1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀመንበር

ሰኞ፣ ጥር 24 2002

በማላዊ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን የያዙት ፕሬዚደንት ቢንጉ ዋ ሙትሀሪካ ትናንት በአዲስ አበባ በተከፈተው የህብረቱ የመሪዎች ጉባዔ ላይ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀ መንበርነትን ስልጣን ተረከቡ።

ፕሬዚደንት ቢንጉ ዋ ሙትሀሪካምስል AP
የሊቢያውን መሪ ሞአመር ጋዳፊን የተኩት ፕሬዚደንት ሙትሀሪካ በዚሁ ወቅት ባሰሙት ንግግር የአፍሪቃ መንግስታት አህጉሩን ለማሻሻል ይቻል ዘንድ አህጉሩ በታደለው ግዙፍ የተፈጥሮ ሀብት በትክክለኛ መንገድ እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል። በያመቱ በዙር ለተለያዩት የአፍሪቃ አካባቢዎች የሚደርሰውን የአፍሪቃ ህብረትን የሊቀ መንበርነት ስልጣን የሚይዘው አፍሪቃዊ መሪ ይህ ነው የሚባል ግልጽ የፖለቲካ ስልጣን ባይኖረውም፡ ህብረቱ በሚወስዳቸው ውሳኔ ላይ የፖለቲካ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላል። በዚህም መሰረት ሙትሀሪካ የሊቀመንበርነቱን ስልጣን በተረከቡበት ጊዜ አፍሪቃ ራስዋን ማሻሻል የምትችልበት ጊዜ አሁን መሆኑን በመጠቆም፡አፍሪቃውያን መሪዎች ለአህጉሩ መሻሻል ከፍተኛ ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በህንድ የዴሊ ዩኒቨርሲቲ በምጣኔ ሀብት ትምህርት የተመረቁት አዲሱ የአፍሪቃ ህብረት ሊቀ መንበር ሙትሀሪካ የማላዊ ፕሬዚደንት ቢንጉ ዋ ሙትሀሪካ ወደሀገራቸው በመመለስ እአአ እስከ 1978 ዓም ድረስ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ካገለገሉ በኋላ የቀድሞው እና ራሳቸውን የማላዊ የዕድሜ ልክ መሪ ብለው የሾሙት የፕሬዚደንት ሄስቲንግ ካሙዙባንዳ ፖለቲካ በመቃወም በተመድ ውስጥ የአፍሪቃ የንግድና የልማት ፊናንስ ክፍል ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ሰርተዋል። ፕሬዚደንት ካሙዙባንዳ ባረፈባቸው ግፊት በሀገራቸው የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን እአአ በ 1993 ዓም ባስተዋወቁበት ጊዜ የቀድሞው ፕሬዚደንት ባኪሊ ሙሉዚ እስከዚያን ጊዜ ድረስ በሶስት አሰርተ ዓመት የካሙዙባንዳ አምባገነን አገዛዝ አንጻር በህቡዕ ይንቀሳቀስ የነበረውን የተባበረው ዴሞክራቲክ ግንባር ፓርቲ አቋቋሙ፤ ሙትሀሪካም የዚሁ ከአንድ ዓመት በኋላ ፡ እአአ በ 1994 ዓም በሀገሪቱ በተካሄደው የመድብለ ፓርቲ ምርጫ ያሸነፈው ፓርቲ ደጋፊ ሆኑ። ይሁንና፡ ሙሉዚ የተከተሉትን ኤኮኖሚ ፖሊሲ በመቃወም ሙትሀሪካ የራሳቸውን የተባበረውን ፓርቲ መሰረቱ። ሆኖም፡ እአአ በ1999 ዓም በተከሄደው ምርጫ የሙሉዚን ፓርቲ ማሸነፍ ባለመቻላቸው እና ሙሉዚም የማዕከላዩ ባንክ ተጠባባቂ መሪ አድርገው በሾሙዋቸው ጊዜ ፓርቲያቸውን አፍርሰው የሙሉዚን ፓርቲ እንደገና ተቀላቀሉ። እአአ በ 2002 ዓም የኤኮኖሚ አቅድ እና የልማት ሚንስትርነትን ስልጥን ያዙ፤ እአአ በ 2004 ዓም የቀድሞው ፕሬዚደንት ባኪሊ ሙሉዚ ህገ መንግስቱን በመለወጥ የስልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው በቀረበት ጊዜ ነበር ሙትሀሪካን እንዲተኩዋቸው አጩዋቸው። ሙትሀሪካ በዚያን ዚዜ በተካሄደው የአውሮጳ ህብረት እና የኮመንዌልዝ ታዛቢዎች የማጭበርበር ተግባር ታይቶበታል ባሉት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሀገር መሪነቱን ስልጣን ይዘዋል ይሁንና፡ ከቀድሞው ፕሬዚደንት ባኪሊ ሙሉቲ ጋር ግንኙነት እየተበላሸ በመሄዱ፡ ሙትሀሪካ ከተበበረው ዴሞክራቲክ ግንባር በመለያየት እአአ በ 2005 ዓም ዴሞክራሲያዊውን ፕሮግረሲቭ ፓርቲን አቋቋሙ። ከዚያም የመንግስቱ ዓቃብያነ ህግ የቀድሞው ፕሬዚደንት ሙሉዚ ለጋሽ ሀገሮች ለድሀይቱ ሀገር ማላዊ የሰጡትን አስራ ሁለት ሚልዮን ዶላር ለግል ጥቅም አውለዋል በሚል ክስ መስርተውባቸዋል። የሰባ ስድስት ዓመቱ የሚቀርበው አገላለጽ እንደተናጋሪው ግለሰብ ይለያያል። አንዳንዶች ሙትሀሪካን በተጨባጭ ሂደት የሚያምኑ ምሁር ወይም ጸረ ሙስና ታጋይ ሲሉዋቸው፡ ሌሎች ግን ለፕሬዚደንታዊው ምርጫ በዕጩነት ባጩዋቸው የቀድሞውን የማላዊ ፕሬዚደንት ባኪሊ ሙሉዚን አንጻር ፊታቸውን በማዞራቸው እንደ ከሀዲ እና ከተለመደው የፖለቲካ አሰራር ወጣ ያለ ሂደት የሚከተሉ አድርገው ያዩዋቸዋል። አርያም ተክሌ/ነጋሽ መሀመድ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW