አዶዬ - የጅማ ፍቅር - ከጠይብ አባፎጊ ጋር
ሐሙስ፣ ሐምሌ 3 2017
አዶዬ - የጅማ ፍቅር - ከጠይብ አባፎጊ ጋር
አቶ ጠይብ አባፎጊ ይባላሉ፤ ከወራቶች በፊት በአፋን ኦሮሞ ለአንባቢያን ያቀረቡት እና «አዶዬ» በሚል የጅማ ማኅበረሰብ ባህል እና የአኗኗር ዘይቤን ያሳዩበት የልብ ወለድ መጽሐፋቸዉ ታዋቂነትን አስገኝቶላቸዋል። በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት አቶ ጠይብ አባፎጊ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለረጅም ዓመታት በባህልና ቱሪዝም፤ ባህልን በማስተዋቅ ዘርፍ እንደሰሩ አጫዉተዉናል። ባለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ የፓርላማ አባል ነበሩ። ነዋሪነቴ አሁን አዲስ አበባ ዙርያ በምትገኘዉ በሸገር ከተማ ነዉ ያሉን አቶ ጠይብ አባፎጊ፤ አዶዬ የተባለዉ መጽሐፋቸዉ ስላደጉባት የጅማ ገጠር መንደር፤ «ጅማ ዞን መና ወረዳ፤ደጋ ቀበሌ» ማኅበረሰቡ ከልጅነት እስከ እዉቀት የሚያልፍባቸዉን ባህላዊ እና ማኅበረሰባዊ መስተጋብሮች በልብ ወለድ መልክ ጽፈዉ በመጽሐፍ ማቅረባቸዉን አጫዉተዉናል።
ደራሲ ጠይብ አባፎጊ እንደነገሩን ህጻናት ምሽት ላይ እሳት ዳር ሆነዉ፤ ቀን ቀን ከብት ጥበቃ ላይ ህጻናት በአካባቢዉ ባህል መሰረት የሚጫወትዋቸዉን፤ በአጠቃላይ ቤተሰቦች ልጆቻቸዉ አካባቢያቸዉን እንዲረዱ የሚያደርጉባቸዉን ዘዴዎችን ጨምሮ ማህበረሰቡ ከህጻንነት እስከ አዋቂነት ያለዉን መስተጋብር በመጻሕፋቸዉ ከትበዋል። አቶ ጠይብ በጅማ ህቡ የሚጠቀምባቸዉን ስነቃሎችንም ጽፈዋል።
ደራሲ ጠይብ አባፎጊ በትዉልድ መንደራቸዉ ያለዉን የሰርግ ባህል ሥነ-ስርዓት ጠቅሰዋል። ጅማ በእጅ ጥበብ ከሚታወቁባቸዉ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጠይብ አባፎጊ ጅማ በተለይ በእንጨት ቁሳቁስ ስራ፤ የታወቀ፤ አካፋ የተሰራዉም በጅማ መሆኑን ጥንታዊ ታሪኩን ተናግረዋል።
በጅማ ቡናን ለመጠጣት ብቻ ሳይሆን ለመድሃኒትነት ፤ በባህላዊ ሥነ-ስርአት እና ክንዉኖች ላይ ጥቅም ላይ እንደሚዉል ተናግረዋል። አካባቢዉ ለቡና ያለዉ ክብር ለየት ያለ መሆኑንም አቶ ጠይብ አክለዋል።
የጠይብ አባፎጊ በጅማ ባህላዊ መስተጋብር ላይ ያተኮረዉ መጽሐፋቸዉን በአማርኛ ለመተርጎም እያሰቡ ናቸዉ። ዘመኑ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የአጭር መረጃ መለዋወጫ በመሆኑ፤ መጽሐፍ አንባቢያን መቀነሱ አሳሳቢ ነዉ ሲሉ የተናገሩት አቶ ጠይብ የማንበብ ባህላችን ሊበረታታ ይገባል ሲሉም በአንክሮ ተናግረዋል።
አቶ ጠይብ አባፎጊ መጽሐፋቸዉን « አዶዬ» ሲሉ ነዉ የሰየሙት። አዶዩ ማለት ደግሞ የማይቋረጥ እህትማማችነት መሆኑን አጫዉተዉናል። ደራሲ ጠይብ አባፎጊን ለሰጡን ቃለ-ምልልስ በዶቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን ዝግጅት እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ