አዲሱ የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) ምን ይዞ መጣ ?
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 14 2015
ዛሬ ቅዳሜ ምሥረታውን ያካሄደው አዲሱ የፖለቲካ ፓርቲ የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ዎሕነን) የተሰኘ መጠሪያን የያዘ ነው ፡፡ ንቅናቄው የተመሠረተው በተለያዩ ብሄር ተኮር እና አገርአቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በአመራርነት እና በአባልነት ሲሳተፉ በቆዩ ሰዎች አሰተባባሪነት አንደሆነ በፓርቲው የምሥረታ ጉባዔ ላይ ተገልጿል፡፡ ንቅናቄው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባገኘው ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ መሠረት ላለፉት ሦስት ወራት ለምሥረታ የሚያበቃውን ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን የንቅናቄው አመራሮች ለDW ተናግረዋል ፡፡
የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ በዋናነት ይዞ የቀረበው መታገያ ምንድ ነው በሚል ? በዶቼ ቬለ DW የተጠየቁት ከንቅናቄው ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ አቶ አማኑኤል በላቸው “ የንቅናቄው አጀንዳ በዋናነት የዎላይታ ህዝብ በኢትዮጵያ በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች መብቱ ተከብሮለት እንዲኖር ማስቻል ነው ፡፡በተጨማሪም ንቅናቄው በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምንና ለዚህም የሚሠራ ይሆናል ፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን የብሄር ብሔረሰቦች መብት እንዲከበር ይታገላል “ ብለዋል ፡፡ ከዎላይታ ዞን የክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ አዲሱ የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ ያለውን አቋም አስመልክቶም ሕዝቡ የራስ በራስ አስተዳደር ለመመሥረት ያነሳው ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እስኪያገኝ ንቅናቄው አበክሮ እንደሚሠራ አቶ አማኑኤል ተናግረዋል ፡፡
የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ የሚለው ሥያሜ ብሄር ተኮር ሆኖ ሳለ በአገራዊ ፓርቲነት መመዘገቡ እርስ በእርሱ አይቃረንም ወይ ? ከዎላይታ ውጪ በሚገኙ የአገሪቱ አካባቢዎች አባላትን ለማፍራትስ አያስቸግራችሁም ወይ ? በሚል አሁንም በዶቼ ቬለ የተጠየቁት አቶ አማኑኤል “ የዎላይታ ህዝብ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተሠራጭቶ እየኖረ የሚገኝ ህዝብ ነው ፡፡ በሁሉም ክልሎች የዎላይታ ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች ደጋፊ አባላትን ለማፍራት በአገራዊ ፓርቲ ብንደራጅ ይሻላል የሚል እምነት ይዘን ነው ወደ ተግባር የገባነው ፡፡ ይህ ከስያሜው ጋር ይጋጫል ብለን አናስብም ፡፡ ምክንያቱም በቀጣይ ተቀራራቢ ዓላማ ካላቸው አገራዊ ፓርቲዎች ጋር ጭምር በአጋርነት መሥራት የእቅዳችን አንዱ አካል ሆኖ ሥለሚገኝ ነው “ ብለዋል ፡፡
የዎላይታ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ በዛሬው መሥራች ጉባዔው የንቅናቄውን ሊቀመንበር እና ምክትል ሊቀመንበርን ጨምሮ 15 የሥራ አስፈጻሚ እና 45 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን ሰይሟል ፡፡ ከደቡብ ክልል ከሚገኙ ዞኖች አንዱ የሆነው የዎላይታ ዞን ከፍተኛ የፖለቲካ ፉክክሮች የሚይታበት አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ በዞኑ ከገዢው የብልፅግና ፓርቲ በተጨማሪ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ዎብን እና የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ዎህዴግ የተባሉ ዋንኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ ፡፡
ሽዋንግዛው ወጋዮሁ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር