አዲሷ የሶማልያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር
ሰኞ፣ ጥቅምት 26 2005 ወይዘሮ ፎዚያ ዩሱፍ ሃጂ ትናንት አስሩ የሶማሊያ መንግስት የካቢኔ አባላት ሲመረጡ ነበር ለጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣን መሾማቸው የታወቀው። በሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ ከምገኘው ራስ ገዙ የሶማሊ ላንድ ግዛት ነበር አዲሷ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የመጡት። ወይዘሮ ፎዚያ ለረዥም ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር ኖረዋል። በሶማሊያ ታሪክ ሴት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣን ስትይዝ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ወይዘሮ ፎዚያ በሶማሊያ ለውጭ ጠቅላይ ሚኒስትረነት ከመታጨታቸው በፊት በሶማሊ ላንድ ለፕረዚደንትነት ተወዳድረው ነበር። ሆኖም ግን የሶማሊ ላንድ የምርጫ ቦርድ ለቦታው ብቁ አይደሉም በማለት ከውድድሩ ሰርዟቸዋል። በዚህ ምክንያት ነበር ወይዘሮ ፎዚያ ፊታቸውን ወደ ሶማሊያ የመለሱት።
በቅርቡ የተሾሙት አዲሱ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲ ፋራህ ሺርዶን ወይዘሮ ፎዚያን ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የመረጡት በሶማሊ ላንድ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ነው ይላል ነዋሪነቱ ሞቃዲሾ የሆነው ጋዜጠኛ መሐመድ ሺኔ፣
«ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሶማሊያ ታሪክ ሴት ተሿሚን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ላይ በማስቀመጥ የሶማሊ ላንድ ህዝብ ልብ ውስጥ ሰርጾ ለመግባት እየሞከሩ ነው።»
ወይዘሮ ፎዚያ ለፕረዚደንትነት እንዳይወዳደሩ የከለከሉ የሶማሊ ላንድ ሹማምንቶች በሹመቱ ዜና አልተደሰቱም። ምክንያቱም እነሱ ብቁ አይደሉም ያሏቸው ወይዘሮ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲመረጡ ማየት አይፈልጉምና። ሆኖም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ፣ የሶማሊ ላንድ ሹማምንቶች እንደሚሉት ብቃት አያንሳቸውም ይላል ጋዜጠኛው መሐመድ፤
«ወይዘሮ ፎዚያ ኃላፊነታቸውን ተገቢና ብቁ በሆነ መልኩ መወጣት ይችላሉ፣ ምክንያቱም የተማሩ ናቸው። ከብዙ የሲቪል ማህበራትና ሰብዓዊ ድርጅቶች ጋር ሰርተዋል። በዛ ላይ ጋዜጠኛና የአንድ ቴሌቢዥን ጣቢያ ባለቤትም ናቸው።»
እአአ በ1991 የሲያድ ባሬ አገዛዝ ከወደቀ በኋላ የሶማሊ ላንድ ግዛት ሹማምንቶች ግዛቱ ከሌላው የሶማሊያ ክልል ተለይቶ ነጻ ወጥቷል በማለት ማወጃቸው ይታወሳል። ሆኖም ለሶማሊ ላንድ እስካሁን እውቅና የሰጠ አንድም ሀገር የለም። የአዲሷ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዱና ዋነኛ ተግባር ይህ የሶማሊ ላንድ ጉዳይ ነው ይላሉ የአፍሪቃ ቀንድ የፖሊቲካ ተንታኟ ላውራ ሃሞንድ፣
«ተቀዳሚ ተግባራቸው ሆኖ የሚታየኝ ሶማሊያ ከሶማሊ ላንድ ጋር ሊታደርግ ከምትችል ስምምነትና ለሶማሊ ላንድ እውቅናን ከመስጠት አንጻር የሚያደርጉት ጥረት ነው። ያ በጣም ጠቃሚ ነው። በሌላ በኩል ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ማለትም ከብሪታኒያ፣ ከዩናይትድ ስቴትስና ከአውሮፓ ህብረት እንዲሁም ከሌሎች በሶማሊያ ፖሊቲካ ከሚሳተፉ ሀገራት ጋር በሚደረገው ድርድር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ብዙ የውጭ ጉዳይ ሥራዎችም ይጠብቋቸዋል።
ትናንት በተደረገው የሶማሊያ መንግስት የካቢኔ ሹመት ከወይዘሮ ፎዚያ ሌላ ሌሎች ዘጠኝ ካቢኔዎች ሹመት አግኝተዋል። ከዚህ በፊት የነበረው 15 የሚኒስቴር ቦታዎች አሁን ወደ 10 ዝቅ ብለዋል። የሚኒስቴሮቹ ቁጥር መቀነስ ምን ችግር ሊያመጣ ይችላል ለሚለው ጥያቄ መሐመድ ሺኔ መልስ ሲሰጥ፤
«ብዙ የሶማሊያ ህብረተሰብ ክፍሎች በዚህ ካቢኔ ውስጥ በትክክል ስለመወከላቸው እርግጠኞች አይደሉም። ይህ ሌላ ችግር ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን ጠቅላይ ምኒስትሩና ፕሬዚዳንቱ ቃል እንደገቡት ለነኚህ የህብረተሰብ ተወካዮች የተለያዩ ስልጣን በመስጠት ጥያቄያቸውን የሚመልሱ ይመስለኛል- ለምሳሌ የአምባሳደርነትና ሌሎች ተቀራራቢ የሥልጣን ቦታዎችን በመስጠት።»
የአስሩ የሶማሊያ መንግስት ካቢኔ አባላት ሹመት በቅርቡ ለሶማሊያ ፓርላማ ቀርቦ እንደሚጸድቅ ይጠበቃል።
ገመቹ በቀለ
ተክሌ የኋላ