ትምህርትአፍሪቃ
አዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በቅርቡ ሊያስመርቅ ነው
ረቡዕ፣ ኅዳር 23 2013ማስታወቂያ
በቅርቡ የተመራቂ ተማሪዎችን ቅበላ ከፈጸሙ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የኾነው አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ተማሪዎችን ለማስመረቅ መዘጋጀቱን ዐስታወቀ። በትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት ለአንድ ወር ተቋርጦ የነበረው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ጥሪም ዳግም ተጀምሯል። ግጭቱ ባለፈዉ ጥቅምት 24 ከመከሰቱ አስቀድመው የተመራቂ ተማሪዎችን ቅበላ ከፈጸሙ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ነዉ። ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አራት ሳምንታት የመማር ማስተማር ሂደቱን ቀጥሎ ታኅሣስ 10 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. የምረቃ ስነ ስርዓት አከናውናለሁ ብሏል። የሃሮማያ እና የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎች በበኩላቸው ነገሮች አሁን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ ተመልሰዋል ተብሎ በመታመኑ ለተመራቂ ተማሪዎች ዳግም ጥሪ አድርገናል ብለዋል፡፡ ከትግራይ ክልል እና ከአጎራባች አከባቢዎች የሚመጡ ተማሪዎችን በተመለከተ ግን በተለየ ሁኔታ የሚስተናገዱ ይሆናል ነው የተባለው። የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የመማር-ማስተማሩ መርሐ ግብር በጎሳ ግጭትና በኮቪድ 19 ስርጭት ምክንያት ባለፉት ዓመታት ሲደነቃቀፍ ነበር።
ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ