አዲሱ የኮሮና ፈዋሽ መድሃኒት ተስፋና ስጋት
ሐሙስ፣ ኅዳር 23 2014ሁለት ዓመታትን ሊያስቆጥር ጥቂት ቀናት የቀሩት የኮሮና ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ ከመከላከያ ክትባት ውጭ የረባ ፈዋሽ መድሃኒት አልተገኘለትም።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሙከራ ላይ የሚገኘው ሞሎፒራቪር የተሰኘ መድሃኒት ተስፋ ማሳደሩን ተመራማሮዎች እየተገለፀ ነው።ሜርክ በተባለው የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የተሰራው ይህ መድሃኒት የኮሮና ተዋህሲ የሚያደርሰውን ጉዳትና ህመም በግማሽ ይቀንሳል ተብሏል። ከብራውን ዩንቨርሲቲ የህክምና ባለሙያ የሆኑት ሜጋን ራኒ ለመድሃኒቱ አድናቆት አላቸው።
"ሰዎች ከፍተኛ ተጋላጭነት ሲኖራቸው እና በኮቪድ-19 ሲያዙ ቤት ውስጥ ሊወስዱት የሚችሉት ክኒን ነው። እናም ያ ለውጥ ማምጣት የሚችል ነው። ይህ እስካሁን ከህክምና መሳሪያ ሳጥኖቻችን ውስጥ ከጎደሉብን አስፈላጊ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው።»
በትናንትናው ዕለት የመከሩት የአሜሪካ የጤና አማካሪዎች ቡድንም አዲሱ የኮቪድ-19 ክኒን ስራ ላይ እንዲውል ድጋፍ ሰጥቷል። በዚህ ሁኔታ መድሃኒቱ ከተፈቀደ፣ አሜሪካውያን በቤት ውስጥ ሊጠቀሙበት ለሚችሉት የኮቪድ-19 የመጀመሪያ ህክምና ይሆናል ተብሏል።
በብሪታንያ የሪዲንግ ዩንቨርሲቲ የስነ-ህይወት ባለሙያ የሆኑት ሲሞን ክለርክ በበኩላቸው ተዋህሲው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የመድሃኒቱ መገኘት አስደሳች ነው ይላሉ።
«በጣም የሚያስደስት ህክምና ነው። ለህክምና ባለሙያዎችም ከፍተኛ ጉዳት ሳያስከትል የተዋህሲውን ስርጭት ለመግታት የሚያስችል አስደደናቂ እና አስደሳች የህክምና ዘዴ ነው ። ስለዚህ ተጨማሪ ከፀረ-ባክቴሪያ መድሃኒቶች ጋር ሲነፃፀር ብዙ የፀረ- ተዋህሲ መድሃኒቶች የሉንም። የፀረ-ባክቴሪያ መድሃኒቶችም በእርግጥ ለተዋህሲ ማከሚያ አይሆኑም። ስለዚህ ይህ በጣም አስደሳች በጣም አስገራሚ ነው».
መድሃኒቱ አስቀድሞ በብሪታንያ ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፤ በዩኤስ አሜሪካ ግን እስካሁን የተፈቀደው ብቸኛው የኮቪድ-19 ሕክምና በደም ሥር የሚሰጥ ነው። ይህ መድሃኒት በዋጋ ደረጃም ቢሆን በጣም ውድ በመሆኑ ብዙዎች የሚጠቀሙበት አይደለም።ስለሆነም በአሜሪካ የመድሃኒት አስተዳደር ሞልኖፒራቪር ከፀደቀ ለኮቪድ-19 ህሙማን በእንክብል መልክ የሚሰጥ የመጀመሪያው መድሃኒት ይሆናል ተብሏል።
እንደ ባለሙያዎቹ መድሃኒቱ በኮቪድ-19 ሳቢያ የሚመጣ ሞትንና ሆስፒታል ገብቶ መታከምን በግማሽ ይቀንሳል ተብሏል።ይህም ክትባቱን ላላገኙ ለፅኑ ህሙማን አዲስ ተስፋ የሚፈነጥቅ ነው።የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ የጤና አማካሪው አንቶኒ እስቴፋን ፋውች ግን የመድሃኒቱ መገኘት መልካም ቢሆንም ስርጭቱን ለመከላከል ግን ዋነኛ መፍትሄ አይደለም ባይ ናቸው።
«በዚህ መድሃኒት ደስተኛ ነን። እና ብሩህ ተስፋም አድሮብናል። ምንም እንኳን ይህ መድሃኒት በአሁኑ ስዓት ለአደጋ ጊዜ አገልግሎት እንዲውል ፍቃድ እየጠየቅን ቢሆንም፤ በመጀመሪያ ደረጃ ስርጭቱን ለመከላከል ምትክ መሆን የለበትም።ለዚህም ነው ክትባት የምንሰጠው።»
በሌላ በኩል መድሃኒቱ ተዋህሲውን የዘረ መል በማነቃቃት አደገኛ ወደ ሆነ ባህሪ እንዲቀየር ሊያደርገው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።ከዚህ በተጨማሪ መድሃኒቱ በነፍሰጡር ሴቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው ተመራማሪዎቹ አሳስበዋል። በመሆኑም የአሜሪካው የመድሃኒት አስተዳደር መድሃኒቱ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ተጨማሪ ጥናቶችን እና ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሐመድ