1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አነጋጋሪዉ የዋልድባ መነኮሳት ጉዳይ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2 2010

በሽብር ወንጀል ተከሰዉ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚገኙት ሁለት የዋልድባ መነኮሳት «ተፈተዋል«በሚል  በማህበራዊ ድህረ ገፆች ሲነገር ቆይቷል። ይሁን እንጅ መነኮሳቱ አሁንም ድረስ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት መሆናቸዉን ቅርበት ያላቸዉ ሰወች ይገልፃሉ።

Äthiopien Kality Gefängnis
ምስል DW/Y. G. Egziabher

Walidiba Monks are Sill in Prison. - MP3-Stereo

This browser does not support the audio element.



የኢትዮጵያ መንግስት ለተሻለ  ሀገራዊ መግባባት ሲባል በምህረትና በይቅርታ እስረኞችን እንደሚለቅ ካስታወቀ ወዲህ ይፈታሉ ተብሎ ከተጠበቁ ታሳሪወች መካከል በሽብር ወንጀል ተከሰዉ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኙት አባ ወ/ሰላሴና  አባ ገ/ኢየሱስ የተባሉት  ሁለቱ  የዋልድባ መነኮሳት  ይገኙበታል።  በዚህ የምህረት አዋጅ መሰረት መንግስት የተወሰኑ ታሳሪዎችን  መልቀቅ ከጀመረ ወዲህም እነዚህ መነኮሳት እንዲፈቱ በማህበራዊ ድህረ-ገጾች ዘመቻ ተካሂዶ ነበር።ምንም እንኳ መነኮሳቱ አሁንም ድረስ ማረሚያ ቤት ቢሆኑም  ያለፈዉ ዓርብ ጀምሮ «ተፈተዋል» የሚለዉን መረጃ ብዙወች በማህበራዊ ድህረ ገፆች  ተቀባብለዉታል። የመነኮሳቱን ጉዳይ በቅርብ እንደሚከታተል የገለጸልን ጋዜጠኛ ጌታቸዉ ሽፈራዉ «ተፈተዋል» የሚለዉን ወሬ ከሰማ በኋላ ጉዳዩን አረጋግጦ አለመፈታታቸዉን ከ ሶስት ጊዜ በላይ በግል ገፁ መጻፉን ይናገራል።
«ይህ ዜና ከተሰማበት ጀምሮ ሀሙስ ዕለት ሶስት ዜና ሰርቻለሁ ፤እንዳልተፈቱ።ከዚያ በኋላ እሁድ የጠየቃቸዉ ሰዉ ነበረ።ለኔ ለጌታቸዉ ብለዉ መልክት ልከዉልኝ ነበር እንዳልተፈቱ። እንዲያዉም ይሄ ዜና በተሰራበት ወቅት እነሱ ስግደት ላይ ነበሩ።ማንም ያናገራቸዉ ሰዉ የለም።የእነሱ የመፈታት ዜና እንዲያዉ ለማወናበድ ይመስለኛል።»
እነዚህ መነኮሳት የሀይማኖት አባቶች መሆናቸዉና  ወቅቱም  የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ በዓልን የሚያከብሩበት መሆኑ  «ተፈተዋል» ለሚለዉ ወሬ አንዱ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ጋዜጠኛ ጌታቸዉ  ያብራራል። 
«አሁን የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓል ነዉ ።ፋሲካ ነዉ።በዚህ ወቅት ምናልባት መነኮሳቱ ይፈታሉ ከሚል ተስፋ ይመስለኛል።አ።ብዛኛዉ ይህን ዜና የሰሩት ሰዎች  ሰዉ መነኮሳቱ ተፈተዋል ብሎ ተስፋ እንዲያደርግ ይመስለኛል።መነኮሳቱ ተፈተዋል ብሎ ሰዉን ለማረጋጋት የሚፈልግ አካል ይመስለኛል፤ከመንግስት ዉጭ በኔ ግምት ማለት ነዉ።ምክንያቱም መነኮሳት ናቸዉ ዋልድባ ነዉ የሚሄዱት እና የተባለዉን ሰዉ ተስፋ እንዲያደርግ የተፈለገ ይመስለኛል።»
መነኮሳቱ በተከሰሱበት መዝገብ ዉስጥ ከሚገኙ 35 ተከሳሾች  33ቱ መፈታታቸዉን የሚናገረዉ ጋዜጠኛ ጌታቸዉ  የእነዚህ ሁለት የሀይማኖት አባቶች እስካሁን ከዕስር አለመለቀቅ ግን ከህግ ጠበቃ ባሻገር የሚከራከርላቸዉ ተቋም ባለለመኖሩ የተነሳ ነዉ  የሚል እምነት አለዉ።
«አራተኛና አምስተኛ ተከሳሾች ናቸዉ።አንደኛና ሁለተኛ ተከሳሾች ተፈተዋል።ሶስተኛ ተከሳሽም ተፈቷል።ከስድስተኛ ተከሳሽ ዉጭ ያሉት ሁሉም ተፈተዋል።ሁለተኛ ተከሳሽ ብቻ ነዉ የቀረዉ።የእነሱ ጉዳይ ከሌሎች ከተከሰሱ ሰዎች ያነሰ ቢሆን እንጅ እንትን ያለ አይደለም።ያለመፈታታቸዉ ምክንያት የሚመስለኝ መጀመሪያ ተቋም ያስፈልጋል።የተቃዋሚ ፓርቲ ሲታሰር የተቃዋሚ ፓርቲዉ መግለጫ ያወጣል።ጋዜጠኛ ሲታሰር የጋዜጠኛ ተቋማትና ሌሎችም መግለጫ ይወጣሉ።ግፊት ያደርጋሉ።እነኝህ ሰዎች መጀመሪያ ግፊት ሊያደርግላቸዉ ይገባ የነበረዉ በተቋም ደረጃ ሲኖዶስ ነዉ።ሲኖዶሱ ደግሞ ይህን ያህል በግልፅ ስለነዚህ አባቶች መታሰራቸዉን አስመልክቶ እስከአሁን ግፊት ሲያደርግ አልታየም።»
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረዉ  በማረሚያ ቤት ሆነዉ ክሳቸዉን እየተከታተሉ የሚገኙት እነዚህ  መነኮሳት ከዓመት በላይ የታሰሩ ሲሆን በመጭዉ ሚያዚያ 18 ቀንም የፍርድ ቤት  ቀጠሮ እንዳለቸዉ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ድረስም መነኮሳቱ አለመፈታታቸውን ሰምተናል።
ያለፈዉ ጥር መንግስት ካወጣዉ የምህረት አዋጅ ወዲህ በተለያዩ ክልሎች በሺህዎች  የሚቆጠሩ  ሰወች ከዕስር የተለቀቁ ሲሆን ፤አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተሾሙ ወዲህም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ደንብ ተላልፋችኋል ተብለዉ የታሰሩ 19 ሰወች ከአማራ ክልል እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና ፖለቲከኛ አንዷለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች ከአዲስ አበባ ባለፈው ሳምንት ከዕስር መለቀቃቸዉ ይታወቃል። ጉዳዩን በተመለከተ የመነኮሳቱን ጠበቃ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብን ጥረት ብናደርግም ሊሳካልን ባለመቻሉ አስተያየታቸዉን ማካተት አልቻልንም።

ምስል Tigist M./Befekadu Hailu
ምስል DW/Y. G. Egziabher


ፀሐይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW