አዲሱ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ፖሊሲ በሩሲያ - ዩክሬን ጦርነት ላይ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 10 2017
አራት ዓመት የዘለቀውን የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት በተመረጡ ማግስት እንድሚያስቆሙ በቁጭት ሲናገሩ የነበሩት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥጣን ከመጡ ስድስት ወራት በኋላ ለዩክሬን የመሣርያ እርዳታ እንደሚሰጡ፤ በሩሲያ ላይም ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ ባለፈው ሰኞ አስታውቀዋል። ፕሬዝዳንቱ በዚህ መግለጫቸውና ውሳኔያቸው እንደ ቀድሞው ፕሬዝዳንትት ጆ ባይደን አሜርካንን በጸረ ሩሲያ አቋም ከዩክሬን ጋር ከተሰለፉት አውሮፓውያኑ ጋር መቀላቀላቸውና ክሩሲያው ፕረዝዳንት ቪላድሚር ፑቲን ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸው ስለመሆን አለመሆኑ ግን በአሁኑ ወቅት በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል ነው የሚገለጸው። ሆኖም ግን ሰኞ ዕለት በኋይት ሀውስ ከኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ ጋር በሰጡት መግለጫ፤ የአየር መቃወሚያዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የጦር መሣራያዎችን በኔቶ በኩል ለዩክሬን እንደሚልኩ አረጋግጠዋል። «የጦር መሣሪያዎችን በገፍ ለኔቶ እናቀርባለን፤ ኔቶ በበኩሉ መሣሪያዎቹን ለዩክሬን እንዲደርስ ያደርጋል፤ ወጭውንም ሙሉ በሙሉ ይሸፍናል» በማለት የጦር መሣሪያዎቹ የሚቀርቡት በሽያጭ መሆኑንም አስታውቀዋል።
አሜሪካ የጦር መሣሪያዎቹን የምታቀርበው በሽያጭ ስለመሆኑ
የኔቶ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተም አሜሪካ የጦር መሣሪያዎቹን የምታቀርበው በሽያጭ መሆኑ ተገቢና በኔቶ ጉባኤ በተደረሰው ስምምነት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል። «ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችላትን አቅም እንድትገነባ እንፈልጋለን። ወጭውን አውሮፓ መሸፈኑ ትክከልኛና ተገቢም ነው ነው» በማለት አባል አገሮች መሣሪያዎቹን በመግዛት ለዩክሬን ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በውሳኔው ላይ የሚቀርቡ ትችቶችና አስተያየቶች
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡበት የአሜሪካ ትቅደምና በሌሎች አገሮች ጦርነቶች ጣልቃ ያለ መግባት ፖሊሲ አንጻር ለዩክሬን በተዘዋዋሪም ቢሆን የጦር መሣሪያ ለመርዳት ያሳለፉት ወሳኔና ሩሲያንና አጋሮቿንም በማዕቀብ ለመቅጣት መዛታቸው በአውሮፓውያኑ ዘንድ ትልቅ የፖሊሲ ለውጥ ተደርጎ ተወስዷል። የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ጦርነቱን ለማስቆምና አሜሪካንን በሌሎች ጦርነቶች ላለመዝፈቅ የገቡትን ቃል የሚጥስ ነው የሚሉ የፕሬዝዳንቱ ደጋፊዎች ያሉትን ያህል፤ በኔቶ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሚስተር ማት ዊትከርን የመሳሰሉት ደግሞ እርዳታው በነጻ የሚሰጥ ሳይሆን በሽያጭ የሚቀርብና ንግድም በመሆኑ የአሜሪካንን የመሣሪያ እንዱስትሪ የሚያነቃቃና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚያስገኝ፤ የፕሬዘደንቱ ትክክለኛ የአሜሪካ ትቅደም የውጭ ፖሊሲ መገለጫ ነው በማለት ይከራከራሉ።
አሜሪካ ከሽያጭ በተጨማሪ ወጭ እንድትጋራ ስለመጠየቋ
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ንግድ እንጂ የውጭ መጋራት ያለበት አይደለም በማለት ቅሬታ ያላቸው የአውሮፓ አገሮች ድምጽም መሰማት ይዟል። የሕብረቱ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ ወይዘሮ ካያ ካላስ እራሳቸው የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ጥሩ ቢሆንም ከአሜሪካ የሚጠበቀው ግን ከዚህ በላይ መሆኑን ነው የጠቆሙት «ፕሬዝዳንት ትሩምፕ ለዩክሬን የጦር መሣሪያዎችን ለመላክ ማስታወቃቸውን በደስታ ተቀብለነዋል፤ ሆኖም ግን አሜሪካ በሺያጭ ሳይሆን የጦርነቱን ወጭ እንድትጋራን ነው የምንፈልገው» በማለት አሜሪካ በዩክሬን ጉዳይ ከዚህም በላይ ልትሳተፍ እንደምትችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዝ ፈረንሳይና ጣሊያን ከአሜሪካ መሣሪያ እየገዙ ለዩክሬን በማቅረቡ ፕሮግራም ተሳታፊ እንደማይሆኑ ማስታወቃቸው ተስምቷል ።
የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ አሜሪካንን ወደጦርነቱ ለማስገባት የሚደረገው ጥረት አካል ስለመሆኑ
ይህ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ፤ ዩኪሬን ከሩሲያ ጋር እያካሄደችው ባለው ጦርነት አሜሪካ ከጎኗ የቆመች ያህል እንዲሰማት ያደረገ ሲሆን፤ በሩሲያ በኩል ግን ውሳኔው በጦርነቱ ምንም አይነት ለውጥ እንደማያመጣ ነው የሚነገረው። የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስርጌይ ላቭሮቭ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ውሳኔ ኔቶና አውሮፓ አሜሪካንን ጎትተው ወደ ጦርነቱ ለማስገባት የሚያደረጉት ጥረት አካል መሆኑን ገልጸው፤ በሩሲያና የንግድ አጋሮቿ ላይ ማዕቀብ የሚጣልበት ቀነ ገደብ መቀመጡ የተለመደ እንደሆነና የንግድ አጋሮቻቸው ግን በዛቻና ማስፈራራያ አቋማቸውን ይለውጣሉ ተብሎ እንደማይታሰብ አስታውቀዋል።
ገበያው ንጉሤ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ