አፍሪቃውያን ተማሪዎች ለምን ወደ ሩሲያ ዩኒቨርሲቲውች ይሄዳሉ?
ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2018
ሩሲያ በጎርጎሪያኑ 2025፣ ካመለከቱ 40,000 በላይ አፍሪካውያን መካከል ከ5,000 በላይ ተማሪዎችን በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተቀብላለች። እንደ ሩሲያ የባህል እና ዲፕሎማሲ ኤጀንሲ ሮስትሩድኒቼስቶቭ በ2024 ከነበሩት ማመልከቻዎች በእጥፍ ጨምሯል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመልካቾች ከሱዳን፣ ጊኒ፣ ጋና እና ቻድ የመጡ ናቸው። በሩሲያ ቋንቋ ኮርሶች ላይ ባለሥልጣናቱ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል ።
አፍሪካውያን ተማሪዎች ወደ ሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች ለከፍተኛ ትምህርት መመለሳቸው የሚያስገርም አይደለም ሲሉ ታዛቢዎች ይናገራሉ። በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዘመን፣ ክሬምሊን የሶቪየት-ዘመን ግንኙነቶችን ለማደስ እና በመላ አፍሪካ አዲስ ሕብረትን በመመስረት ከምዕራቡ ዓለም ጋር በተፈጠረው ግጭት ዓለም አቀፋዊ ተጽኖዋን ለማሳደግ ጥረት እያደረገች ነው።
በጎርጎሪያኑ 2022 ዩክሬንንከወረረች ወዲህ ፣ ሩሲያ ዓለም አቀፍ መገለልን ለመቃወም ከደቡባዊው የዓለም አቀፍ ክፍል (ግሎባል ሳውዝ) ጋር ያላትን ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከረች ነው።ሩሲያ የትምህርት፣ ሀይል እና ወታደራዊ ትብብርን እንደ መጠቀሚያ መሳሪያዎች አድርጋለች።
በደቡብ አፍሪካ የኩዋዙሉ-ናታል ዩኒቨርሲቲ ኢመርተስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሩሲያዊቷ የታሪክ ምሁር ኢሪና ፊላቶቫ፣ ለDW እንደተናገሩት ነፃ የትምህርት ዕድሉ አጋር ለማግኘት ነው። «የነፃ ትምህርት ዕድል መስጠት አጋር ለማግኘት የሚያስችል በጣም ርካሹ መንገድ ነው። ሩሲያ በአሁኑ ጊዜ አጋሮች ያስፈልጓታል።በተለይ ከጦርነቱ ወዲህ ሩሲያ ፤ራሷን ፀረ-ቅኝ ግዛት ሀገር አድርጋ ምስል ፈጥራለች። አፍሪካውያንም ሀሳቡን ገዝተውታል።»ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በአውሮፓ ህብረት ወይም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚማሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ቁጥር ሩሲያ ውስጥ ከሚማሩት የአፍሪካ ተማሪዎች ያነሰ ነው።በ2013 በተደረገ ጥናት በፈረንሳይ ብቻ ከ92,000 በላይ አፍሪካውያን ተማሪዎች ይማሩ ነበር ተብሏል። .
የባህል አሻራ ማስፋፋት
ሩሲያ በአህጉሪቱ ያላትንየትምህርት እና የባህል አሻራ ለማጠናከር “የሩሲያ ሀውስ” ተብሎ በሚጠራው ፕሮግራምም የባህል እና የትምህርት ማዕከሎቿን በመላው አፍሪካ የማስፋፋት እቅድ እንዳላት አስታውቃለች።የሮሶትሩድኒቼስቶቭ ኃላፊ የፍገኒ ፕሪማኮቭ በጥቅምት ወር በሞስኮ ለተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ ኤክስፖ 2025 እንደተናገሩት ለግብፅ፣ ዛምቢያ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኢትዮጵያ አዳዲስ ማዕከላት ታቅደዋል።
«በአሁኑ ጊዜ የሩስያ ቋንቋ ኮርሶች በብዙ የአፍሪካ ሃገራት እየተሰጡ ነው። በአሁኑ ጊዜ እና እሱን መከታተል ለሩሲያ ስኮላርሺፕ፣ ለዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት፣ የሥራ እድሎች እና ለአዲስ የአኗኗር ዘይቤዎች በር ይከፍታል» ብለዋል።«በአፍሪቃ እያደገ የመጣው የ«ሩስያ ሀውስ» መጨመርም ከቋንቋ ኮርሶች እና በመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው የስኮላርሺፕ ማመልከቻዎች እንዲጨምር አድርጓል።በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ውስጥ ባለሥልጣናት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሩሲያ ቋንቋ ኮርሶችን ለመስጠት አቅደዋል። የሩሲያ ወታደራዊ አማካሪዎች እና የግል ተቋራጮችም የፕሬዚዳንቱ ፋውስቲን-አርቼንጅ ቱአዴራ አቅምም በሩሲያ ወታደራዊ ድጋፍ ላይ የተመሠረተ ነው።
የፕሮፓጋንዳ እና የቅጥር ጉዳዮች
ይሁን እንጂ ተቺዎች እንደሚሉት የሩስያ ሀውስስ በውጭ አገር የክሬምሊን ትርክት የሚያራምዱ ስውር የፕሮፓጋንዳዎች መሳሪያ ሆነው ያገለግላሉ።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም አንዳንድ የውጭ ሀገር ተማሪዎች ለቪዛ ማራዘሚያ ወይም ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ወደ ሩሲያ ጦር ሠራዊት እንዲገቡ ግፊት እንደተደረገባቸው በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ ስጋት አድሮባቸዋል።በዩክሬን ኃይሎች የተማረኩ በርካታ ተማሪዎች ወታደራዊ ኮንትራት የፈረሙት በመባረር ወይም በመታሰር ዛቻ ተገደው መሆኑን ገልፀዋል።ሌሎች ደግሞ ወደ ሌላ የሩሲያ የጦርነት ሥራ፤ ለምሳሌ የጦር መሳሪያ እና ጥይቶችን በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ውስጥ እንዲሰሩ ተደርገዋል። ተንታኞች እንዲህ ዓይነት አሰራር የሩስያን የኃይል ፍላጎት ሊያዳክም እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ።«በአሁኑ ጊዜ ሰዎች ለትምህርት ተጋብዘው ለትምህርታቸው ገንዘብ ተከፍሎ፤መጨረሻ ላይ የተለየ ነገር ካደረጉ ፤ ለሩሲያ ገጽታ በጣም መጥፎ ነው» ያሉት ፊላቶቫ፣ አክለውም «ሩሲያ የአፍሪካ አገሮችን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ አጋርነት ትፈልጋለች።»ብለዋል።
ያለፈውን የሶቪየት ታሪክ ለመድገም
በሶቪየት የግዛት ዘመን፣ ሞስኮ ራሷን በእስያ፣ በአፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ ያሉ አዲስ ነጻ መንግሥታት አጋር አድርጋለች።
በሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊ ካልሆኑ አገሮች የመጡ ተማሪዎች፣ ብዙዎቹ ከጊዜ በኋላ የፖለቲካ ወይም የንግድ መሪዎች ሆነው በሶቪየት ኅብረት ትምህርት አግኝተዋል።የዚህ ምልክት ተደርጎ የሚታየው በ1960 ዓ.ም የተቋቋመው የፓትሪስ ሉሙምባ የሕዝቦች ወዳጅነት ዩኒቨርስቲ ፤የሶቪየት የውጭ ፖሊሲ አላማዎችን ለማራመድ በማደግ ላይ ካሉ ሃገራት ተማሪዎችን ያሰለጠን ነበር።
ለአፍሪካ ተማሪዎች ተመጣጣኝ ትምህርት
ከጂኦ-ፖሊቲካው ባሻገር ሩሲያ ውስጥ የትምህርት ክፍያ እና የኑሮ ወጪዎች ከምዕራቡ ዓለም እንዲሁም ከአንዳንድ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች በጣም ያነሱ ናቸው።«የሩሲያ ዩኒቨርሲቲዎች በአውሮፓ ወይም በአንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት ከመማር በጣም ርካሽ ናቸው»ሲል ሩሲያ ውስጥ የሚማሩ ሦስት ልጆች ያሏቸው ዚምባብዌዊ ወላጅ ኪት ባፕቲስት ተናግረዋል።«በሩሲያ ውስጥ እዚህ ዚምባብዌ ከሚማር ተማሪ ጋር ሲወዳደር መጠለያ እና ምግብ በጣም ርካሽ ነው።» ብለዋል ።ሩሲያ ውስጥ ለመድኃኒት እና ለሌሎች ልዩ ሙያዎች ዓመታዊ የትምህርት ክፍያ በ$2,000 (€1,719) እና $10,000 (€8,596) መካከል ሲሆን በአውሮፓ ወይም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ግን ከ$20,000 እስከ $40,000 ይደርሳል።ከዚህ አንፃር «የተመጣጣኝ ዋጋ እና ሩሲያ ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ያለው ጥሩ ግንኙነት ትልቅ ምክንያቶች ናቸው። በአፍሪካ ውስጥ ያሉ ብዙ ወጣቶች ሩሲያ ውስጥ መማር ይመርጣሉ» ብለዋል ማኩምቤ ለDW።
ፊላቶቫ በበኩላቸው በክሬምሊን ሆን ተብሎ ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ዝቅተኛ ወጪዎችን እንደሚይዝ ተናግረዋል።«ነጻ የትምህርት ዕድሉ ሙሉ በሙሉ የሚከፈል ከሆነ ከፍለው መማር ለማይችሉ አፍሪካውያን ተማሪዎች ጥሩ አጋጣሚ ነው።ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት ትምህርት በምዕራቡ ዓለም አልፎ ተርፎም በአፍሪካ ብርቅ ነው።» ሲሉ ገልፀዋል።
ምዕራባውያን አገሮች ተማሪዎችን እየገፉ ነው
ተንታኞች በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደውን የኢሚግሬሽን እና የቪዛ ፖሊሲዎች ወደ ሩሲያ ለሚደረገው ሽግግር እንደ ሌላ ምክንያት ይጠቅሳሉ።በሰኔ ወር ዩናይትድ ስቴትስ ለበርካታ የአፍሪካ ሃገራት የተማሪ ቪዛዎችን ጨምሮ ቪዛ መስጠትን አግዳለች።
ዋሽንግተን ከ6,000 የሚበልጡ የተማሪ ቪዛዎችን ከልክ በላይ መቆየትን እና «ሽብርተኝነት መደገፍ»ን ጨምሮ የአሜሪካን ሕግ ጥሰዋል በሚል ሰበብ ሰርዛለች።ባፕቲስት እንደሚሉት «የምዕራባውያን አገሮች አሁን ነጻ የትምህርት እድት እና ቀላል የተማሪ ቪዛ ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ነው።
«በእኛ ጉዳይ አሜሪካ የመጀመሪያዋ አማራጭ ነበረች፣ የቪዛ ማመልከቻዎች ግን መቋረጣቸውን አውቀናል ።»ብለዋል።
ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ