1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲስ የተቋቋመው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን ያስነሳው ቅሬታ

ዓርብ፣ ነሐሴ 5 2015

በኦሮሚያ ክልል የተቋቋመው የምሥራቅ ቦረና ዞን ከቀሰቀሰው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ገበያ መቆሙን ቢሮዎችም ዝግ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የወረዳ አመራሮችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምሥራቅ ቦረና ከጉጂ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን አጣምሮ የተቋቋመ ነው

INFOGRAFIK Äthiopien: Konfliktreiche Grenzregion EN
የኢትዮጵያ ካርታ

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና በሚል ከጉጂ፣ ቦረና እና ባሌ ዞኖች የተወሰኑ ወረዳዎችን ቆርሶ የተመሰረተው አዲስ ዞን አሁንም የህዝብ ቅሬታ መነሻ መሆኑን አላቋረጠም። በተለይም በጉጂ ዞን ስር ይተዳደር የነበረውና አሁን ላይ ምስራቅ ቦረና ስር እንዲተዳደር በአዲሱ መዋቅር የተወሰነበት ጎሮ ዶላ ወረዳ ከፍተኛ የህዝብ ተቃውሞ እንደቀጠለበት ነዋሪዎች እየገለጹ ነው።እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት የገበያ ስፍራዎችን መዝጋትን ጨምሮ ሂደቱን የተቃወሙት ላይ ይፈጸማል ያሉት እስራት መቀጠሉንም አመልክተዋል፡፡ ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዝርዝሩን ልኮልናል።

በእድሜያቸው ገፋ ያሉ መሆኑን ገልጸው ግን ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ  ጠይቀውን አስተያየታቸውን የሰጡን የጎሮ ዶላ ሀርቀሎ ከተማ ነዋሪ በአዲሱ መዋቅር ስር አመራሮች የሚመደቡት የህዝብ ይሁኝታ የተሰጣቸው ሳይሆን ባለስልጣናት የሚያስቀምጡአቸው ብቻ ሆነዋል ሲሉ ቅሬታቸውን ይጀምራሉ፡፡ “ሰው ፍላጎት ያላሳየባቸው ደግሞም ያልመረጣቸው ነው በግድ እንዲመሩን እየተቀመጡ ያሉት፡፡ የወረዳው ህዝብ የሚወዳቸው ድምጽም የሆኑን ግን እያንዳንዳቸው ወደ እስር ቤት ተለቅመዋል፡፡ በዚህ መልክ በግድ ሊያስተዳድሩን ሲሰሩ ህዝቡ ግን እምቢ እያለ በርካታ ሰው ከተማውን ለቀው እየወጣ ነው፡፡ ወታደር ይዘው ሊያስገድዱን ቢሰሩም ሰው የሚወዳቸው አመራሮች አንድም የለም በዚህ አሁን፡፡”

የፀጥታ ስጋት ሆኖ የቀጠለው የጉጂ እና ምሥራቅ ቦረና ዞን መዋቅር

እስራት በወረዳው ቀጥሏል ያሉን ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ እስካሁን የዞኑን መዋቅር ተቃውመው የታሰሩት ሰዎች ቁጥር ከ120 እንደሚበልጥም አንስተውልናል፡፡ “ከአዲስ ዞን አወቃቀር ጋር ተያይዞ ጎሮዶላ ወረዳ ላይ የተለየ ችግር ነው የተስተዋለው፡፡ እስካሁን 120 ሰዎች ታስረዋል፡፡ ከነዚያ ውስጥ የተፈቱ አሉ፡፡ ግን ደግሞ በፍርድ ቤት ነጻ ተብለውም ያልተለቀቁ አሉ፡፡ የወረዳው አስተዳዳሪን ጨምሮ 14 ሰዎች ከነዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ኅብረተሰቡ የገበያ አድማ አድርጓል፡፡ ከተቃውሞው የተነሳ እንቅስቃሴ የለም፡፡”

ሌሎች የወረዳው ነዋሪዎችም በሰጡን አስተያየት ችግሩ እየተባባሰ እንጂ የመቃለል አዝማሚያን አላሳየም፡፡ “አሁን በቀደም አንድ መኪና ተቃጥሏል፡፡ የተሰባበረም ነበር፡፡ ይህ ችግር ከተከሰተ በኋላ የተቃጠለው መኪና 5ኛው መሆኑ ነው፡፡ ከሰሞኑ የህዝብ ውይይትም ተደርጎ ምንም እልባት አላመጣም፡፡ እንዳውም እስራቱ ተጠናክሮ ነው የቀጠለው፡፡ ሰው ይህንኑ እየሸሸ ነው፡፡”

የምሥራቅ ቦረና ዞን ጉዳይ በጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቶ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ሲሰጥበት የዞን መዋቅር ውሳኔው የማይቀለበስ ነው የሚል ምላሽ ተሰጥቷልምስል Seyoum Getu/DW

ቅሬታ አቅራቢው ማህበረሰብ መፍትሄ ላለውም እልባት ይጣራል፡፡ “ችግሩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከ20 ጊዜ በላይ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽመናግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ባለስልጣናት አዲሱን መዋቅር ተቃውመው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ መልስ ግን የለም” ሲሉ ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

“መፍትሄው ወደ ነበርንበት መዋቅር መልሰውን በምንወዳቸው እንድንተዳደር መፍቀድ ነው፡፡ በዲሞክራሲ እንጂ በመግፋት በግድ ማስተዳደሩ መፍትሄ ነው ብለን አናምንም” ያሉን ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ናቸው። 

የፀጥታ ስጋት የፈጠረው ግጭት በጉጂ ዞን

ሰሞኑን በምስራቅ ቦረና በጎርፍ ምክንያት ከ18 ሺህ በላይ አባወራዎች ተፈናቅለው ከ30 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት በጎርፍ ማለቃቸውን ባወጣው ሪፖርት ያመለከተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ (UNOCHA) በጉጂና ምስራቅ ቦራና አዋሳኝ ላይ ያለው የጸጥታ ሁኔታ ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ማድረጉን ማሳወቁም ይታወሳል፡፡

ስለነዋሩዎቹ ቅሬታ ከአከባቢው ባለስልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በተለይም የወረዳው አዲስ አስተዳዳሪ አቶ ጌቱ ጩሉቄ እና ለምስራቅ ቦረና ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጁራ ኦዳ በተደጋጋሚ ደውለን የጽሁፍ መልእክትም ብንልክላቸውም ምላሻቸውን ባለማኘታችን አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ ከሳምንታት በፊት ጉዳዩ በጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባኤ ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቶ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ምላሽ ሲሰጥበት የዞን መዋቅር ውሳኔው የማይቀለበስ ነው የሚል ምላሽ መሰጠቱ ይታወሳል።

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW