1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አፍሪቃን ማስተዋወቅ ነው ዓላማችን»: አቤኔዘር ታደሰ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ግንቦት 25 2015

አቤኔዘር ታደሰ የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርት ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው። በስሩ አምስት ወጣት ሰራተኞችን ቀጥሮ እየሰራ የሚገኘው የ25 ዓመቱ ወጣት እንደ ጀማሪ ስራ ፈጣሪ ያለፈበትን መንገድ እና ምርቶቹን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንዴት እንደበቃ አጫውቶናል።

Äthiopien Leder
ምስል Sabawiyan Leather

አቤኔዘር ታደሰ የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርት ኢትዮጵያዊ ወጣት ነው።

This browser does not support the audio element.

ከኢትዮጵያ ውጭ ገበያ ግንባር ቀደም ከሚባሉ ዘርፎች አንዱ የቆዳ ምርት ነው። እንደ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከሆነ ኢትዮጵያ በዋነኛነት ያለቀለት የቆዳ ምርት ወደ ውጭ እየላከች ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመረተው የቆዳ ጫማም እያደገ መጥቷል። ጓንት፣  ቦርሳዎች እና ሌሎች የቆዳ ውጤቶች ከፍተኛ አቅም ያላቸው ምርቶች እንደሆኑ ይገልፃል። 
አቤኔዘር ታደሰ የቆዳ ምርት ዘርፍ ሰፊ የስራ እድል እንደሚፈጥር የተረዳው ከስድስት ዓመታት በፊት ነበር። ይህም የዩንቨርስቲ ተማሪ ሳለ ከጓደኞቹ ጋር አብረው ለመስራት ባደረጉት ጥናት ነው። « ስለዚህ የቆዳ ቢዝነስ ገና እንዳልተነካ ለማየት ችለናል። ከዛ ይህንን ገበያ ከመረጥን በኋላ ምን አይነት አዲስ ነገር ይዘን መምጣት እንችላለን ብለን አሰብን። በወቅቱ አንድ ላይ ነበር የጀመርነው ግን በተለያየ ምክንያት ብዙዎቹ ወደ ውጭ ሀገር ሄዱ ፤እዚህ ያሉትም ሌላ ፊልድ መረጡ። ከዛ እኔ ብቻዬን ቀጠልኩ። » ይህም ላለፉት ስድስት አመታት።

ምስል Sabawiyan Leather

አቤኔዘር  ዛሬ  የ«ሳባውያን ሌዘር» የሚል መለያ ያለው የቆዳ ምርቶች መስራች እና ሥራ አስኪያጅ ነው።  ዩኒቨርስቲ ውስጥ የማርኬቲንግ እና የሶሲዮሎጂ ተማሪ ነበርኩ የሚለው አቤኔዘር « ትምህርቱ ለንግድ ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር እና ስለ ንግድ እንዲያስብ በር ከፋች እንደሆነለት ይናገራል።
ትኩረቱን በቆዳ እና በጨርቅ የተሰሩ የእጅ ቦርሳዎች ላይ ያደረገ ይመስላል። ከ3000 በላይ ተከታዮች ያሉት የቴሌግራም የመገበያያ ገፁ ላይ በብዛት የሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት ጨርቆችን የተጠቀመባቸው የቆዳ ቦርሳዎች ይገኛሉ። « የአፍሪቃ ማንነትን የሚገልፁ ቦርሳዎች ነው የምንሰራው። ስንጀምር እኛ ምን አይነት አዲስ ነገር ይዘን ወደ ገበያ እንመጣለን ስንል የበለጠ አፍሪቃን ማስተዋወቅ ላይ አተኮርን»
ለዚህም «ኬንያ በሄድኩበት ወቅት ያየሁት ረድቶኛል» ይላል። ይህም ኬንያውያን ለውጭ ሀገር ዜጎች  ገበያ ላይ ያቀረቡት ስራ ነው። አቤኔዘርም ወደ ሀገሩ እንደተመለሰ ያየውን ለመተግበር ሞክሯል።
« መጀመሪያ ላይ በእኛ በሀገር ውስጥ ጥለት ነበር የሞከርነው። ግን ብዙ ምላሽ አላገኝበትም። በአፍሪቃ ጨርቅ ስንሞክረው ግን የተሻለ ምላሽ እና ቅበላ አገኘን። ስለዚህ በአፍሪቃ ጨርቆች እየሰራን እንገኛለን።» ይህም አቤኔዘር ስራዎቹ በሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት እንዲተዋወቅለት እድል ከፍቷል። ሁለት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኤምባሲዎች ያዘጋጁት ባዛር ላይ በመገኘት ስራዎቹንም ለማስተዋወቅ ችሏል። የቆዳ ምርቶቹን ወደ አውሮፓ እና ሌሎች ምዕራባዊ ሀገራትም ለመላክ አቤኔዘር እቅድ አለው። ለዚህ ግን የምዕራባውያን ፍላጎትን ማሟላት ይጠበቅበታል። ይህ ብቻ አይደለም። « ለአውሮፓ ገበያ ከቆዳ ብቻ የተሰሩ ምርቶችን ማቅረብ ይኖርብናል። ይህንንም እየሰራን ነው።  ከዚህ ሌላ መንግሥት ኤክስፖርትን ያበረታታል ብለን እናምናለን። የተሻሉ ፖሊሲዎች ቢወጡ ኤክስፖርት የማናደርግበት ምንም አይነት ምክንያት የለም። አሁን ያለው ፖሊሲ ግን ለስታርትአፕ የሚሆን ፖሊሲ አይደለም። ግን ማሻሻያዎች ይኖራሉ ብዬ አምናለሁ።»

ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ዋቢ አድርጎ እንደፃፈው ኢትዮጵያ ባለፈው የጎርጎሮሲያኑ አመት ወደ ውጪ የላከቻቸው ምርቶች በመጨረሻው ሩብ ዓመት  በከፍተኛ ሁኔታ ማለትም ከ 977 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወደ 778 ሚሊዮን ቀንሷል።  ኢትዮጵያም በዋናነት ወደ ውጭ የላከቻቸው ወርቅ እና ቡና ናቸው። እንደ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኢትዮጵያ በዋጋ ተፎካካሪ እና ጥራት ያለው ቆዳ እና ሌጦ የማቅረብ አቅም አላት።በጥራት፣ ውፍረት፣  ጥንካሬ፣  እና  የሌጦው ንፁህ ውስጣዊ ገጽታ በዓለም ዙሪያ ታዋቂነትን አግኝቷል። ኢትዮጵያም እንደ ጎርጎሮሳውያን   በ2020 ዓ.ም 800 ሚሊዮን ዶላር ከቆዳ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አግኝታለች። 
በዘርፉ እንደሚሰራ ኢትዮጵያዊ አቤኔዘር የሀገሩን ከቆዳ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዴት ይገመግመዋል?

ምስል Sabawiyan Leather
ምስል Sabawiyan Leather

« ገና ብዙ እንደሚጠቅብን እና ብዙ መስራት እንደምችል ነው። አንድ ጊዜ ባደረግነው ፍለጋ የደረስንበት ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ከአፍሪቃ አንደኛ ፣ከአለም ደግሞ ሶስተኛ ናት። ግን ይህም ሆኖ ለአለም ኤክስፖርት የምናደርገው የቆዳ ውጤት ትንሽ ነው።  የቆዳ ኢንዱስትሪ እንደሚባለውም የውጭ ምንዛሬ ሊያመጣልን የሚችል ትልቅ ዘርፍ ነው።»
አቤኔዘርስ ባለፉት ሁለት አመታት በንግድ  የተሻለ እና ተስፋ ሰጪ ነገር  ለማየት ችለናል ይላል።» የግል ስኬቱን ሲገመግም። « ለትላልቅ ድርጅቶች ፣ ለኤምባሲ ስራዎቻችንን ማቅረባችን የበለጠ እንድንሰራ ረድቶናል። ስለዚህ ያለፉት ሁለት አመታት ለኛ ስኬታማ አመታት ናቸው። ግን እዛ ላይ የሚያበቃ አይደለም»
«እኔን ጨምሮ ስድስት ሰራተኞች ነን» የሚለው አቤኔዘር እንደ ወጣት የንግድ ባለቤት እና ሥራ አስኪያጅ ያሰማራቸው ሰራተኞች ወጣቶች ናቸው ይላል። « አንድ ስራ እስካላለቀ ድረስ ዕረፍት የሚባል ነገር የለም» የሚለው አቤኔዘር ነገ ላይ የራሳቸው ነገር እንዲኖራቸው እየነገርኳቸው ጠንካራ የስራ ባህል እንዲኖራቸው ላደርግ ችያለሁ።
አቤኔዘር ከነበረው ተሞክሮ ለሌሎች ንግድ ጀማሪዎች የሚያካፍለው ምክር ከትንሽ ነገር መጀመር ካሰቡበት ሊያደርስ እንደሚችል ነው።  « ምክንያቱም ትላልቅ ነገሮች በሙሉ የተነሱት ከትንሽ ነገር ነው። ገና ብዙ ዘርፎች አሉ። ሰዎች የተለያየ ዘርፍ ላይ እየሞከሩ ቢሰሩ ጥሩ ነው።» ይላል« ሳባውያን ሌዘር» የሚል መለያ ያለው የቆዳ ምርቶች መስራች እና ሥራ አስኪያጅ አቤኔዘር ታደሰ።

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW