1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የጀርመን መራኄ መንግስሥት ኦላፍ ሾልዝ ማናቸው?

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 12 2014

ሽንፈትን ሳያማርሩ በጸጋ መቀበል ፣ከወደቁበት በመነሳት በጽናት ያለጥርጥር ወደፊት መራመድ ኦላፍ ሾልዝ የሚከተሉት መርህ ነው። ይህን መመሪያቸው ያደረጉት ሾልዝ በቅርቡ እንደተናገሩት እጩ መራኄ መንግሥት ለመሆን የወሰኑት ከአራት የፓርቲያቸው ነባር አባላት ጋር ካካሄዱት ሚስጥራዊ ስብሰባ በኋላ ነበር።

Deutschland | Schloss Bellevue - Ernennungsurkunde Scholz
ምስል Emmanuele Contini/Getty Images

መራኄ መንግሥት ኦላፍ ሾልዝ ማናቸው?

This browser does not support the audio element.

ሶሻል ዴሞክራቱ ኦላፍ ሾልዝ 16 ዓመታት ጀርመንን የመሩትን የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አንጋፋ ፖለቲከኛ አንጌላ ሜርክልን ተክተው ሶስት ፓርቲዎች የተጣመሩበትን መንግሥት መምራት ከጀመሩ እነሆ ሁለት ሳምንት ሆናቸው። ባለፈው ህዳር 29 ቀን 2014 ዓም ፤በጎርጎሮሳዊው ታኅሳስ 8 2021 ዓም ነበር የጀርመንን ከፍተኛ ስልጣን የያዙት ኦላፍ ሾልዝ ዘጠነኛው የፌደራል ጀርመን መራኄ መንግሥት ናቸው። ከእስካሁኖቹ የጀርመን ጥምር መንግሥታት በዓይነቱ የሚለየው አዲሱ መንግሥት ያለፈው ምርጫ አሸናፊ ሶሻል ዴሞክራት ፓርቲንና በምርጫው የተሻለ ድምጽ ያገኙትን፤ የአረንጓዴዎቹንና ፓርቲና ነጻ ዴሞክራቶች ፓርቲን ያጣመረ ነው።ብዙም ልታይ ልታይ የማይሉት ሾልዝ ብዙም ሳይጠበቅ ነበር በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2020 ዓም የፓርቲው እጩ መራኄ መንግሥት ሆነው የተመረጡት። እስከ 2019 ዓም ድረስ ሾልዝ የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።ይህ ምናልባትም ፓርቲው የተለየ የግራ ክንፍ መሪ በመፈለጉ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በሆዳቸው የሚይዙትና ስራ ላይ ብቻ የሚያተኩሩት ሾልዝ የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ አመራሮችና አባላትን ድጋፍ ማግኘት ባለመቻላቸው ነው ተብሎ ይታመናል። 
ይሁንና ኦላፍ ሾልዝ በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትርነትን ከምክትል መራኄ መንግስትነት ጋር ደርበው መያዛቸው ፖለቲካዊ ብቁነታቸውን አግዝፎ በ2020 ለእጩ

ምስል Michael Sohn/AP Photo/picture alliance

መራኄ መንግሥትነት አበቃቸው። ያኔ የመሀል ቀኝ አቋም ካላቸው ከእህትማማቾቹ  ከክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲና ከክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ ጀርመንን ሲመራ የነበረው የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ በህዝብ አስተያየት መመዘኛዎች የነበረው የህዝብ ድጋፍ ዝቅተኛ  ነበር።ሾልዝ ያኔ የማሸነፍ ፍላጎት እንዳላቸው እና የወደፊቱም የጀርመን መራኄ መንግሥት እንደሚሆኑ ሲናገሩ ብዙዎች ማመን አቅቷቸው ነበር። ለወራት ሲቀለድባቸውም ነበር።ይሁንና ሾልዝ  ሁሉን ቻል አድርገው ሳያማርሩ የምርጫ ዘመቻቸውን ያካሄዱበት መንገድ መራኄ መንግሥትነት ሆነው ለመመረጥ የረዳቸው የስኬታቸው መሰረት ተደርጎ ተወስዷል። ሽንፈትን ሳያማርሩ በጸጋ መቀበል፤  ከዚያም ከወደቁበት በመነሳት በጽናት ያለጥርጥር ወደፊት መራመድ የዶቼቬለዋ ዛቢነ ኪንካርትዝ እንደዘገበችው ኦላፍ ሾልዝ የሚከተሉት መርህ ነው። ይህን መመሪያቸው ያደረጉት ሾልዝ  በቅርቡ እንደተናገሩት እጩ መራኄ መንሥት ለመሆን የወሰኑት ከአራት የፓርቲያቸው ነባር አባላት  ጋር  ካካሄዱት ሚስጥራዊ ስብሰባ በኋላ ነበር።
«አመሰግናለሁ ሳሲካ ፣ኖርቤርት አመሰግናለሁ፣ ላርስ አመሰግናለሁ፣ ሮልፍ አመሰግናለሁ ።ከዊሊ ብራንት ሀውስ ብዙም በማይርቅ ስፍራ በሚገኝ በአንድ ጥሩ ምግብ ቤት ተቀምጠን ማንም እዚያ መሆናችንን ሳያውቅ እጩ መራኄ መንግሥት ለመሆን ወሰንኩ።ማናችንም ለእረፍት ሄድን ብለን አልተናገርንም።ማንም አላወቀም፤ከዚያም በኋላ ውሳኔ ላይ ተደረሰ።ይህ የኛ ስራ ውጤት ነበር። አመሰግናችኋለሁ።«
ሾልዝ እንዳሉት ፓርቲያቸው የመስከረሙን ምርጫ ያሸነፈው በአንድ በመተሳሰሩ ነው።
«እንደ ፓርቲ አንድ ላይ ነን።እርስ በርሳችን ተያይዘናል። ውድ ጓዲትና ጓዶች እንድናሳካው እንፈልጋለን ብለን ነበር።የፌደራል ጀርመን ምርጫን አሸንፈናል።»

ምስል Gladstone/Wikipedia

በጎርጎሮሳዊው ሰኔ 14 1958 ዓም የዛሬ 63 ዓመት ኒደርዛክሰን በተባለው የጀርመን ፌደራዊ ክፍለ ግዛት ውስጥ በምትገኘው  ኦስናብሩክ በተባለችው የምዕራብ ጀርመን ከተማ ነው የተወለዱት። ወላጆቻቸው የኢንዱስትሪ ሰራተኞች ነበሩ። ሾልዝ ያደጉት ደግሞ በሌላዋ የጀርመን ፌደራዊ ግዛት በወደብ ከተማዋ በሀምቡርግ ነው።  ከፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ቤተሰብ የተወለዱት ሾልዝ ክርስትናም የተነሱ ቢሆንም ሲያድጉ ከእመነቱ ገሸሽ ብለው አሁን የየትኛውም ሃያማኖት ተከታይ አይደሉም። የዛሬ ሁለት ሳምንት የመራኄ መንግሥትነቱን ስልጣን የተረከቡበት የቃለ መሃላ ስነ ስርዓት ማሰረጊያ የሆነውን «እግዚአብሔር ይርዳኝ» የሚለውን ቃል አልፈውታል። 
ይሁንና ለሀገራቸው የክርስትና ቅርስም ሆነ ባህል ያላቸውን አድናቆት ከመግለጽ አይቆጠቡም። በሐምቡርግ ከተማ የሕግ ትምህርት አጥነተው በተለይ ከስራና ቅጥር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በጥብቅና ሰርተዋል።የሶሻል ዴሞክራት ፓርቲ አባል የሆኑት ገና የ17 ዓመት ወጣት ሳሉ በ1970ዎቹ ነበር። ከጎርጎሮሳዊው 1998 እስከ 2011 ዓመተ ምህረት የጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ነበሩ።በ2001 ዓም በሀምቡርግ ግዛት መንግሥት ውስጥ እንዲሁም 2002  የፓርቲያቸው የኤስ ፔ ዴ ዋና ፀሀፊ ሆነው ከያኔው ሶሻል ዴሞክራቱ መራሄ መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር ጋርም ሰርተዋል።ፓርቲያቸው ከእህትማማቾቹ ፓርቲዎች ከክርስቲያን ዴሞክራትና ከክርስቲያን ሶሻል ኅብረት ፓርቲዎች ጋር ተጣምሮ በመሰረተው የመጀመሪያው የሜርክል የስልጣን ዘመን በ2007 የስራና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።ከ2009ኙ ምርጫ በኋላ ኤስ ፔ ዴ  ከጥምሩ መንግሥት ሲወጣ ሾልዝ ወዳደጉባት ሐምቡርግ ተመልሰው የከተማዋ የፓርቲው ምክትል ሃላፊ ሆኑ። 2011 ላይ በተካሄደው የሀምቡርግ ግዛት ምርጫ ፓርቲያቸው አሸንፎ ሾልዝ የከተማዋ ከንቲባ ሆኑ።በዚሁ ሃላፊነትም እስከ ጎርጎሮሳዊው 2018 ድረስ አገልግለዋል።ሾልዝ በዚህ ሃላፊነት ረዥም ጊዜ የቆዩ የመጀመሪያው ከንቲባም ሆነዋል። ሾልዝ ፓርቲያቸው ኤስ ፔዴ እንደገና ከሜርክል ጋር በተጣመረበት በአራተኛ የሜርክል መንግሥት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትርና ምክትል መራኄ መንግሥት ነበሩ።የሾልዝ የፖለቲካ ህይወት ውጣ ውረዶች አልተለዩትም። ሁሉንም ግን በራስ መተማመናቸው እንደተወጧቸው ነው የሚነገርላቸው። የፖለቲካው ማማ ላይ ለመድረስ ትጋታቸውና ጥንካሬያቸው ረድቷቸዋል። ሾልዝ በወጣትነት ዘመናቸው ያራምዱት የነበረውን አስተሳሰብም በሂደት ቀይረዋል።በ1980 ዎቹ የኤስ ፔ ዴ የወጣቶች ድርጅት ምክትል ሊቀመንበር በነበሩበት ጊዜ የካፒታሊስት ኤኮኖሚ እንዲሸነፍ ነበር ፍላጎታቸው።በዚህም አክራሪ ሶሻሊስት ይባሉ ነበር።ይሁንና በአንድ የሐምቡርግ የህግ ተቋም ውስጥ በተለይ በሰለጠኑበት የስራ ሕግ ልዩ ጠበቃ ሆነው ሲሰሩ የንግድ እና የግል ድርጅቶች ስራ እንዴት እንደሚካሄድና ጥቅማቸውንም ይበልጥ ካወቁ በኋላ ግን አስተሳሰባቸውን ለወጡ።

ምስል imago images

ሾልዝ በኤኮኖሚ ፖሊሲ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም መስኮች ባከናወኗቸው ተግባራትና ባገኙት ውጤት ስማቸው ይነሳል።ከመካከላቸው በ2001 ዓም የሐምቡርግ የአገር አስተደር ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የአደንዛዝ እጽ አዘዋዋሪዎችን ለመዋጋት ፖሊስ ማስረጃ ለመያዝ የሚያስችለውን እርምጃ እንዲወስድ መፍቀዳቸው አንዱ ነው። የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ዋና ጸሀፊ በነበሩበት ጊዜ ያያኔው መራኄ መንግሥት የጌርሃርድ ሽሮደር አጀንዳ 2010 የሚባለው «የተሻሻለው ስራና የቅጥር ደንብ» ወደፊት እንዲራመድ አግዘዋል ።በወቅቱ በርካታ የኤስፔዴ አባላት የደንቡ ተቃዋሚዎች ነበሩ። 
ኦላፍ ሾልዝ ብዙውን ጊዜ በንግግራቸው ስሜታቸውን አያንጸባርቁም። ሲናገሩም ቁጥብ ናቸው።። የሚያውቋቸውና አብረዋቸው የሰሩ እንደሚናገሩት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲናገሩ ሰምተው አያውቁም። ሲናደዱም ጮክ ብለው ሲናገሩ አልሰሟቸውም። ሲበሳጩም እግራቸውን ወዲያና ወዲህ ያደርጋሉ። ጆሮአቸው ይቀላል ይላሉ።ይህ በመስከረም በቴሌቪዥን በተካሄደው የምርጫ ዘመቻ ክርክር ላይ በክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ተፎካካሪያቸው አለአግባብ በተጠቁበት ወቅት ታይቷል።  ኦላፍ ሾልዝ ከጎርጎሮሳዊው 2007 ዓም አንስቶ በተከታታይ በመንግስታዊ ሃላፊነቶች ሰርተዋል። እናም እነዚህ ሃላፊነቶች ለመራኄ መንግሥትነት ብቁ የሚያደርጓቸውተደርገው ይወሰዳሉ። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በኮቪድ ምክንያት ስራ ያቆሙ ኩባንያዎችን በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ በመመደብ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በውጭ ፖሊሲያቸውም የቀደመው መንግሥት የጀመረውን በመቀጠል ያምናሉ።በቅርቡ እንደተናገሩት መንግሥታቸው እንደ ሜርክል መንግሥት ሁሉ አውሮጳን የማጠናከር እቅድ ይዟል።

ምስል John Thys/Pool Photo via AP/picture alliance / ASSOCIATED PRESS

«አውሮጳን ጠንካራና ሉዓላዊ ለማድረግ መጣር አለብን ። በኔ አመለካከት ይህ እኛ ጀርመኖች ልናከናወነው የሚገባ ቁልፍ ተግባር ነው።  በመሀል አውሮጳ የሚገኝ ትልቅ ሀገር አለን ። ብዙ ህዝብና ትልቅ የኤኮኖሚ ኃይል ያለንም ነን።ለዚህም ነው አውሮጳ በአንድ ድምጽ ብዙ መናገር እንደምትችል ለማረጋገጥ የምንፈልገው።የዓለም ህዝብ ቁጥር በቅርቡ 10 ቢሊዮን ይደርሳል።ቻይና ዩናይትድ ስቴትስና ሩስያ ብቻ ሳይሆኑ ከእስያ ሌሎች በርካታ ሀገራት ብቅ እያሉ ነው። ከመካከላቸው ኮሪያ ጃፓን ኢንዶኔዥያ ማሌዥያ ህንድ ይጠቀሳሉ።ለዚህም ነው አስፈላጊ የሆኑ ጥቂት መርሆችን መሰየም የሚያስፈልገው።አንደኛው ጠንካራ የአውሮጳ ኅብረት ነው።ምክንያቱም ያ ካልሆነ ሚናችንን መጫወት አንችልም። ይህ ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር መተባበርን ያካትታል ፤በተለይም እንደአሁኑ ዓይነት ወሳኝ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ።አርግጥ ነው ይህ የኔቶን ትብብርም ይጨምራል» 
በኤኮኖሚው መስክም ጀርመን የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን ተጽእኖ መቋቋም ትቻለለች ሲሉ ደጋግመው ተናግረዋል። ጀርመን እስከ 2022 መጨረሻ 450 ቢሊዮን ዩሮ አዲስ ብድር ትወስዳለች።ሾልዝ  የሚያድገው የጀርመን ኤኮኖሚ ብድሯን እንድትቋቋም ያደርጋል ሲሉ በምርጫ ዘመቻቸው ቃል ገብተዋል።ሾልዝ የጎርጎሮሳዊው 2008 ን የገንዘብ ቀውስ የተወጣችው ጀርመን ይህም አያቅታትም ትወጣዋለች ነው የሚሉት።ሆኖም የኮሮና ወረርሽኝ አሁን ተጠናክሮ መስፋፋት ማሳሰቡ አልቀረም ።ከዚህ ሌላ ሶስት የተለያየ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች የተጣመሩበትን መንግሥታቸውን ማስተዳደርም ሌላው ፈተና ሳይሆንባቸው እንደማይቀር ይገመታል።

ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW