የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ህብረት አጋርነት
ማክሰኞ፣ የካቲት 24 2012የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ህብረት አጋርነት ዘንድሮ 20 ዓመት ይደፍናል።የተመሰረተውም በጎርጎሮሳዊው 2000 ካይሮ ግብጽ ውስጥ በተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ህብረት ጉባኤ ላይ ነው።አጋርነቱ የሚመራውም ሁለቱ አህጉራዊ ድርጅቶች በሊዝቦን ፖርቱጋል በጎርጎሮሳዊው 2007 ባካሄዱት ሁለተኛ ጉባኤዓቸው ላይ ባጸደቁት የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ህብረት የጋራ ስልት ነው።ዓላማውም የአፍሪቃና አውሮጳን የኤኮኖሚ ግንኙነትን በማጠናከር እና ዘላቂ ልማትን በማራመድ ሁለቱን ክፍለ ዓለሞች ማቀራረብ ነው።በሰላም በፀጥታ በዴሞክራሲ በብልጽግና በትብብር እና ሰብዓዊ ክብርን በማስጠበቅ ረገድ አብሮ መስራትም በአጋርነቱ ተካቷል። ይሁን እና የሁለቱ ህብረቶች አጋርነት አውሮጳ ሰጭ አፍሪቃ ደግሞ ተቀባይ የሆነችበት የሰጭና ተቀባይ ግንኙነት ብቻ በመሆን ይተቻል። ባለፈው ታህሳስ የአውሮጳ ህብረት ከሚሽን ፕሬዝዳንትን የተረከቡት ጀርመናዊቷ ወይዘሮ ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ይህን ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች ለማሳየት እየሞከሩ ነው። ሥራ በጀመሩ በመጀመሪያው ሳምንት የመጀመሪያ የውጭ ጉብኝታቸውን በአፍሪቃ በተለይም በአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ በአዲስ አበባ ማድረጋቸው ትኩረት ስቦ ነበር።ይህ የፎን ዴር ላየን የአፍሪቃ የመጀመሪያ ጉብኝት ምክንያታዊ ነበር።በዚሁ ጉብኝታቸው ከአፍሪቃ ህብረት ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩት ፎን ዴር ላየን መጀመሪያ ወደ አፍሪቃ የሄዱት አፍሪቃ ለአውሮጳ ህብረት አስፈላጊ እንደሆነች ለማሳየት መሆኑን ተናግረዋል።ከርሳቸው ጉብኝት ቀጥሎም የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሼል የፎን ዴር ላየንን ፈለግ በመከተል በየካቲት ተመሳሳይ ጉብኝት አድርገው ነበር። ባለፈው ሳምንት ደግሞ ፎን ዴር ላይየን የህብረቱን ኮሚሽነሮች ይዘው አዲስ አበባ ለሁለተኛ ጊዜ በመሄድ ከአፍሪቃ ህብረት ባለሥልጣኖች ጋር ተወያይተዋል።የሁለተኛው ጉብኝት ትኩረት እንደ መጀመሪያው ጉብኝት ሁሉ ግልጽ ነበር፤የአፍሪቃ ክፍለ ዓለም ለአውሮጳ አስፈላጊ መሆንዋን ዳግም ማሳየት ።በአጭር ጊዜ ውስጥ የተደገመው የፎን ዴር ላየን የአፍሪቃ ህብረት ጉብኝት በክፍለ ዓለሙ የተለየ ፍላጎት እንዳላቸው ያሳያል ተብሏል።ይሁን እና ከአውሮጳ የልማት ፖሊስ አስተዳደር ማዕከል ጌሬት ላፖርት እርምጃውን በተለየ መንገድ ነው የሚያዩት።በርሳቸው አስተያየት የፎን ዴልር ላየን ጉብኝት የሚያመለክተው ሌላ ነው።
«ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባን መልሰው መጎብኝታቸው በተወሰነ ደረጃ መረበሻቸውን ይገልጻል።እንደሚመስለኝ የአውሮጳ ህብረት፣ ሌላው ዓለም አፍሪቃን አጋር ለማድረግ የሚያደረገው ጥረት በመጠኑም ቢሆን ረብሿቸዋል።የዓለም ኃያላን አፍሪቃን ከጎናቸው ማድረግ መፈለጋቸው አውሮጳ እያሳሰባት ነው።በሌላ በኩል ደግሞ አውሮፓ ለአፍሪቃ ያላትን ፍላጎቷን በግልጽ ማሳወቋ በጎ ጎን ነው።»
ፎን ዴር ላየን በጉብኝታቸው እንደተናገሩት የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ህብረት ግንኙነት ፣ከቀድሞ በተለየ መንገድ እንዲካሄድ ይፈልጋሉ።አጋርነቱ እንደ ቀድሞ የሰጪና የተቀባይ ሳይሆን ሁለቱንም ወገኖች በእኩል ደረጃ የሚያስቀምጥ አጋርነት እንዲሆን ነው የሚፈልጉት። የልማት እርዳታ ላይ ብቻ ያተኮረው የእስካሁኑ ግንኙነት በኤኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ጥቅሞች ላይ እንዲያተኩር ይሻሉ። ይህም ውረታን መሠረት ያደረገ የሁለቱንም ጥቅሞች የሚያስከብር ትብብር ይሆናል ነው የተባለው። ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስም አጋርነቱ አውሮጳን እና አፍሪቃን በእኩል ደረጃ የሚያስቀምጥ አጋርነት እንዲሆን ከልብ መፈለጋቸውን የሚያሳዩ ሁለት ነጥቦች እንዳሉ ፎን ዴር ላየን ተናግረዋል።
«አንደኛው ወደዚህ የመጣነው ከ22 ኮሚሽነሮች ጋር ነው።ይህን ያህል ቁጥር ያለው ፤ልዑካን ኖሮም አያውቅም።ይህም ለኛ የአፍሪቃ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት ጉዳይ ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።ሌላው ደግሞ የተነጋገርንባቸው ጉዳዮች ናቸው።አዎ ስለ ሰላም እና ጸጥታ ተነጋግረናል። ከዚሁ ጋርም ስለ እድገት እና ብልጽግናም መክረናል።አስፈላጊ ስለሆነው ስለ ዲጂታላይዜሽንም እንዲሁ የአየር ንብረት ለውጥ እንዴት መከላከል እንደሚቻልም ተወያይተናል።»
ፎን ዴር ላየን ይህን ቢሉም የአዲስ አበባው የሰላም እና የፀጥታ ጥናት ተቋም ባልደረባ ሚሼል ንዳየ ግንኙነቱ በጋራ ጥቅሞች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጉ አዳጋች ሊሆን ይችላል ነው የሚሉት።በርሳቸው አስተያየት ግንኙነቱን ለመለወጥ በቅድሚያ የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል።
«አጋርነቱ እንደገና በማስተካከል ረገድ እንደሚመስለኝ ከእጅግ አስቸጋሪው ጉዳዮች አንዱ ግንኙነቱ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ማድረጉን ማረጋጋጥ ነው።እንደሚመስለኝ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው መቅደም ያለበት።አሁንም አፍሪቃን እንደ ክፍለ ዓለም አውሮጳ የሚያቀርባቸውን ማናቸውንም ሃሳቦች እሺ እያለ የሚቀበል አድርጎ የማየት ዝንባሌ አለ።እኔ እንደማስበው ጌዚው ተለውጧል።አሁን ያሉት ከአዲሱ ትውልድ የሆኑ መሪዎች የሀገሮቻቸውም ጥቅሞች የሚረዱ ናቸው።
የግጭቶችን መስንሴ በማጥናት መፍትሄያቸውን የሚጠቁመው ክራይስ ግሩፕ የተባለው ተቋም የአፍሪቃ አካባቢያዊ ጉዳዮች ክፍል ሃላፊ ኤሊሳ ጆብሰን የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ አጋርነት ተግዳሮት ዘፈረ ብዙ መሆኑን ነው የሚያስረዱት።እነዚህ ተግዳሮቶችም በሁለቱ ህብረቶች ግንኑነቶች ላይ ጫና ማሳደራቸው አይቀርም እንደ ጆብሰን።
«ምንም እንኳን አፍሪቃ ለአውሮጳ ጠቃሚ አጋር ብትሆንም አውሮጳ ብቻ አይደለችም ከአፍሪቃ ጋር መሰል ግንኙነት ያላት።አፍሪቃ እና ቻይና ፣አፍሪቃ እና ሩስያ መሰል ግንኑነቶች አሏቸው። የባህረሰላጤው ሀገራትም በአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ስለዚህ ይህ ለአውሮጳ ተግዳሮት ነው።አውሮጳ በቃልዋ መጽናት አለመጽናትዋ ለአፍሪቃ ህብረት ጠቃሚ አጋር ሆና ለመዝለቅ ሌላው ቁልፍ ተግዳሮት ነው።ሌላ ተግዳሮት ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ነው። የሁለቱ ግንኙነት የሰጭ እና ተቀባይ ነው።የአውሮጳ ህብረት ሰጭ የአፍሪቃ አገራት ደግሞ ተቀባይ ናቸው።ይህ በግንኙነቱ ላይ ከባድ ጫና ይፈጥራል።የቅኝ አገዛዝ ጥላ አሁንም ከክፍለዓለሙ አልጠፋም።ይህ አሁንም በሁለቱ ክፍለ ዓለማት ግንኙነት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል።»
በባለፈው ሳምንቱ የአዲስ አበባው የአፍሪቃ ህብረት እና የአውሮፓ ህብረት ከፍተና ባለሥጣናት ውይይት አጀንዳዎች የፍልሰት ጉዳይ ይገኝበታል። የአውሮጳ ህብረት ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ህገ ወጥ የሚለውን ስደት የአፍሪቃ ሃገራት እንዲከላከሉት ይፈልጋል። ይህን ለማሳካትም የአውሮጳ መንግሥታት የስደት መነሻ እና መተላለፊያ ለሚባሉ ሃገራት ልዩ ልዩ ድጋፎችን ያደርጋሉ።ምንም እንኳን ህገ ወጥ ከሚባለው ስደት መንስኤዎች መካከል ግጭቶች እና ድህነት በዋነኝነት ቢጠቀሱም አውሮጳውያን ለህጋዊው ስደት በራቸውን መዝጋታቸው ሌላው ችግሩን ያባባሰ ምክንያት መሆኑ ነው የሚነገረው።የሁለቱን ህብረቶች ግንኙነቶች በሚመለከቱ ውይቶች ላይ ህገ ወጡን ስደት ለመከላከል አውሮጳ በአማራጭነት ህጋዊውን ስደት እንድትፈቅድ ጥያቄዎች መቅረባቸው አልቀረም።ይሁን እና እነዚህ ጥያቄዎች ሰሚ ያገኙ አይመስሉም። አውሮጳ ለዚህ ጥያቄ መልስ አለመስጠቷም በሁለቱ ክፍለ ዓለሞች ግንኙነት ላይ ጫና ማድረጉ አይቀርም ይላሉ።
«ለአውሮፓ ህብረት ቁልፍ ጉዳይ ስለሆነው ስለ ፍልሰት ለመነጋገር አፍሪቃውያን በፍልሰት ጉዳዮች ላይ ሊሟሉ ይገባቸዋል የሚሏቸውንም ጉዳዮች ማየት ያስፈልጋል።የአፍሪቃ ህብረት አባል ሃገራት ዜጎቻቸው ወደ አውሮጳ በሕጋዊ መንገድ የሚገቡባቸው መንገዶች እንዲመቻቹ እየጠየቁ ነው።የአውሮፓ ህብረት በእነዚህ የአፍሪቃውያን ጥያቄዎች ላይ ለመወያየት በርግጥ ፈቃደኛ ነው የሚለው አነጋጋሪ ነው።ይህም የሁለቱ ክፍለ ዓለማት አጋርነት ወደፊት እንዳይራመድ እንቅፋት መሆኑ የሚቀር አይመስለኝም።»
ፎን ዴር ላየን የሁለቱን ክፍለ ዓለማት ግንኑነት ወደ አዲስ ደረጃ ለማሸጋገር ይፈልጋሉ ።የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋኪ እንዳሉት አፍሪቃውያን ግን አሁንም ጥያዌዎች አሏቸው።
«በማናካሂዳቸው የተለያዩ ውይይቶች ላይ የተለየ አመለካከት ባለንና እና ተመሳሳይ አቋም በማናርምድባቸው ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎችን እናነሳለን።በነዚህ ጉዳዮች ላይም እንደ እውነተኛ አጋር በሁሉም ጥያቄዎች ላይ እንወያያለን።»
ውይይቱ በሚቀጥለው ዓመት ሮም ኢጣልያ በሚካሄደው የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ጉባኤ ላይም ይቀጥላል።በጉባኤው ላይ ፎን ዴር ላየን አዲሱን የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ አጋርነት አቅጣጫ የሚጠቁመውን ስልት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ