1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተመረጠለት

ሰኞ፣ ጥር 1 2015

ዶክተር ተሾመ አዱኛ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ዞኖችን በአንድ በማጣመር የተቋቋመው የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው ተመረጡ። ይኸ የከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ተብሎ የሚጠራውን አወቃቀር የሚያፈርስ ነው። የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ተጠሪነት ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሆኗል።

Äthiopien Stadt Sheger hat ersten Bürgermeister gewählt
የሸገር ከተማ ከንቲባ ቃለመሃላ ሲፈጽሙምስል Seyoum Getu/DW

አዲሱ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተመረጠለት

This browser does not support the audio element.

በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን በማጣመር 12 ክፍለ ከተሞች እና 36 የወረዳ አስተዳደሮችን በማዋቀር ሸገር ከተማ በሚል ስያሜ ዛሬ በይፋ የተመሰረው አዲሱ ወጥ ከተማ ከዚህ ቀደም በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን መዋቅርን ፈራሽ ያደርገዋል። ዛሬ የተመሰረተው ምክር ቤት ተጠሪነቱም ለክልሉ ፕሬዝዳንት ይሆናል ተብሏል። በዚህም የከተማው ምክር ቤት አፈ ጉባኤን ጨምሮ የከተማውን አስተዳደር አስፈፃሚ አካላትንም በይፋ ሰይሟል። በዚህም መሰረት ዶክተር ተሾመ አዱኛ የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ፤ አቶ ጉዮ ገልገሎ በምክትል ከንቲባነት ተመርጠዋል።

የአዲሱ ከተማ አዲስ ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ በተለይም ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቆይታ የቀድሞ ልዩ ዞን መፍረስ እና የአዲሱ ከተማ ምስረታ አስፈላጊነትን በማብራራት ነው ለጥያቄዎቻችን ምላሽ የሰጡን፡፡ ቀደም ሲል በልዩ ዞን ስር ገብተው የነበሩ ከተሞች ሰፊ የማልማት እቅድ ቢያዝላቸውም በታሰበው ልክ ከመሄድ ይልቅ ለህገወት ግንባታ እና መሰረታዊ የአገልግሎት ቅልጥፍና ችግር መጋለት ሌላ አማራጭ በማስፈለጉ ነው ሸገር ከተማ የተመሰረተው ብለዋልም፡፡

ባለፈው ሳምንት ውስጥ በልዩ ዞን ስር ቆይተው በአዲሱ የሸገር ከተማ መዋቅር ስር ያልገቡት እንደ ጫንጮ እና ሰንዳፋ ያሉ ከተሞች ቅሬታ አንስተዋል፡፡ በተለይም ማህበረሰቡ መሰረታዊ የአስተዳደር አገልግሎቶችን ለማግኘት ዞን ድረስ ለመሄድ መገደዳችን ተቀባይነት የለውም በማለት አዲሱ ከተማ ልዩ ዞኑን ከማፍረስም በተጨማሪ አስተዳደሩን መክፈሉን ተቃውመው ነበር፡፡

የሸገር ከተማ ተሿሚዎች ቃለመሃላ ሲፈጽሙምስል Seyoum Getu/DW

የአዲሱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ አዱኛ ግን 160 ሺህ ሄክታር ላይ የተመሰረተው አዲሱ ግዙፍ ከተማ ከዚህ በላይ ቢሰፋ ለቁጥጥርና መምራት አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር የሚችል መሆኑ አስተዳደራዊ ስፋቱን መገደብ የግድ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና ወደፊት የከተማው የማስተዳደር አቅም ታይቶ ጥያቄ የሚያነሱ አከባቢዎች ወደ ከተማው የሚካለሉበት አግባብ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን አዲሱ ከተማ ከዚህ በላይ የመስፋት አቅሙም ሆነ ፍላጎቱ እንደሌሌውም አመልክተዋል፡፡

ዛሬ በይፋ የተመሰረተው ከተማ ገና ከጅምሩ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ውዝግቦች ሲነሱበት ቆይተዋል፡፡ በተለይም በከተማው ምስረታ የከዚህ ቀደሙ ልዩ ዞን ከፊል አስተዳደሮች አለመካተት እና በከተማው ምስረታ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ እውቅና አለመስጠት የአዲሱ ከተማ ምስረታን የህጋዊነት ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው ተብሎም አወዛግቧል፡፡ የአዲሱ ከተማ ከንቲባ ዶ/ር ተሾመ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡

የሸገር ከተማ ምክር ቤት ምስረታ ምስል Seyoum Getu/DW

“ጨፈው ለአስፈጻሚ አካላት በሚሰጠው ስልጣን መሰረት አስፈጻሚው አካል ለህብረተሰቡ ይበጃል ያለውን ውሳኔ በማስተላለፍ ከተማውን በአዲስ አመልክ ለማደራጀት ወደ ጨፌ መሄድን አያሻውም” በማለት በዚህ ረገድ የሚቀርቡትን ትችትና ነቀፋዎች ተቀባነት የሌላቸው በማለት አጣጥለዋል፡፡

በፊንፊኔ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን እና የመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደራዊ ወሰን ከብዙ ውዝግብ በኋላ ዘንድሮ ከተካለለ ገና ወራት ብቻ ተቆጥሯል፡፡ በዚሁ ባጠረ ጊዜ ልዩ ዞኑ ፈርሶ አዲስ የከተማ አስተዳደር መዋቅር ሲመሰረት ከመዲናዋ ጋር ያለው ትስስር ምን ልመስል ይችላል የተባሉት ከንቲባው፡ የአዲሱ ከተማ መዋቅር መዲናዋ ጋር የሚደጋገፍ እንጂ ምንም ጉዳት የማድረስ ውጥን የለውም ብለዋል፡፡ ይልቁንም ሁለቱ ከተሞች ተደጋግፈው ለነዋሪዎቻቸው ምቹ ሁኔታን ለማፍጠር አቅምና እድላቸው ይሰፋልም ነው ያሉት፡፡

ምስል Seyoum Getu/DW

ከህገወጥነት የፀዳ ሳቢ ከተማ መገንባት፣ ጽዱና የተሻለ መሰረተ ልማት መገንባት ብሎም ኢንቨስትመንትን መሳብ ከአዲሱ ከተማ አስተዳደር ምስረታ ዋነኞቹ ግቦች ናቸውም ተብሏል፡፡ በቀጣይ 7 ዓመታት አዲሱ የሸገር ከተማ በቤቶች ልማት አኳያ እንኳ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ማስቀመጡም ተብራርቷል።

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW