አዲሱ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ካቢቤና ተቃውሞው
ሰኞ፣ ሚያዝያ 13 2017
አዲሱ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ አዲስ የካቢኔ አባላት ሰይመዋል። ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞ ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ታግደው የነበሩ ጀነራሎች ወደ ስራ እንዲመለሱ አድርገዋል። በሌላ በኩል የግዚያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አካታች አይደለም ሲል በጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ክንፍ ወቅሷል።
በቅርቡ የትግራይ ግዝያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንትነት የተረከቡት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ አዲሱ ካቢኔአቸው ያሳወቁ ሲሆን የዶክተር ደብረፅዮን ህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ምክትል ፕሬዝደንት መሆናቸው ተረጋግጧል። ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ በፊት በካቢኔ ያልነበሩ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ክንፍ ማእከላይ እና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት በዚህ የጀነራል ታደሰ ወረደ ካቢኔ ተካተዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀድሞ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ታግደው የነበሩ ጀነራሎ፥ በአዲሱ ፕሬዝዳንት ውሳኔ ዳግም ወደ ስራ መመለሳቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ጀነራል ፍስሃ ኪዳኑ የትግራይ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሐላፊ ሆነው እንዲቀጥሉ መደረጉም በፕሬዚዳንቱ ተፈርሞ የወጣ ደብዳቤ ያመለክታል።
ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕረዚደንት ጀነራል ታደሰወረደ ለክልሉ መንግስታዊ እንዲሁም ለመንግስት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሐን ብቻ በሰጡት የመጀመርያ መግለጫቸው የግዚያዊ አስተዳደሩ የመጪው ግዚያት የትኩረት አቅጣጫዎች አብራርተዋል። ፕሬዝደንቱ እንዳሉት በትግራይ ሰላም ማረጋገጥ፣ የህዝብ ድህንነት መጠበቅ እንዲሁም የፍትህ ስርዓቱ ማሻሻል ከቀዳሚዎቹ ተግባራት መካከል እንደሚሆን አንስተዋል።
በትግራይ በተለይም በጦርነቱ እና ከጦርነቱ በኃላ ባለግዜ እየተበራከተ መሆኑ የሚነገረው ሕገወጥ የማዕድናት ማውጣት ስራ መቆጣጠር ደግሞ ሌላው ትልቅ የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆን በፕሬዝዳንቱ ተገልጿል።
ጀነራል ታደሰ "በማዕድን ማውጣት ስራ አሁንም ሕገወጥ ተግባር በተጋሩ እየተፈፀመ መሆኑ አስደንጋጭ አለመሆኑ አንድ ነገር ሆኖ፥ ይህ ሕገወጥ ተግባር ከቀጠለ ነገ እጃችን በሚጠመዝዙ ትላልቅ ሐይሎች እጅ ልንገባ እንደምንችል አውቀን፥ በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ተጋሩ እስካሁን የሰበሰቡት ሀብት በትግራይ ልማት ላይ እንዲያውሉ ማመቻቸት፣ ያለው ሕገወጥ ማዕድን የማውጣት ስራ ለትውልድ የሚተርፍ መዘዝ ያለው በመሆኑ ሙሉበሙሉ መቆጣጠር እና ስርዓት ማስያዝ ግዜ የማይሰጥ እንዲሁም ምክንያት የማያሻው ጉዳይ ነው" ብለዋል።
በትግራይ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው መመለስ፣ በክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት መስራት እንዲሁም ሕገወጥ የመሬት ወረራ መቆጣጠር እንዲሁም ሌሎች አጀንዳዎች በፕሬዚዳንቱ ዋነኛ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስራዎች እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት መግለጫ ያሰራጨው በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራ የህወሓት ክንፍ የጀነራል ታደሰ ወረደ አዲሱ ካቢኔ አካታች አይደለም በማለት ተችቷል። በአቶ ጌታቸው የሚመራው የህወሓት ክንፉ እንዳለው አዲሱ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ ለአንድ ቡድን ብቻ በማዳላት አካታች ያልሆነ ካቢኔ መስርተዋል ያለ ሲሆን ይህ እንዲስተካከልም ጥሪ አቅርቧል። ግዚያዊ አስተዳደሩ ሁሉን አካታች እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ስንነጋገር ቆይተናል ያለው መግለጫው ይሁንና ፕሬዝደንቱ ለማነጋገር የተደረገ ጥረት እንዳልተሳካላቸውም አንስቷል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ነጋሽ መሐመድ