የአፍሪቃ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ
ቅዳሜ፣ ጥር 29 2013የአፍሪቃ ሕብረት መሪዎች ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ ውይይታቸውን ዛሬ በኢንተርኔት ማካሄድ ጀምረዋል። መሪዎቹ አህጉሪቱን በሚመለከቱ የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ጉዳዮች እና በወረርሽኙ ምክንያት ችላ የተባሉ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በዋናነት እንደሚወያዩ ተገልጿል። የዘንድሮው የመሪዎች ጉባኤ የተጀመረው ግብፅ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታው በአፍሪቃ መገኘቱ ከተረጋገጠ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ መሆኑ ነው። ወረርሽኙ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትል ይሆናል በሚል ተሰግቶ የነበረ ቢሆንም ከሌሎች የዓለም ክፍሎች ጋር ሲነፃፀር በሽታውን ጥሩ በሚባል ደረጃ አፍሪቃ መቋቋሟ ተገልጿል። የአፍሪቃ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) እንደሚለው በዓለም ላይ በተህዋሲው ከተያዙት 3,5 በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው ከአፍሪቃ። በበሽታው ወይም በከሽታው ጋር በተያያዘ ሕይወታቸው ካለፉትም ቢሆን በአፍሪቃ የተመዘገበው አራት በመቶ ነው። እንዲያም ሆኖ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት የኮቪድ 19 ክትባት የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ላይ ይገኛሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ላለፈው አንድ ዓመት የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር ሆነው ያገለገሉት የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዝደንት ስሪል ራማፎዛን በመተካት የዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቺሴ ኬዴ በይፋ ሥራቸውን ለመጀመር ተሰይመዋል። ራማፎዛም ዛሬ ከወንበራቸው በመነሳት ሥልጣኑንን አስረክበዋል።
« የሕብረታችንን ባንዲራ ለፕሬዚዳንት ቺሴ ኬዴ እያስረከብኩ ህብረታችንን ለመምራት ለሚወስዱት ኃላፊነት መልካሙን ሁሉ እመኝላቸዋለሁ።»
ከዚህም ሌላ የአፍሪቃ ሕብረት አባል ሃገራቱ በ34ተኛ ጉባኤያቸው የቀድሞው የቻድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሳ ፋኪ ማህማትን ዳግም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር አድርገው መርጠዋል።
ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሠ