አዲስ ሕገ መንግሥት ያጸደቀችው ቱኒዝያ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 21 2014
የዓረቡ የጸደይ አብዮት ወይም ዓረብ ስፕሪንግ እየተባለ የሚታወቀው ህዝባዊ እንቅስቅሴ መነሻነት የምትጠቀሰው ቱኒዝያ፤ ባለፈው ሰኞ ባካሄደችው ህዝበ ውሳኔ፤ አዲስና ለፕሬዝዳንቱ የበለጠ ስልጣን የሚሰጥ ህገመንግስት አጽድቃለች። እ እ እ በ2010 እና 11 ዓም አምባገነነዊ አስተዳደሮችን በመቃወምና ለውጥ በመሻት በቱኒዚያ፤ ግብጽ፤ ባህሬን፤ ሊቢያ፣ የመንና ሶሪያ በመሳሰሉት ያረብ አገሮች የተካሄዱት ህዝብዊ እንቅስቅሴዎች፤ ለበርካታ አመታት በስልጣን ላይ የነበሩ ገዥዎችን በመገዳደርና ከስልጣን በማስወገድ ይጠቀሳሉ። ይሁንና ከቱኒዚያ በስተቀር ብዙዎቹ የዚያን ግዜው አብዮት የተካሂደባቸው የአረብ አገሮች፤ አንድም እንደ ግብጽ ሌላ አምባ ገነናዊ አስተዳደር ተከለዋል፤ ዓሊያም እንደ ሊቢያ የመንና ሶሪያ ጭራሽ ፈርሰዋል ወይም በማያቁርጥ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቀዋል።
ቱኒዝያ ግን የዴሞክራሲና ፕሬስ ነጻነት የተረጋገጡባትና የመድብለ ፓርቲ ስራት የተመሰረተባት በአጠቃላይም የጸደዩ የአረብ አብዮት የተስካባት አገር በመሆን ስትጠቀስ ነው የቆየችው። ይሁንና ለውጡን ተከትሎ የመጡት መንግስታት የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ፤ ፖለቲከኖቹ በሽኩቻና ሙስና ጭምር ተዘፍቀዋል በማለት በርካቶች ቅሬታና ተቃውሞችን ሲያሰሙ ነው የሚደመጡት።
እ እ እ 2019 ዓም በፕሬዝዳንትነት የተመረጡት የቀድሞው የህግ ፕሮፈሰር ሚስተር ካይስ ሰይድ፤ ከሚሰማው ህዝባዊ ተቃውሞና ምናልባትም ከመንግስት አቅም ማነስ በመነሳት፤ ባለፈው አመት ፓርላማውን በትነው ስልጣኑን ከተቆጣጠሩ በኋላ፤ የመንግስት መዋቅርንና አሰራርን የሚቀይር ነው ያሉትን አዲስ ህገመንግስት ለህዝበ ውሳኔ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ሳይድ ፓርላማውን የበተኑበትን፤ አዲስ ህገመንግስት እንዲረቀቅና ህዝበውሳኔ እዲካሄድ ያዘዙብትን አግባብ፤ የቱኒዝያ ፖለቲከኞች አምርረው ነው የተቃወሙት። ድርጊቱ አምባገነናዊነትና ምናልባትም ቱኒዚያ ወደ ቀድሞው ስራት እንድትመለስ የሚያደርግና ከመፈንቅለ መንግስት ድርጊት ጋር የሚመሳሰል ነው በማለት ፕሬዝዳንቱን ከሰዋቸዋል፤ ህዝቡም በህዝበ ውሳኔው እዳይካፈል ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ሁኒታና ውዝግብ መሀል ባለፈው ሰኞ የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ግን ፤ ለምርጫ ከወጣው ህዝብ የ92 ከመቶውን ድጋፍ እንዳገኘ ተገልጿል። ለህዝበ ውሳኔው ድምጹን ለመስጠት የወጣው ህዝብ ግን አንስተኛ እንደሆነ ነው የሚታወቀው። በቱኒዚያ የምርጫ አስፈጽሚ እንደተገለጸው ከሆነ፤30 ከመቶ ው መራጭ ህዝብ ብቻ ነው ድምጹን የሰጠው። ያም ሆኖ፤ ውጤቱ እንደተገለጸ፤ የፕሬዝድንቱ ደጋፊዎች በሌሊት አደባባይ በመውጣት ደስታ ድጋፋቸውን ገልጸዋል፤ “ በጠላቶቹ ላይ ድልን እንዲቀዳጅ እመኝለታለሁ: አላህ ከጠላቶቹ ይጠብቀው፤ እንኳን ደስ አለህ ስይድ” ሲሉ የተሰሙት እናት በሌሊት ወተው ድስታቸውን ክገለጹት የሚጠቀሱ ናቸው።፡ፕሬዝዳንት ሳይድም ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር በህገ መንግስቱ መጽደቅ ቱኒዚያ ወደ አዲስ ምእራፍ የገባች መሆኑን አስታውቀዋል።
ተቃዋሚዎቹ በበኩላቸው የህዝበ ውሳኔው ሂደትም ሆነ ዉጤቱ ኢ-ህገመንግስታዊና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት ተቃውሟቸውን አጠንክረው ቀጥለዋል ። በአቡዳቢ ዩንቨርስቲ ፕሮፊሰር የሆኑት ዶክተር ሞኒካ ማርክስም ህዝበ ውሳኔው የቱኒዚያ ዴሞክራሲ ለግዜውም ቢሆን የተቀበረ መሆኑን የሚያመላክት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
ይህ የህገ መንስት ለውጥ ቱኒዚያን ወዴት ሊወስዳት እንደሚችል ለጊዜው በግልጽ አይታወቅም። የቻታሃም ሀውስ የአፍርካ ዳይሬክተር ሚስተር አሌክስ ቪንስ እንደሚሉት ግን የቱኒዚያ ሁኒታ አሁንም አሳስቢ ነው። “አሁን በቱኒዚያ ባለው ሁኒታ አሳሳቢው ጉዳይ ከዚህ ቀደም በሌሎች አገሮች ህዝበ ውሳኔን ተቃውመው የነበሩ ፓርቲዎች እንደ መፈንቅለ መንግስት የመሳሰሉ አማራጮችን ያዩበትን ሁኔታ የሚያስታውስ ነው። ባለፈው አመት በጊኒ የሆነው ይህ ነው። የተክሄደውን ህዝበ ውሳኔ የተቃወሙ ሀይሎች ሳያሳክላቸው ሲቀር፤ ወታደሩ ጣልቃ እንዲገባና መፈንቅለ መንግስት እንዲያካሂድ ነው ያበረታቱት በማለት የቱኒዚያ ጉዳይም አሳስቢ ሊሆን እንደሚችል አስታውቀዋል።
ገበያው ንጉሤ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ