1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

አፍሪቃውያን ካርዲናሎች በመጭው የጳጳስ ምርጫ እና በኮንጎ የካቪላ መመለስ የፈጠረው ውጥረት

ፀሀይ ጫኔ
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 18 2017

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ዓለም ይልቅ የአማኞቿ ቁጥር በአፍሪካ እያደገ ነው። በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ካቶሊኮች ውስጥ የአፍሪካውያን 20 በመቶውን ይይዛሉ።ከዚህ አንፃር ቤተክርስቲያኗ በሟቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ምትክ አፍሪቃዊ ጳጳስ ትምርጥ ይሆን?በሌላ በኩል የኮንጎ የቀድሞው መሪ ጆሴፍ ካቢላ አማፂያንን ተቀላቅለዋል መባሉ ውጥረት ፈጥሯል።

 ጋናዊው ካርዲናል ፒተር አኩያህ ቱርክሰን ርዕሰሊቃነ ፃጻሳት ፍራንሲስ ጋር
ጋናዊው ካርዲናል ፒተር አኩያህ ቱርክሰን ርዕሰሊቃነ ፃጻሳት ፍራንሲስ ጋር ምስል፦ Vatican Media/ZUMA/IMAGO

ትኩረት በአፍሪቃ፤አፍሪቃውያን ካርዲናሎች በመጭው የካቶሊክ ጳጳስ ምርጫ እና በኮንጎ የካቪላ መመለስ የፈጠረው ውጥረት

This browser does not support the audio element.

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በፍራንሲስ ህልፈት ሃዘን ላይ ናቸው። በ88 ዓመታቸው  ያለፈው ሰኞ በፋሲካ ማግስት ሮም ውስጥ ያረፉት የቤተክርስቲያኗ መሪ  በ12 ዓመታት የጵጵስና ዘመናቸው “የሕዝብ ጳጳስ” በመባል ይታወቃሉ።
በተለይ በአፍሪካ የሚገኙ ብዙ ካቶሊኮች ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ማሳያዎች ይልቅ ቀለል ባለ የሕይወት ዘይቬ በመከተል መምራትን ከመረጡት ከአርጀንቲናዊው ተወላጅ ሊቀ ጳጳስ ፍራንሲስ ጋር የቅርብ ትስስር እንዳላቸው ይገልፁ ነበር።
በአፍሪቃ ከፍተኛ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ባሏት ናይጄሪያ  አስደሳች የፋሲካ በዓል በሚከበርበት ቅዳሜና እሁድን ተከትሎ  አብያተ ክርስቲያናት እና ካቴድራሎች ላይ የሀዘን ድባብ የነገሰ ይመስላል።ከሌጎስ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሚራንዳ ሞሸሸ የሚወደዱ ጳጳስ ነበሩ ይላሉ።
«የምወደወዳቸው ጳጳስ ነበሩ። እና በጣም ትሑት እና ጌታን የሚወዱ ነበሩ። ማለቴ ለዓለም ሁሉ እና ለካቶሊክ እምነት ብዙ ነገር አድርጓል። ልቤ ተነክቷል። በእግዚአብሔር ቸርነት የእሳቸውን ባሕርይ የያዘ እና ሁሉም ነገር እንደ እሳቸው የሆነ ሌላ ጳጳስ እንዲኖረን እመኛለሁ።» ብለዋል።

አፍሪቃዊ የሀይማኖት አባት 

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ዓለም ይልቅ አፍሪካ በፍጥነት እያደገች ያለችበት ቦታ ነው። ከቫቲካን በወጣው አኃዛዊ መረጃ መሠረት በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ካቶሊኮችን ውስጥ የአፍሪካውያን 20 በመቶውን  ይይዛሉ።
ይህን መነሻ በማድረግም፣ ቤተ ክርስቲያኗን የሚመራ አንድ አፍሪቃዊ ጳጳስ እንዲመረጥ የሚጠይቁ ጥሪዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየበረከቱ መጥተዋል።ኮንክላቭ እየተባለ በሚጠራው የቤተክርስቲያኒቱ ጉባኤ፤-ቀጣዩን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የመምረጥ ኃላፊነት የተጣለባቸውን 135 ከፍተኛ ካርዲናሎች ይሰበሰባሉ። ጉባኤው በግንቦት ወር መጀመሪያ የሚካሄድ  ሲሆን የተወሰኑ የአፍሪቃዊ ስሞችም በእጩዎች ዝርዝር ውስጥ ይኖራሉ።
በቤተክርስቲያኒቱ ታሪክ እስካሁን  ከሰሜን አፍሪቃ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት የመሩ ሲሆን፤ ባለንበት ዘመን ደግሞ  ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪቃዊ ጳጳስ የሚመረጥበት ጊዜ  የደረሰ ይመስላል።በጉባኤው ወቅት፣ እያንዳንዱ ካርዲናል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ከፍተኛ ቦታ ለመያዝ  የራሳቸውን ወይም የሌላ ካርዲናልን ስም ወደፊት ማምጣት ይችላሉ። ልክ እንደሌላው የአመራር ስራሁሉ፤  ውድድሩን  ለማሸነፍ ከዚህ ቀደም የነበረ  የስራ ልምድ ብዙውን ጊዜ እንደ ወሳኝ እና እንደ ቁልፍ ነገር ይቆጠራል።
በመጪው ጉባኤ ከሌሎቹ ጋር  በመሆን ከአፍሪቃ 18 ካርዲናሎች የሚለዩ ቢሆንም፣  ከአህጉሪቱ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት  ሁለት ስሞች ብቻ ናቸው።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሌላው ዓለም ይልቅ የአማኞቿ ቁጥር በአፍሪካ እያደገ ነው። በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ካቶሊኮች ውስጥ የአፍሪካውያን 20 በመቶውን ይይዛሉ።ምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

ፒተር ቱርክሰን፡ ባለ ግርማ ሞገሱ የጋና ሰላም ፈጣሪ

ለቀጣዩ ጵጵስና ከሚመረጡት መካከል ጋናዊው ካርዲናል ፒተር ቱርክሰን ይገኙበታል።የረዥም ጊዜ የኬፕ ኮስት ሊቀ ጳጳስ ሲሆኑ፤በ2009 ዓ/ም ወደ ሮም ተዛውረው ፣  የፍትህ እና የሰላም ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ሲስተር ጃሲንታ ቶኒባ እንደሚሉት በሁለቱ ጳጳሳት መካከል ተመሳሳይነት አለ።
«በጳጳሱ እና በካርዲናል ቱርክሰን ስብዕና ውስጥ አንዳንድ ተመሳሳይነት አለ። ትህትና፣ ቀለል ያለ አቀራረብ ፣ለድሆች እና ለችግረኞች ርህራሄ እና ፍቅር በመስጠት። እንዲሁም ለእናት ምድር   ተቆርቋሪነ በመሆን። ይህም ለህዝባችን ህይወት ጠቃሚ  ነው።»
ታዲወስ ኩሽ የተባሉት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቄስ በበኩላቸው፤
« ካርዲናል ፒተር አፒያ ቱርክሰን በእርግጠኝነት ቤተ ክርስቲያንን በብዙ መንገድ መምራት የሚችሉበት ሁሉም ባሕርያት አሏቸው። የብሔራዊ ሰላም ምክር ቤት የመጀመሪያ ሊቀ መንበር ነበሩ። እና በአገር አቀፍ ደረጃ ጥሩ ሰርተዋል። በተለይ  በ 2008 ምርጫችን በጣም ከባድ በነበረበት ወቅት ነገሮችን ለማስታረቅ  በጥሩ ሁኔታ ሰርተዋል ። ያ በእውነቱ ለጋና ሰላም አምጥቷል። ፈጣሪ ራሱ ሰላም የሚፈጥሩ የተባረኩ ናቸው ይላል። ስለዚህ እርሳቸው በእርግጥ የእግዚአብሔር ልጅ ናቸው። እናም መንፈስ ቅዱስ በካርዲናሎች ኮሌጅ ላይ እንዲወርድ የክርስቶስ ልብ እና ሀሳብ ያለው ሰው ቤተ ክርስቲያኗን ይመራ ዘንድ እንጸልያለን።»ብለዋል።

ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፡ የኮንጎ ንቁ የቤተ ክርስቲያን መሪ

በመላው አፍሪቃ ሰላምን የሚፈጥሩ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ይህ ስሜት  የካቶሊክ አማኞች ብቻ አይደለም።በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ  ግጭት ለአስርተ አመታት ሲካሄድ ቆይቷል።  በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ባለፉት ወራት በመንግስት እና በኤም 23 አማፂያን መካከል ደም አፋሳሽ ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደ 50 ሚሊዮን በሚጠጉ ወይም  የሀገሪቱን ግማሽ ያህል ህዝብ  የካቶሊክ እምነትን ይከተላል።ከዚህ አንፃር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከሰሃራ በታች ካሉ ታላላቅ ጉባኤዎች አንዱ ነው።
ሀገሪቱ በአፍሪቃ በካቶሊክ እምነት ውስጥ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች መገኛም ነች።በአፍሪካ  የኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየምን የሚመሩት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በካቶሊክ እምነት ውስጥ በአፍሪካ ውስጥ ታዋቂ ከሆኑ ሰዎች አንዱ ናቸው።አምቦንጎ ቤሱንጉ የካርዲናል አማካሪዎች ምክር ቤት አካል በመሆን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ታማኝ በመሆን ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል።ያም ሆኖም፣ በአቡነ ፍራንሲስ እና በካርዲናል አምቦንጎ ቤሱንጉ መካከል ጉልህ ልዩነቶች ነበሩ። ምንም እንኳን በካርዲናል አምቦንጎ ለሴቶች እኩል እድል እንደ መስጠት ያሉ አንዳንድ የተራማጅ አስተሳሰቦችን የሚደግፉ ቢሆኑም፤ በ2023 ዓ/ም በአቡነ ፍራንሲስ የተላለፈውን የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ከቤተክርስቲያኒቱ በረከት የማግኘት ፈቃድን ከተቹት መካከል አንዱ ነበሩ። 
የአፍሪካ ኤጲስ ቆጶሳትጉባኤዎችን በመወከል፣ አምቦንጎ ቤሱንጉ አዋጁን ለመቀበል ፍቃደኛ ባለመሆናቸው፣ በመላው አፍሪቃ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኙ ሲሆን፤  ሮም ለተቃውሞው የሰጠችው ምላሽ ዝምታ ነበር።የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ኤጲስ ቆጶስ ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ዶናቲየን ንሾል እንደሚሉት   ለኮንጎ ሰላም ባደረጉት የማይናወጥ ድጋፍ  ሟቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንሲስ፤ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሁል ጊዜ ሞቅ ያለ እና የትብብር መንፈስ የጎላበት ነበር ።

ማቹ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን መሪ ርዕሰሊቃነ ፃጻሳት ፍራንሲስ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋርምስል፦ Pacific Press Agency/IMAGO

በጎርጎሪያኑ በ2023 ዓ/ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በኪንሻሳ ባደረጉትን ጉብኝት የማይረሱ ትዝታዎች እንዳሏቸውም ንሾል ተናግረዋል። በወቅቱ በሀገሪቱ በተፋላሚ ወገኖች መካከል መግባባት ለመፍጠር ባደረጉት ጥረት፤ ከሰሜን ኪቩ ግዛት የልዑካን ቡድንን ተቀብለዋል።
በመሬት ላይ፣ ለብፁዕ ካርዲናል አምቦንጎ ቤሱንጉ የጵጵስና ውድድር  ትልቅ ድጋፍ አለ። ኪንሻሳ የሚገኙት ሁጉስ ታምፉሙ ለDW እንደተናገሩት ይህ አፍሪካውያን ቤተ ክርስቲያኗን መምራት እንደሚችሉ ለማሳየት ለማሳየት ትልቅ ዕድል ነው።  
«ይህ ድል ለአፍሪካውያን እና ለሁላችንም የካቶሊክ ክርስትያኖች ድል ነው። ምክንያቱም  አፍሪቃ የመምራት አቅም እንዳላት ለማሳየት ለእኛ ትልቅ ነገር ነው።በግብረ ሰዶማውያን ላይ በተነሳው ክርክር ወቅት ካርዲናል አምቦንጎ ፤ ይህን እንደ አፍሪካዊ መቀበል አንችልም ሲሉ መቃወማቸውን እናስታውሳለን።ስለዚያም በጣም ግልፅ ነበር። እናመሰግናቸዋለን፣ ሁሉም ክርስቲያኖች ከጎናቸው ይሆናሉ።»

አፍሪቃውያን አፍሪቃዊ ጳጳስ ይፈልጋሉ?

ለአንዳንድ አፍሪካውያን እንደ አምቦንጎ ቤሱንጉ ያሉ ካርዲናሎች ብዙዎች አውሮፓ ተኮር ከሚሉት አመራር  ራሳቸውን ያገለሉ መሆናቸው ነው።
ታምፉሙ እንደሚሉት የአምቦንጎ ቤሱንጉ የተመሳሳይ ጾታ በረከቶችን አለመቀበል፤ አፍሪቃውያን ከቤተ ክርስቲያናቸው ምን እንደሚጠብቁ የሚያመለክት ነው። እሳቸው በግልፅ «አይ እኛ አፍሪካውያን ይህን አንቀበልም።» ብለው ነበር።ሆኖም ግን በግብረ ሰዶም ላይ እንዲህ ያለ ፅኑ ተቃውሞ በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ለመመረጥ ለአፍሪቃውያን ዕጩዎች  አሉታዊ ተፅዕኖ  ሊኖረው ይችላል።
ምክንያቱም የፍራንሲስ የቤተክርስቲያኑ የማስታረቅ እርምጃዎች ከአፍሪካ ውጭ፣ በአብዛኛዎቹ ተቀባይነት አግኝተዋል። አንዳንድ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሟቹ ጳጳስ  ጉዳዩን የበለጠ መግፋት ይችሉ እንደነበር ፍንጭ ሰጥተዋል።
DW ስለ አፍሪካውያኑ ጳጳሳት የመመረጥ ዕድል የተጠየቃቸው ንሾል የአዲሱ ጳጳስ ምርጫ ከኮታ እና ከዘር የተሻገረ ነው ይላሉ።
«ፖለቲካ ውስጥ አይደለንም ። በኮታ፣ በተራ  እና  በዘር የሚታሰብበት ቦታ አይለም። እኛ ለሁሉም የሚሆን ቦታ ባለበት ሁለንተናዊ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነን። እንደ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንን የሚመራው መንፈስ ቅዱስ ሥራውን እንዲሠራ መፍቀድ አለብን። እንደ ካህን ነፍሱ በሰላም እንዲያርፍ መፀለይ፣ ጌታም በዘላለማዊ ብፁዕነቱ እንዲቀበለው መፀለይ፣ ነገር ግን መነሻው ምንም ይሁን ምን ጌታ ከልቡ እረኛ የሚሆነውን ጳጳስ እንዲሰጠን ልንጸልይ ይገባል። በጣም አስፈላጊው ነገር ይህ ነው።»

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ለሟቹ ርዕሰሊቃነ ፃጻሳት ፍራንሲስ ፀሎተ ፍትሃት ሲደረግምስል፦ Seyoum Getu Hailu/DW

ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው

ከመጋረጃ ጀርባ ግን ባለሙያዎች ቱርክሰን ወይም አምቦንጎ ቤሱንጉ የመወዳደር  ዕድል ጥርጣሬ ውስጥ ያስገቡታል። የመጀመሪያው የእድሜ ጉዳይ ሲሆን፤የ 76 ዓመቱ ቱርክሰን ለአንዳንዶች በጣም ያረጁ መስለው ሊታዩ ይችላሉ። የ 65 ዓመቱ አምቦንጎ ደግሞ በአንዳንዶች ዘንድ በጣም ወጣት ሊባሉ እና ለአስርተ አመታት ቤተክርስቲያኗን ይዘው ሊቆዩ ይችላሉ የሚል ፍርሃት ሊያሳድር ይችላል።
ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዘመናት  ለቁጥር የሚታክቱ የጾታ ጥቃቶችን  በግልጽ ለመፍታት ያለመቻሏ ጉዳይ ነው።ይህ የሚያሳዝን የቤተ ክርስቲያኗ ምዕራፍ በፍራንሲስ አስተዳደር በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በሌሎችም  መሻሻል ቢታይም፣ አፍሪካ ውስጥ ግን ጉዳዩ አሁንም ድረስ አይነኬ ይመስላል። 

በዚህ የተነሳ በጉባኤው ላይ የሚካፈሉ ካርዲናሎች አቋማቸው ለስላሳ ወይም አሻሚ ተብሎ ሊተረጎም በሚችል ሁኔታ እጩዎችን ለመምረጥ ሊያቅማሙ ይችላሉ። የሌጎስ ሊቀ ጳጳስ አልፍሬድ አዴዋሌ ማርቲንስ፣ግን የቤተክርስቲያኗ ምእመናን በማንኛውም ሁኔታ ወደ ጉባኤው እንዲቀርቡ አስጠንቅቀዋል።ማርቲንስ ከDW ጋር ባደረጉት ቆይታ የፍራንሲስ ጵጵስናን ተከትሎ ብቁ ተተኪ የማግኘት ጥያቄ  በፊት ከነበረው የበለጠ የተወሳሰበ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
«እሳቸው  ፍራንሲስ ከሩቅ ቦታ ከመጡ ካርዲናሎች ውስጥ መምረጣቸው በራሱ ማንም ሰው ከየትኛውም ቦታ ሊቀ ጳጳስ ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው ። አፍሪቃ በተፈጥሮዋ ከቁጥር ብዛት እና ካለው አስደናቂ ብዝሃነት አንፃር  በእርግጠኝነት ለቤተ ክርስቲያኗ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ወሳኝ ናት።ማንም በዚህ ላይ መከራከር አይችልም።እርግጠኛ ነኝ  የመንፈስ ቅዱስ ስራ እና የሚመርጡት ካርዲናሎችም በአእምሯቸው ውስጥ ይህ ሃሳብ ይኖራል። ለዚህ ነው ማንኛውንም ነገር መጠበቅ አለብን የምለው።»

በኮንጎ የካቪላ መመለስ የፈጠረው ውጥረት

ከዚህ ቀደም ሰላምን ለማስጠበቅ የተደረጉትን በርካታ ያልተሳኩ ሙከራዎችን ተከትሎ ታዛቢዎች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በኤም 23 አማፂያን መካከል የተፈረመውን የመጨረሻውን የእርቅ ስምምነት በታላቅ ጥንቃቄ እየተመለከቱት  ነው። በኳታር የተካሄደው የመጨረሻው የሰላም ስምምነት በሀገሪቱ ባለፉት ወራት ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን  ተከትሎ የተካሄደ  ነው።
«በጋራ ስምምነት ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ማንኛውንም የጥላቻ ንግግር እና ማስፈራሪያ ውድቅ ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣሉ»ይላል ያለፈው ረቡዕ ሁለቱ ወገኖች ያወጡት የጋራ መግለጫ ።
ነገር ግን በዚህ ስምምነት መካከል በሀገሪቱ  ሌላ ዜና ተስፋን ያጨለመ ይመስላል።
የቀድሞው የኮንጎ ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ካቢላ ለብዙ ወራት በኤም 23 አማፂያን ቁጥጥር ስር በምትገኘው እና በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኘው በጎማ  ከተማ በቅርብ ቀናት  መታየታቸው ተዘግቧል።የካቢላ በጎማ መታየት በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ከፍተኛ ክርክር ከመፍጠሩ ባሻገር የሚናፈሰው ወሬ የኮንጎን መንግስትም ያስቆጣ ይመስላል።

የኮንጎ የቀድሞው መሪ ጆሴፍ ካቢላ ከስደት ተመልሰው አማፂያንን ተቀላቅለዋል መባሉ የሀገሪቱን መንግስት አስቆጥቷል። ምስል፦ Arlette Bashizi/REUTERS

ለሪፖርቶቹ ምላሽ የኮንጐ መንግስት የካቢላን፤  የህዝቦች መልሶ ግንባታ እና ዲሞክራሲ ፓርቲን (PPRD) እንዲታገድ  እና በቤተሰቡ እና በፖለቲካ አጋሮቹ ላይ የጉዞ ገደቦችን አውጥቷል። የካቪላ  ፓርቲ በክሱ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።
ነገር ግን የPPRD ደጋፊ የሆነው አማኒ ካኪምባ ክሱ መሠረተ ቢስ ነው ብሎ ያምናል።ካኪምባ “ካቢላን እዚህ ጎማ ውስጥ መገኘቱን የሚያረጋግጥ ፎቶ ወይም ቪዲዮ ማንም አላሳየም” ሲል ካኪምባ ገልጾ ካቢላ የሚደብቅበት ምንም ምክንያት ስለሌለ ወደ ሀገራቸው የመመለስ ነፃነት ሊኖራቸው ይገባል ሲሱ ይከራከራሉ።

ኪንሻሳ ስለ ካቢላ መመለስ ምላሽ ሰጠች

ሆኖም መንግሥት ነገሮችን በተለየ መንገድ ሊመለከት ይችላል።ካቢላ በኤም 23 አማፂያን ቁጥጥር ስር ወደምትገኘው ወደ ጎማ መመለሳቸው በኮንጎ መንግስት ዘንድ ከፍተኛ የሀገር ክህደት ተግባር ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። ምክንያቱም ቡድኑ በሩዋንዳ መንግስት የተደገፈ  የውጭ  ወኪል ሆኖ ነው የሚታየው። የሀገር ውስጥ እና የፍትህ ሚኒስቴር በቀድሞው መሪ ላይ ህጋዊ ክስ መጀመሩን እና የካቢላን ንብረቶች መያዙን አስታውቋል።

ነገር ግን በሴንት ፖል ኦታዋ፣ ካናዳ የግጭት ጥናት ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ኢቮን ሙያ ለDW እንደተናገሩት የካቢላን ንብረት መያዙ ከባድ ስህተት ነው።እሳቸው እንደሚሉት ካቢላ የቀድሞ ርዕሰ ብሄር በመሆናቸው፤  በሠራዊቱ እና በሀገሪቱ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ  ክብር ይገባቸዋል ። ንብረቶቻቸውን መያዝም ሁኔታውን የበለጠ ያባብሰዋል ብለዋል ።ያም ሆኖ ካቢላ ወደ ኮንጎ ስለመምጣታቸው ምንም አይነት መግለጫም አልሰጡም።ኢቮን ሙያ ካቢላ እንቆቅልሽ ናቸው ይላሉ። «እስካሁን ከኪጋሊ ወደ ጎማ ስለመሄዳቸው እና ጉማ ስለመቀመጣቸው የሚያረጋግጥ ምንም ነገር የለም።ሁሉም ነገር ግምት ነው።ካቢላ በስልጣን ላይ ሆነውም ሆነ ስልጣን ለቀው ሁልጊዜ እንቆቅልሽ ናቸው።» በማለት ገል\ጸዋል።

የማይመች ትብብር

በስልጣን ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ ግን ካቢላን እንደ ስጋት የቆጠሩ አይመስልም። ሁኔታው ግን ስልጣናቸውን የሚጎዳ ነው።
ካቢላ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚደንት ሆነው ለ18 ዓመታት እስከ 2019 ድረስ ቆይተዋል። በመጨረሻም ካቢላ ከፌሊክስ ችሴኬዲ ጋር ጥምረት ፈጠሩ።ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በ2023 ዓ/ም በሁለቱ መሪዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ  ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሰደድ ተገደዱ።
ያ አለመስማማት በክልላዊ ፖለቲካ እና በአጠቃላይ ግጭት ውስጥ ከፍተኛ ስም  ካላቸው እና   የኤም 23 አማፂያን እንደ ወታደራዊ ክንፍ ከሚቆጥሩት የኮንጎ ወንዝ አሊያንስ (ኤኤፍሲ) ንቅናቄ መሪ ከኮርኔይል ናንጋአ ጋር  የተገናኘ ሆኗል-።
ናንጋ በ2015 የኮንጎን ምርጫ ኮሚሽን እንዲመ በጊዜው ፕሬዝዳንት በካቢላ ተሰይመው ነበር።የካቢላን ተተኪ ለመምረጥ በ2018 በተደረገው ምርጫም  ሰርተዋል።ይሁን እንጂ በተለይ የሁለቱ ምርጫዎች የማጭበርበር ውንጀላ የበዛበት ሲሆን፤ የችሴኪዲ ተቀናቃኝ ማርቲን ፋዩሉ በትክክል ድምጽ ማግኘቱን በርካታ ዘገባዎች አረጋግጠዋል።ነገር ግን ችሴኪዲ ምንም ይሁን ምን የምርጫው አሸናፊ ተብለዋል።

'ካቢላ አቋማቸውን ግልጽ ማድረግ አለባቸው'

ካቢላ ከናንጋ ጋር ባለቸው ግንኙነት የM23 አማፂ ቡድንን ይደግፋሉ በሚል በተደጋጋሚ  ተከሰዋል።
ነገር ግን ኦቮን ሙያ እንደሚሉት  ካቢላ የኤም 23 ተገንጣይ ቡድንን መደገፍ ቢያንስ "አከራካሪ" ነው። ፕሬዚዳንት በነበሩበት ወቅት  የአማፂውን ንቅናቄ መዋጋታቸውንም ይገልፃሉ።ከዚህ አንፃር የመንግስት ምላሽ የተጋነነ ነው ይላሉ።
«ለካቢላ መመለስ የመንግስት ምላሽ የተጋነነ ይመስላል።ይህ በመንግስት እና በተቃዋሚ ዎች መካከል ባለው ግንኙነት ውስጥ አደገኛ ቅድመ ሁኔታን ያስቀምጣል።እኛ ጦርነት ውስጥ ነን።እና ፕሬዚዳንቱ ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ እየሞከሩ ነው።የፖለቲካ ስርዓቱን አንድ ክፍል በማስቀረት ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ መሞከር ጥሩ መንገድ ነው ብዬ አላምንም።» ሲሉ ተናግረዋል። ሙያ እንደሚገልፁት ፤ ካቢላ እየተካሄደ ባለው ግጭት አቋማቸውን ግልጽ ካደረጉ እንዲሁም ከዓማፅያን ቡድኖች እና እንደ ናንጋ ካሉ መሪዎች ጋር ያለቸውን ግንኙነት በይፋ ከገለፁ፤ዓላማቸው በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎም አይችልም።

የአንዳንድ ሰዎች አስተያየት ግን ካቢላን የሚተች ነው

«በጣም ያሳዝናል።የሴናተር ኮፍያ ለብሰው ለ18 ዓመታት ሀገር የመሩት የቀድሞ  ፕሬዚዳንት የነፃነት መፈክር ይዘው ምስኪኖችን በሚገድል አማፂ ቡድንን ሲመሩ ማየት።ብቸኛው ዓላማ ደግሞ ስልጣን መልሶ ለማግኘት ነው።» ብለዋል።
ነገር ግን ሙያ፤ በሂደት ላይ ባለው ሁኔታ እና ኮንጎ ውስጥ በሚንቀሳቀሱት ከ120 በላይ አማፂ ቡድኖች ላይ መንግስት እና የተቃዋሚዎች  የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ብለው ያምናሉ። 

በኮንጎ የተካሄደው እርቅ ተጨማሪ ንግግሮችን የሚፈልግ ቢሆንም፤ ካቢላ በሠላም ጥረቱ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎታቸውን አልደበቁም።ምስል፦ Siphiwe Sibeko/REUTERS

የካቢላ ሚና በሰላም ጥረቶች ላይ 

በኮንጎ የተካሄደው እርቅ ደካማ እና ተጨማሪ ንግግሮችን የሚፈልግ ቢሆንም፤ ካቢላ በሠላም ጥረቱ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎታቸውን አልደበቁም።
«ለ 18 አመታት ርዕሰ ብሄር ነበሩ።  በኪንሻሳ ውስጥ ከአማፂያን እና ከመንግስት ጋር የመነጋገር ችሎታ አላቸው።. ካቢላ ከሩዋንዳ እና ከሌሎች ከዲሞክራቲክ ኮንጎ  የግጭት ተዋናዮች ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸው። ስለሆነም ከአሁኑ መንግስት ጋር በመተባበር የሽምግልና ጥረቶችን እስካደረጉ ድረስ ጠቃሚ  ሊሆኑ ይችላሉም።» ብለዋል።ችሴኪዲ ግን ካቢላን እንደ ሰላም ፈጣሪ ሳይሆን እንደ ግጭት ቀስቃሽ ነው የሚመለከቷቸው። -
ካቢላ በበኩላቸው፤ ቼሴኬዲ በኮንጎ ውስጥ ያለውን ግጭት በተፋላሚ ወገኖች መካከል ከሚደረገው የውስጥ ውይይት ይልቅ፤ በውጪ ጣልቃ ገብነት ላይ በመተማመን የሀገሪቱን ግጭት አላግባብ እየተጠቀሙ ነው ሲሉ ከሰዋል።እንደ  ኦቮን ሙያ ገለጻ፤ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሁለቱ መሪዎች መግባባት እና የተቀናጀ ጥረት አስፈላጊ ነው።
«እኛ በግጭት ውስጥ ነው።,» ያሉት ሙያ፤  የፖለቲካ ስርዓቱን አንድ አካል በማግለል ሀገሪቱን አንድ ለማድረግ መሞከርም ጥሩ መንገድ አይደለም ።» ሲሉ ለDW ተናግረዋል።


ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW