና በተመሳሳይ ከሀገር ውስጥ የሚመጣውን ግፊት ለመቋቋምም ይረዳል።»የሱዳን ህዝብ ካለፈው ዓመት የተሃድሶ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ተቃውሞ ላይ ስለነበር ፤ በአሁኑ ወቅት የህጎቹ መሻሻል ትክክለኛ ጊዜ መሆኑንም ይናገራል። «እነዚህ ህጎች በእርግጥ የግለሰብን ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነት የሚጥሱ ነበሩ። ሀገሪቱ አሁን በሽግግር ጎዳና ላይ ነው ያለችው ።ስለዚህ በእነዚህ ህጎች ላይ ለውጥ ለማድረግ ይህ ጊዜ ብሩህ ነው ብዬ አስባለሁ።» አል -ጊዞሊ በበኩላቸው የሴት ልጅ ግርዛትን በህግ ማገድ አስፈላጊ የመንግስት እርምጃ መሆኑን ያምናሉ። ነገር ግን የሴት ልጅ ግርዛትን መከልከልና በወንጀል የሚያስቀጣ ማድረግ ብቻውን በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን እንደዚህ ዓይነቱን ጥቃት ለመዋጋት ትክክለኛ መፍትሄ ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ ፡፡ የሴትልጅ ግርዛትን የሚከለክል ሕግ ሲወጣ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም የሚሉት አል-ጊዞሊ ይህ አይነቱ ማሻሻያ የተራማጅ መንግስታት ወይም ራሳቸውን ተራማጅ ብለው የሚገልፁ መንግስታት ምልክት መሆኑን ያስረዳሉ።እንደ እርሳቸው ገለፃ በቅኝ ግዛት ወቅት እንዲሁም በ1970 ዎቹ በሀገሪቱ የሴት ልጅ ግርዛትን ለመግታት የተደረጉ ሁለት ቀደምት ሙከራዎች ቢኖሩም ፤ተጨባጭ ውጤት ግን አላመጡም። ያ በመሆኑ በጎርጎሪያኑ 2014 ዓ/ም የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ባወጣው መረጃ መሠረት የሱዳን የሴት ልጅ ግርዛት ከ86 በመቶ በላይ ደርሶ ነበር፡፡ስለሆነም ይህ ህግ ሥር ከሰደዱ ማህበራዊና ባህላዊ ደንቦች ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ፤ እንደ ባህላዊ ልምድ ተደርገው የሚቆጠሩና በቤት ውስጥ የሚፈፀሙ ጥቃቶችን ለመዋጋት፤ የህግ አማራጮች ብቻ የተሻሉ መንገዶች ላይሆኑ ይችላሉ።ስለዚህ ለህጉ ተፈጻሚነትና ጥቃቱን ለመከላከል ከተፈለገ የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አስምረውበታል።
የቲምቡክቱ የጦር ወንጀል ክስ
በምዕራብ አፍሪዊቷ ሀገር ማሊ በጎርጎሮያኑ 2012 ዓ/ም አጥባቂ የእስላምና ጥምረት የተባለ ቡድን በሰሃራ በረሃ የምትገኝ ቲምቡክቱ የተባለች ጥንታዊት ከተማ ተቆጣጥሮ ነበር።በጥር 2013 ዓ/ም የማሊና እና የፈረንሳይ ሀይሎች ከተማዋን ነፃ እስኪያወጧት ድረስ ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በመፈፀምና ለአንድ ምዕተአመት ያስቆጠረን ቅርስ አውድሟል በሚል ቡድኑ ይከሰሳል። ዘሄግ የሚገኘው የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በ2018 በቁጥጥር ስር የዋሉትን አል ሐሰን አብዶል አዚዝ ሞሐመድን ቡድኑን ይመሩ ከነበሩት መካከል አንዱ ናቸው ብሎ ያለፈው ማክሰኞ ክስ መስርቶባቸዋል ፡፡አል ሀሰን ከሚያዚያ 2012 እስከ ጥር 2013 ባለው ጊዜ ሰሜናዊ ማሊን የገዛው «አንሳር ዲን» ወይም የእምነት ተሟጋች የተባለው ታጣቂ ቡድን አባልና የእስላማዊ ፖሊስ ዋና አስተዳዳሪ የነበሩ ናቸው። በዚህ ወቅት ታዲያ በሰዎች በተለይም በሴቶች ላይ ለደረሰው ስቃይና እና እንግልት ተጠያቂ መሆናቸውን አቃቬ ህግ ገልጿል። ተከሳሹ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል በሀገራቸው ባህላዊ ነጭ ሻሽ የፊት ገጽታቸውን ሸፍነው ያለፈው ማክሰኞ ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም ምንም አይነት መልስ አልሰጡም ተብሏል።
በማክሰኞው ችሎት በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ዋና አቃቤ ሕግ የሆኑት ፋቶ ቤንሶዳ፤ ተከሳሹ ሰብአዊነትን የሚፃረር ወንጀል ፈፅመዋል ሲሉ ነበር የተደመጡት።«በሰበሰብናቸው መረጃዎች መሰረት ሚስተር አልሳም ከሚያዚያ 2012 እስከ ጥር 2013 ባለው ጊዜ ውስጥ በማሊ ቲምቡክቱ ሰብአዊነትን የሚፃረር ወንጀልና የጦር ወንጀል ፈፅመዋል ሲል መስሪያቤቴ ክስ ይመሰርታል።» አቃቬ ህግ ቤንሶዳ አያይዘውም። «አል-ሀሰን በሰው ልጆች ላይ ለተፈፀመ ወንጀል ተጠያቂ ናቸው ብለን እናስባለን።ሃይማኖትና ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ በግዳጅ ጋብቻ ስም የአስገድዶ መድፈር፣ ወሲባዊ ባርነት እንዲሁም ድብደባ እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶችን ሆን ብለው በመፈፀም በእምሮዊና በአካላዊ ጤና ላይ ከባድ ጉዳቶችን አድርሰዋል።»አል-ሀሰን የተጠረጠሩበትን ወንጀል የፈፀሙት ከታጣቂ ቡድኑ አመራር በተሰጣቸው ትዕዛዝ ነው ወይስ በራሳቸው ስልጣን ነው የሚለውን ለመለየት የነበራቸው ስልጣን ምን ያህል ነው ።የሚለውን ፍርድ ቤቱ ይመረምራል ተብሏል። አቃቬ ህግ ቤንሶዳ ግን የእርሳቸው ትኩረት ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች ፍትህ እንዲያገኙና በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ማድረግ ነው። «ተጎጂዎችን ቀዳሚ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።ተገቢ ፍትህ እንዲያገኙ የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ እንጥራለን ፡፡ እንደዚህ አይነቶቹን አሰቃቂ ወንጀሎችና ኢ-ሰብአዊነትን በመዋጋት በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰላምን ፣ ደህንነትን እና መረጋጋትን ለማምጣት የበኩሌን ለመወጣት ቁርጠኛ አቋም አለኝ ፡፡ይህ የኔ ቁርጠኝነት እና ተስፋ ለማሊ ጭምር ነው ፡፡»ከቲምቡቱ የጦር ወንጀል ጋር በተያያዘ ዘሄግ ውስጥ ይህ ሁለተኛ ክስ ሲሆን፤ በጎርጎሪያኑ 2016 ዓ/ም የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት የቀድሞው «የአንሳር ዲን» መሪ አህመድ አል ፋኪ አል ማሃ በከተማዋ ውስጥ ታሪካዊ ስፍራዎችን ማውደማቸውን ካመኑ በኋላ የዘጠኝ ዓመት እስራት ተበይኖባቸዋል። አሁን ጉዳያቸው እየታየ ባሉት ተከሳሽ ላይም ምስክርነት ይሰጡ ይሆናል የሚል ግምት አለ ፡፡አልቃይዳና «አልሳር ዲኔ» የተባለው እስላማዊ ጥምረት የማሊን ሰሜናዊ ክፍል ቲምቡክቱን በ2012 ዓ/ም ተቆጣጥሮ ወደ ፍርስራሽነት ከመቀየሩ በፊት፤ ከማሊ ዋና ከተማ ባማኮ በስተ ሰሜን አቅጣጫ 1 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቲምቡክቱ፤ በአንድ ወቅት «የበረሃ ፈርጥ» የሚል ስያሜ የተሰጣት እና የ «333 ቅዱሳን»ከተማ ተብላ የምትጠራ ነበረች ፡፡ ከጎርጎሪያኑ 1988 ዓ/ም ጀምሮ ከተማዋ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበችም ነበረች።
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ