1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የስደተኞች የጉዞ መስመር 

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27 2011

የሀገራቸው ሰዎች በዓለም ዙሪያ የሚያካሂዱትን የስደት እንቅስቃሴ የሚከታተሉት ኤርትራዊው ዘካርያስ አሁን እንደደረሱበት የስደት መስመሮቹ ጉዞ በሜዴትራንያን ባህር በጀልባ መሆኑ ቀርቶ፣ የዓለምን እኩሌታ ያህል በሚጓዙበት በአውሮፕላን ተቀይሯል።አብዛኛዎቹ አሁን ወደ ሰሜን አሜሪካ መሄድ ነው የሚፈልጉት ይላሉ ዘካርያስ።

Karte Afrikas neue Fluchtroute DE
ምስል DW

በበረሃ እና በባህር ከአፍሪቃ ወደ ምዕራቡ ዓለም የሚደረግ ስደት በሌላ የጉዞ መስመር ተቀይሯል።የዶቼቬለዋ ዚሞነ ሽሊንድቫይን እንደዘገበችው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከአፍሪቃ በበረሃ እና በባህር የሚሰደዱት ቁጥር እየቀነሰ  ወደ ደቡብ አሜሪካ የሚሄዱት ቁጥር ደግሞ እየጨመረ ነው።ቀጣዩ ዘገባ አዲሱን የአፍሪቃውያን የስደት መስመር ያስቃኘናል ኂሩት መለሰ እጠናቅራዋለች።
የሜክሲኮ ባለሥልጣናት በጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ መጀመሪያ ላይ እንዳስታወቁት ወደ ሃገሪቱ የሚገቡት አፍሪቃውያን ስደተኞች ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሯል።ባለሥልጣናቱ እንደሚሉት አሁን ቁጥራቸው 1900 ይጠጋል።አብዛኛዎቹም ግጭቶች ከሚካሄዱባቸው ከካሜሩን እና ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ነው የመጡት።ዓላማቸው ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ናት።ከምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሃገር ኡጋንዳም በርካታ አፍሪቃውያን በአውሮፕላን ግማሹን ዓለም አቋርጠው ይሰደዳሉ።ለደህንነቱ ሲባል ስሙ ያልተጠቀሰው ኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ የሚገኝ የ23 ዓመት ኤርትራዊ በቅርቡ እነዚህን ስደተኞች ከሚቀላቀሉት አንዱ ሊሆን ይችላል።ባለፈው መስከረም ነበር ከኤርትራው ብሔራዊ ውትድርና ሸሽቶ ሃገሩን ለቆ የወጣው።የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እንደሚሉት ብሔራዊ ውትድርና ለዓመታት የጉልበት ሥራ የሚካሄድበት ግዴታ ነው።ወጣቱ ኤርትራዊ በሃገሩ ተስፋ የቆረጠ ይመስላል።
«በኤርትራ በቅርቡ ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም፤በተቃራኒው እንጂ።ድንበሩ ከተከፈተ ወዲህ እንዲያውም ብሷል።ምንም ተስፋ የለንም።» 
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከሁለት ጦርነቶች እና ለብዙ አሥርት ዓመታት ከተካሄደ ግጭት በኋላ ባለፈው ዓመት የሰላም ውል ተፈራርመዋል።ለዓመታት ተዘግቶ የቆየው የሁለቱ ሃገራት ድንበርም በመስከረም ነበር የተከፈተው።ወጣቱ ኤርትራዊ ይህንኑ ድንበር በእግር አቋርጦ ነበር ኢትዮጵያ የገባው።ሆኖም ኢትዮጵያ የሚገኙት የስደተኞች መጠለያዎች ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ከመጠን በላይ በሰዎች በመጨናነቃቸው ያማርራል።እስካሁን አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ወይም በሱዳን አድርገው በረሃ አቋርጠው ሊቢያ የባህር ጠረፍ ይሄዱ ነበር።ከሊቢያም በሜዴትራንያን ባህር ራሳቸውን ለሞት አደጋ አጋልጠው ይጓዛሉ።አሁን ግን በዚህ የስደት መስመር የሚጓዙ ስደተኞች ቁጥር እየተመናመነ ሄዷል ይላሉ ኡጋንዳ የሚገኘው «አፍሪቃ ሞኒተርስ» የሚባለው መንግሥታዊ ያልሆነ የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ድርጅት ምክትል ሃላፊ ዘካርያስ ገሪማ።
«ሱዳኖች ኤርታራውያኑን እያሰሩ ወደ መጡበት ይመልሷቸዋል።ይህን የሚያደርጉትም አንድ ነገር እያደረጉ መሆኑን ለአውሮጳ ህብረት ለማሳየት ሲሉ ብቻ ነው። ኤርታራውያኑ ተመልሰው ወደ ሃገራቸው ሲሄዱ ለደህንነታቸው አስጊ መሆኑን እነሱም አሳምረው ያውቃሉ።የሚልኳቸው ወደ ሞት ነው።»
ከጎርጎሮሳዊው 2015 ዓም ወዲህ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች አውሮጳ ከገቡ በኋላ በርካታ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ስደተኞች ከሚተላለፉባቸው ሃገራት ጋር ስምምነቶች ተፈራርመዋል።በአውሮጳ ህብረት የሚሻል የተባለው«የስደት አያያዝ ፕሮጀክት» ስር፣ ለምሳሌ የሱዳን ድንበር ጠባቂዎች ድንበራቸው በተሻለ መንገድ መጠበቅ ያስችላቸዋል የተባለ ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል።ታዛቢዎች የአውሮጳ ህብረት የአፍሪቃ መንግሥታትን በድንበር ጠባቂነት ቀጥረዋቸዋል ሲሉ ይተቻሉ። ይህ ግን ውጤት አስገኝቷል።አሁን ወደ አውሮጳ ህብረት የሚመጡ ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል።በጎርጎሮሳዊው 2018 በአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት የጥገኝነት ማመልከቻ ያስገቡ ኤርትራውያን ቁጥር 14,910 ነበር። በ2016 ግን 33,370 ነበሩ።ይህም ከእጥፍ በላይ ነው።በአንጻሩ ግን አሁን  ከኤርትራ የሚሰደዱት ቁጥር ከቀድሞ ጋር ሲነጻጸር አልቀነሰም።ከ2018 ቁጥራቸው ወደ 200 ሺህ የሚጠጋ ኤርትራውያን ኡጋንዳ ገብተዋል።አብዛኛዎቹ እንደ 23 ዓመቱ ኤርትራዊ  በሰዎች አሻጋሪ ደላሎች አማካይነት ከኬንያ በአውቶብስ ነው ኡጋንዳ የገቡት።ደላሎቹ ለዚህ ተግባር ከእያንዳንዱ ስደተኛ 1500 ዶላር ይወስዳሉ።ዘካሪያስ ገሪማ እንደሚሉት አዲሱ መንገድ ከኡንጋዳ ይቀጥላል።የሀገራቸው ሰዎች በዓለም ዙሪያ የሚያካሂዱትን የስደት እንቅስቃሴ የሚከታተሉት ኤርትራዊው ዘካርያስ ከብዙዎቹ ጋር በዋትስአፕ እና በፌስቡክ ይገናኛሉ።እናም አሁን እንደደረሱበት የስደት መስመሮቹ ጉዞ በሜዴትራንያን ባህር በጀልባ መሆኑ ቀርቶ፣ የዓለምን እኩሌታ ያህል በሚጓዙበት በአውሮፕላን ተቀይሯል።አብዛኛዎቹ አሁን ወደ ሰሜን አሜሪካ መሄድ ነው የሚፈልጉት ይላሉ ዘካርያስ።
« ኤርትራውያን ስደተኞች አሁን ወደ ሰሜን አሜሪካ እያቀኑ ነው።ከአፍሪቃ አውሮፕላን ጣቢያዎች ወደ ደቡብ አሜሪካ ይበራሉ።ከዛም ወደ ማዕከላዊ አሜሪካ ይሄዳሉ።ተቆጣጣሪዎች እንዳይዟቸው በአብዛኛው በእግር ነው የሚጓዙት።ጉዞው አንድ ሁለት ወይም 6 ወራት አለያም አንዳንዴ ዓመትም ሊወስድ ይችላል።» 
ይህ ጉዞ ውድ መሆኑን ዘካርያስ ያውቃሉ።ከዚህ ቀደም ሱዳን እና ሊቢያ የነበሩ ደላሎች አሁን ኡጋንዳ ተደላድለዋል።እዚያ በተስፋፋው ሙስና ከኢሚግሬሽን ባለሥጣናት በቀላሉ ፓስፖርት ያገኛሉ።በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ኤርትራውያን የሰዎች አሻጋሪዎች መረቦች አማካይነት ደቡብ አሜሪካ ሃገራት ለመግባት አስፈላጊ የሆነውን ቪዛ በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ።ጉዞው እስከ 30 ሺህ ዶላር ይፈጃል። ይህ ለሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎቹ ጥሩ የገቢ ምንጭ ነው። ገንዘቡም በድብቅ ኡጋንዳ በሚገኙ ሬስቶራንቶች ሆቴሎች እና ሱፐር ማርኬቶች ሥራ ይውላል።ሞሰስ ቢኖጋ በኡጋንዳ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት፣ ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ማሻገርን እና የሰዎችን ንግድ ለማስቀረት የሚሰራው ክፍል ባልደረባ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ሕገ ወጡ ተግባር ይፈጸማል ተብሎ ይጠረጠራል።ግን ትክክለኛ መረጃ የላቸውም። 
 «አንዳንዶቹ እንደሚሄዱ እና ሃገራችንም ሰዎች ወደ ሌሎች ሃገራት በሚሸጋገሩባት መተላለፊያነት ይጠቀሙባታል ብለን እንጠረጥራለን።ሆኖም ትክክለኛ መረጃ የለንም።»
የአውሮጳ ህብረት የስደት መርህ ዓላማ በመሰረቱ በአፍሪቃ ያለውን የሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች መረብ መበጣጠስ ነበር።ይሁን እና ይህ መርህ ዘካርያስ እንደሚሉት ሕገ ወጦቹን የሰዎች አሻጋሪዎች ይበልጥ ብልጥ አድርጓቸዋል ።
«የአውሮጳ ህብረት ሕገ ወጥ ደላሎችን ለመከላከል ከሱዳን እና የደረሰበት ስምምነት አልሰራም። ይልቁንም እነሱን ይበልጥ ብልጥ አድርጓቸዋል። አሁን የጉዞ መስመሩ በተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎች ያልፋል።በርካታ ቪዛ ማግኘት ችለዋል። እነርሱን መቆጣጠሩም ቀላል አይሆንም።»

ምስል DW/M. Belloni
ምስል DW/J. Jeffreys
ምስል DW/S. Schlindwein

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW