1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አዲሱ የትራምፕ የአፍሪቃ መርህ

ሸዋዬ ለገሠ Shewaye Legesse
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 4 2018

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪቃን የተመለከተው አዲሱ መርህ ምን ይዞ ነው የመጣው የሚለው ማነጋገር ጀምሯል። አዲሱ የትራምፕ የአፍሪቃ መርህ ከእርዳታ ይልቅ ንግድ በተለይም ጥሬ ሀብቶች ላይ ያተኮረ ነው።

Südafrika | African Growth and Opportunity Act | AGOA
በጎርጎሪዮሳዊው ኖቬምበር 3 ቀን 2023 ደቡብ አፍሪቃ ላይ የተካሄደው በእንግሊዝኛ ምህጻሩ AGOA የተሰኘው የአፍሪቃ እድገት እና እድል ሕግ ጉባኤ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

አዲሱ የትራምፕ የአፍሪቃ መርህ

This browser does not support the audio element.

 

ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪቃን የተመለከተው አዲሱ መርህ ምን ይዞ ነው የመጣው የሚለው ማነጋገር ጀምሯል። አዲሱ የትራምፕ የአፍሪቃ መርህ ከእርዳታ ይልቅ ንግድ በተለይም ጥሬ ሀብቶች ላይ ያተኮረ ነው። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ይህ አካሄድ ምናልባት አፍሪቃ በኤኮኖሚ ይበልጥ እራሷን እንድትችል የሚያደርግ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ባለፈው ሳምንት ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው ሰነድ አሜሪካ ከተመረጡ የአፍሪቃ ሃገራት ጋር «ለጋራ ጥቅም የንግድ ግንኙነት» ለመመስረት መዘጋጀቷን ያመለክታል። በዚህም በኒኩሊየር የኃይል ምንጭ፤ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ፤ እንዲሁም ቴክኒዎሎጂ ወደ አፍሪቃ ለማስገባት፣ በምላሹም ከአፍሪቃ የተፈጥሮ ሀብትና የኤኮኖሚ አቅም ለመጠቀም አልሟል። ለመሆኑ የትራምፕ አፍሪቃን ዋናኛ የተፈጥሮ ጥሬ ሀብት አቅራቢ የማድረግ እቅድ ለክፍለ ዓለሙ ልማት ይጠቅማል?

የፖለቲካ አለመረጋጋት ለአፍሪቃ ዕድል ነው?

ኬንያዊው የኤኮኖሚ ባለሙያ ጀምስ ሺካዋቲ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ሰነድ አፍሪቃ ዝቅተኛ ተሳትፎ ያላት አድርጎ ያሳያል። ይህ ደግሞ ከአፍሪቃ ሕብረትና ተቋማት ጥረትና ፍላጎት ጋር አብሮ አይሄድምም ባይ ናቸው።

«ብሔራዊ የደኅነት ሰነዱ አፍሪቃ ዝቅተኛ ተሳትፎ ያላት ክፍለ ዓለም አድርጎ ነው የሚያቀርበው፤ ይህ ከአፍሪቃ ሕብረት እና የአፍሪቃ አካባቢያዊ የኤኮኖሚ ስብስቦች ከሚያልሙት ማለትም የኤኮኖሚ ትብብርና እንደ አፍሪቃ በአንድነት መንቀሳቀስ ከሚለው ጋር ተቃራኒ መሆኑ በጣም ግልጽ ነው።»

ሺካዋቲ እንደሚሉት የትራምፕ አቀራረብ ለአፍሪቃ ምንም የሚፈጥረው አዲስ እድል የለም። የሚያደርገው ነገር ካለም እንደውም ግጭቶችን ሊያባብስ ይችላል ነው የሚሉት። በዚህ ደግሞ በኤኮኖሚ ወጣ ወጣ ማለት የጀመሩት የባሕረ ሰላጤው ሃገራት እና የአውሮጳ ሕብረት ሁሉ ተመሳሳይ የጥሬ ሀብት ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውን በማመልከትም ቅርምቱ ሌሎች የግጭት ግንባሮች እንዲከፈሉ ምክንያት ሊሆን እንደሚችልም ስጋት አላቸው።

አዲስ የአፍሪቃ ዩናይትድ ስቴትስ መርህን ይዘው ብቅ ያሉት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕፎቶ ከማኅደር ምስል፦ Alex Brandon/AP Photo/dpa/picture alliance

የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርኀግብር UNDP የአፍሪቃ ቢሮ ዳይሬክተር አሁና ኤዚያኮንዋ የኤኮኖሚ ትብብሩ ለአፍሪቃ እድገት ጥሩ አጋጣሚ ነው ባይ ናቸው። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ የልማት ድጋፍ የሚሰጥ ትብብር ሲሆን እንደሆነም ያስረዳሉ። ሆኖም ግን ከዩናይትድ ስቴትስ በኩል የልማት እርዳታ ትብብር ስለመኖሩ የሚያመለክት ነገር የለም። ትራምፕ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት እንዲህ ያለውን እርዳታ በማቋረጥ ነው። ይህንንም ዋነኛውን የአሜሪካ የእርዳታ ድርጅት USAIDን በይፋ በመዝጋት አሳይተዋል። 

ደቡብ አፍሪቃዊው የኤኮኖሚ ተንታኝ ዳንኤል ሲልክ እንደሚሉት የወቅቱ የአሜሪካ ስልት የሀገሪቱን መርህ በግልጽ የለወጠ ነው።

«አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ስልት ከእርዳታ ይልቅ ንግድ ላይ ነው የሚያተኩረው። ከተለያዩ ምርቶች ጋር በተገናኘ በAGOA አማካኝነት ዩናይትድ ስቴትስ በጥቅሉ ታቀርብ የነበረው ጥቅም አብቅቷል። ለጊዜውም ቢሆን ማለት ነው።»

በጎርጎሪዮሳዊው 2000 ላይ ተግባራዊ የሆነው በእንግሊዝኛ ምህጻሩ AGOA የተሰኘው የአፍሪቃ እድገት እና እድል የተሰኘው ሕግ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ከቀረጥ ነፃ ምርቶቻቸውን ወደ አሜሪካ እንዲልኩ የሚፈቅድ ነው። የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማም የሕጉን አስፈላጊነት በማሰብ በሥልጣን ዘመናቸው በዚሁ የዘመን ቀመር እስከ 2015 ድረስ አራዝመውታል። ዶናልድ ትራምፕ ግን ይህ ሕግ ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ሥራ ላይ እንዳይውል አድርገዋል። ውጤቱ አጠራጣሪ ቢሆንም ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ሕጉ ዳግም ተግባራዊ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ በአሜሪካ ምክር ቤት ክርክር እንደሚደረግ ተነግሯል። 

ለአፍሪቃ የተላለፈው የማንቂያ ደወል

የደቡብ አፍሪቃው የኤኮኖሚ ባለሙያ ዳንኤል ሲልክ የትራምፕ እርምጃ የአፍሪቃ ሃገራት በመካከላቸው ያሰቡትን ነጻ የንግድ ትስስር አጠናክረው ክፍተቱን ለመሙላት እንዲንቀሳቀሱ እድል ይሰጣል ነው የሚሉት። አጋጣሚውም የአፍሪቃ ሃገራት በAGOA ላይ የነበራቸውን የድጎማ መተማመን አጥፍቷልም ባይ ናቸው። የአፍሪቃ ሕብረት የነጻ ንግድ ትስስር ደንብ ከጎርጎሪዮሳዊው 2019 ጀምሮ ተግባራዊ ቢሆንም ገና አልተስፋፋም።

54 አባል ሃገራት ያሉት የአፍሪቃ ሕብረት ፕሮጀክት ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የሚኖርበትን ግዙፍ አህጉራዊ ገበያ ያካትታል። የአፍሪቃን የኢንዱስትሪ ልማት ለማሳደግ ቢሮክራሲን መቀነስ እና ዝቅተኛ ቀረጥ ዋነኞቹ እንደሆኑ ታስቧል።

የአፍሪቃ ጉዳዮች ተመራማሪው ሮበርት ካፔል እንደሚሉት የሰሞኑ የዩናይትድ ስቴትስ ሰነድ ለአፍሪቃ አስቸኳይ መልእክት አስተላልፏል። 

«የፕሬዝደንት ትራምፕ እርምጃ ለአፍሪቃ ሃገራት፤ መንግሥታት፣ ሲቪል ማኅበራት፤ እንዲሁም የንግዱ ዘርፍ በትክክል የማስጠንቀቂያ ተኩስ ነው። ራሳችሁን ከአውሮጳ፤ ከቻይና፤ ከሩሲያ እንዲሁም ከዩናይትድ ስቴትስ ጥገኝነት ነጻ መሆናችሁን በአግባቡ አረጋግጡ የሚል።»

ካፔል የአፍሪቃ ሃገራት ኢንዱስትሪያቸውን ማሳደጋቸው ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ። እንዲያ ከሆነም የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ነጻ የንግድ አካባቢን ማቋቋም ይችላል፤ ወታደራዊ ትብብሩን ያጠናክራል፤ ከዚህም ሌላ አፍሪቃውያን የተለያዩ ስልታዊ የትብብር አማራጮችን መመልከት እንደሚችሉም አመልክተዋል።

ብዙውን ጊዜ ፕሬዝደንት ትራምፕ ለአፍሪቃ እና ለአፍሪቃውያን ፖለቲከኞች የሚሰጡት ምላሽ በዘለፋ የታጀበ ነው። አሁን ደግሞ በርካታ አጀንዳዎችን ያጨቀ መርሀቸውን ይፋ አድርገዋል። ካፔል መልእክቱ ግልጽ ነው በማለት ያስጠነቅቃሉ፤ «በሚኖረው መቀራረብ እና ትብብር መምነሽነሽ አይታሰብም።»

የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ሶቺ ሩሲያ በተካሄደው በአፍሪቃ ሩሲያ ጉባኤ ላይ ፎቶ ከማኅደርምስል፦ Sergei Chirikov/Poo/AP

የቻይና አሜሪካ ፉክክር

ከመልክአ ምድራዊ ስልት አኳያ አፍሪቃ ለዩናይትድ ስቴትስ ቁልፍ ሚና የምትጫወት ክፍለ ዓለም ናት። ቻይና ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ከአብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገራት ጋር ዘርፈ ብዙ ትስስር አበጅታለች። የቻይና አፍሪቃ ቅርርብ ዋሽንግተን ላይ መልእክቱ ሌላ ነው። አዲሱ የአሜሪካ የደኅንነት ስልት ግጭቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ እድሎች መኖራቸውን ያነሳል። የአፍሪቃ ጉዳዮች ተመራማሪው ሮበርት ካፔል ግን እዚህም ጋ ዋናው ትኩረት ጥሬ ሀብት ላይ ነው ይላሉ። በምሳሌነትም የታላቁ ሐይቅ አካባቢ ሃገራት መካከል ያለውን ግጭት ለመፍታት የተደረገውን ያነሳሉ። ትራምፕ በሩዋንዳ እና ዴሞክራቲክ ኮንጎ መካከል ያለው ውዝግብ ቆሞ ሰላም እንዲወርድ ያደረጉትን ሙከራ አንዱ ነው። አልዘለቀም እንጂ የሰላም ስምምነትም ሁለቱ ሃገራት ተፈራርመዋል። 

የቡድን 20 አባል ሃገራት የተካተቱበት ብሪክስ ቻይና እና ሩሲያ ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር ይበልጥ እንዲቀራረቡ ያመቻቸ መድረክ ነው። እንዲያም ሆኖ ሲልክ እንደሚሉት እነዚህ ጉልበታማ ሃገራት ወደ አፍሪቃ የሳበው ብዙም ሥራ ላይ ያልዋለው የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ነው። አፍሪቃውያን ነቅተው ለሥልጣን የሚያደርጉትን የእርስ በእርስ ፍልሚያ ትተው የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው እጅ ለማስገባት ቢሠሩ ይበጃቸዋል በማለት መክረዋል። 

ሸዋዬ ለገሠ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW