1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የአፍሪቃ የ2024 ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ

ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 6 2016

ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በአፍሪካ በመጭው የጎርጎሪያኑ 2024 ዓ/ም ብዙ ምርጫዎች ይካሄዳሉ።ነገር ግን የሳህል አካባቢ ያልተረጋጋ ሆኖ እንደሚቆይ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።በርካታ የአፍሪቃ ሀገሮችም ለበለጠ ዲሞክራሲ ይታገላሉ።ነገር ግን የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ በፍጥነት እንደሚያድግ ባለሙያዎች ይተነብያሉ።

 የግብፅ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታህሳስ 18 ቀን 2023 ውጤቱ ይፋ ይሆናል።
ሰሞኑን የተካሄደው የግብፅ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ታህሳስ 18 ቀን 2023 ውጤቱ ይፋ ይሆናል።ምስል፦ Mohamed Elshahed/Anadolu/picture alliance

አፍሪቃ በ2024፤በቀውስ እና በእድገት መካከል

This browser does not support the audio element.


በየጎርጎሪያኑ የዘመን ቀመር 2023 ዓ/ም ተሸኝቶ አዲሱን 2024 ዓ/ም ለመቀበል ሁለት ሳምንት ቀርቶታል። በዛሬው የትኩረት በአፍሪቃ ዝግጅት በመጭው  2024 ዓ/ም የአፍሪቃ አህጉርን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ምን ሊመስል ይችላል የሚለውን በአጭሩ ይዳስሳል። 
በጦርነት፣ በረሀብ እና በድህነት ስሟ ተደጋግሞ የሚነሳው አፍሪቃ በመገባደድ ላይ ባለው 2023 ዓ/ም በርካታ ክስተቶችን አስተናግዳለች። በመጭው 2024 ዓ/ም ከሚጠበቁ ክስተቶች አንዱ ምርጫ ነው። ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በአፍሪካ በመጭው ዓመት ብዙ ምርጫዎች ይደረጋሉ።
በቅርቡ መሪዋን ለመምረጥ ምርጫ ካካሄደችው ግብፅ ስንጀምር፤ ግብፅ በመጭው ታኅሣሥ 18 ቀን 2023 የምርጫ ውጤት ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል። ታዛቢዎች እንደሚሉት አምባገነኑ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በድጋሚ እንደሚመረጡ እና በመጭው ዓመትም እንደሚቀጥሉ ይገምታሉ። በተመሳሳይ ጊዜ ሀገሪቱ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች። .

በሌላዋ አፍሪቃዊት ሀገር ኮንጎ ከቀናት በኋላ ምርጫ ይካሄዳል ነገር ግን በምሥራቃዊው የሰሜን ኪቩ ግዛት የተወሰኑ ክፍሎች በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ናቸው። በጎርጎሪያኑ በየካቲት 2024 ከሚካሄደው ምርጫ በፊት በደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር በሴኔጋል ህዝባዊ ተቃውሞዎች ከወዲሁ ተቀስቅሰዋል። ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል ግፊቱን ለማርገብ ለሦስተኛ ጊዜ ከእጩ ከመሆን ተቆጥበው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ባን ወደ ውድድር ልከዋል።
በጆሃንስበርግ የሮዛ ሉክሰምበርግ ተቋም ሠራተኛ የሆኑት ፍሬድሰን ጊሌንጌ ግን በዘፈቀደ በሚደረግ አፈሳ  እና እስር ምክንያት እስካሁን ድረስ ከመወዳደር የተከለከሉት የተቃዋሚው እጩ ኦስማን ሶንኮ  ችግሮች አሉባቸው ይላሉ። «ይህም አለመረጋጋትን ወደ ሚያስከትል ሁከትና ብጥብጥ ይመራል» ሲሉ ጊለንጌ ለDW ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪቃ አመኔታ ለማግኘት እየታገለች ነው
በደቡብ አፍሪካ በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ምርጫዎች አንዱ በግንቦት ወር ይካሄዳል። እዚህ ያለው ጥያቄ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) አብላጫ ድምፅ ያገኛል ወይ?  የሚል ሲሆን ፉክክሩም በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

ደቡብ አፍሪቃ በመጭው 2024 ዓ/ም ምርጫ ከሚያካሂዱ የአፍሪቃ ሀገሮች አንዷ ነችምስል፦ Denis Farrell/AP Photo/picture alliance

ፓርቲው ከፍተኛ ድምፅ የማጣት ችግር እያንዣበበት በመሆኑ፤ የፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ፓርቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ50 በመቶ በታች በማግኘት ሊንሸራተት ይችላል። ስለዚህም ኤኤንሲ የሥልጣን ዘመኑን ለማረጋገጥ ከትንንሽ ፓርቲዎች ጋር በሚያደርገው ጥምረት ላይ መተማመን እንዳለበት ብዙ ማሳያዎች አሉ። አፍሮባሮሜትር የተባለው የጥናት ተቋም ባደረገው ጥናት አብዛኛው ደቡብ አፍሪካውያን (70 በመቶ) በሀገራቸው የዲሞክራሲ አተገባበር  ቅር መሰኘታቸውን ያሳያል።

ፍሪድሰን ጌሌንግ እንደሚሉት ኅህብረተሰቡ በተለይ አዲሱ ትውልድ ከመንግሥት ብዙ ይጠብቃል። «ደቡባዊ አፍሪቃን ስንመለከት ለምሳሌ በሞዛምቢክ፣ ዚምባብዌ እና ደቡብ አፍሪካ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ውል ቅኝ አገዛዝን በመዋጋት ላይ የተመሰረተ ነው።ነገር ግን ባለፉት ዓመታት አሁን ያለው ትውልድ ካለፈው  የቅኝ ግዛት ታሪክ ጋር ያለው ግንኙነት እየቀነሰ እየቀነሰ እንደመጣ ይሰማናል።እና ከመሪዎቹ የተለየ ነገር ይጠብቃል።»
ደቡብ አፍሪካውያን ከፍተኛ ሥራ አጥነትን እንደ ዋነኛ ችግር አድርገው የሚቆጥሩት ሲሆን፤ የወንጀልና የጸጥታ፣ የመብራት እና የውሃ አቅርቦት እንዲሁም ሙስና ደግሞ ተጨማሪ ችግሮቻቸው ናቸው። በቋፍ ላይ የሚገኘው  Eskom የተባለው የሀገሪቱ የሀይል አቅራቢ ድርጅት ፤ በሀገሪቱ በቂ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ ባለመቻሉ፣ ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ነው። የሀገሪቱ ህዝብ በመንግሥት አመራር ላይ ያለው እምነትም ከምንጊዜውም በላይ ዝቅተኛ ነው።

በሞዛምቢክ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ጊለንጌ እንደሚሉት «ሰዎች ለተቃዋሚዎች የበለጠ ድምጽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው።»
ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች እና ተቃዋሚው ፓርቲ ሬናሞ (ናሽናል ሬዚስታንስ ንቅናቄ) ገዥውን ፍሬሊሞ (የሞዛምቢክ ነፃ አውጭ ግንባር) በጥቅምት ወር በተካሄደው የክልል ምርጫ ላይ ማጭበርበር ተፈፅሟል በሚል እየከሰሰ ነው። እንደ ጊለንጌ አባባል ህዝባዊ አመጽ ይቀጥላል።

ስልጣን መልቀቅ ወይስ ድጋሚ ምርጫ?
በሥልጣን ላይ ባሉት መንግሥታት አለመርካትም በአንዳንድ ሃገራት ሥልጣን ወደ ተቃዋሚዎች እንዲሸጋገር ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ  ጋናን መጥቀስ ይቻላል። በአንድ ወቅት የበለፀገችው የምዕራብ አፍሪካዊት ሀገር  ጋና፤ በእዳ ውስጥ እየተዘፈቀች ነው፣ የመዋዕለንዋይ ፍሰት ቀንሷል ፤ የኑሮ ደረጃም እያሽቆለቆለ ነው። እንደ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት (EIU) አጠቃላይ የፓርላማ የአብላጫ ቁጥር የመቀነስ ስጋት አለ፣ ይህም አስተዳደርን አስቸጋሪ በማድረግ ማኅበራዊ አለመረጋጋት ይጨምራል። ለምሳሌ በማዳጋስካር ወይም እንደ አልጄሪያ እና ቱኒዚያ ባሉ የመግረብ አገሮች ይህ ሊታይ ይችላል ።

በሳህል መፈንቅለ መንግሥት የፈጠረው አለመረጋጋት 
በምዕራብ አፍሪካ ያለው የፖለቲካ ሁኔታም ተለዋዋጭ ነው፡ በወታደራዊ አስተዳደር ቀውስ ውስጥ በሆነችው ማሊ ወደ ሲቪል አስተዳደር መመለስ አሁንም ሩቅ ይመስላል።ማሊ፦ በወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት ማግስት

ሰኒ 18 ቀን 2023 በባማኮ የተካሄደውን ህገመንግስታዊ ሪፍረንደም በመቃወም የተደረገ ሰልፍ ምስል፦ AFP/Getty Images

በጎርጎሪያኑ የካቲት 2024 ይፋ የሆነው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምዕራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ /ECOWAS/ ማዕቀቡን እንዲያነሳ አድርጎታል። ኤኮዋስ በማሊና ቡርኪናፋሶ ላይ የጣለዉን ማዕቀብ አነሳይሁን እንጂ ማሊ ልክ እንደ ቡርኪናፋሶ ድምፅ የመስጫ ጊዜን ለሌላ ጊዜ አስተላልፋለች። ቀደም ሲል ግን የወታደራዊ  ጁንታ መሪው ኢብራሂም ትራኦሬ በሀምሌ 2024 ዓ/ም ምርጫ ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር። ነገር ግን በጥቅምት ወር በአገሪቱ ውስጥ ባለው ሁኔታ እርግጠኛ ባልመሆናቸው አዲስ ቀን ገደብ ሳያስቀምጡ  ለሌላ ጊዜ አስተላልፈዋል።

በለንደን የሚገኘው ቻተም ሀውስ ባልደረባ የሆኑት አሌክስ ቫይንስ እንደሚሉት ተከታታይ መፈንቅለ መንግሥት የታየበት መላው የሳህል ክልልም በ2024 አለመረጋጋቱ ይቀጥላል። «በርካታ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገበት የሳህል ክልል በሙሉ በ2024ም አለመረጋጋቱ ይቀጥላል። ከ 2019 ጀምሮ በማሊ፣ በኒጀር፣ በዴፋክቶ ቻድ፣ በሱዳን እና በቡርኪናፋሶ፣ በጊኒ እና በጊኒ ቢሳው መፈንቅለ መንግሥት አይተናል - የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎች ሊኖሩ ይችላሉ። በ2024 መፈንቅለ መንግሥት የተፈፀመባቸው አገራት ወደ ህገ-መንግሥታዊ ስርዓት ለመመለስ በአጭር ጊዜ  መደራደር ይሞክሩ ይሆናል ።»

ተንታኞች እንደሚሉት ተከታታይ መፈንቅለ መንግሥት የታየበት መላው የሳህል ክልልም በ2024 አለመረጋጋቱ ይቀጥላል

የአፍሪካ ኢኮኖሚ በፍጥነት ማደግ
በአህጉሪቱ በኢኮኖሚ ዘርፍ ያለው አዎንታዊ አዝማሚያ ብሩህ ተስፋን የሚፈጥር ነው። የአገራትን የኢኮኖሚ መረጃ የሚተነትነው፤ ኢኮኖሚክ ኢንተለጄንስ ዩኒት /EIU  / እንደተነበየው  አፍሪካ በ2024 በምጣኔ ሀብት ረገድ ከእስያ ቀጥሎ ሁለተኛዋ ፈጣን አዳጊ አህጉር ትሆናለች።ይህም በአገልግሎት ዘርፍ የሚመራ ሲሆን  በምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ሚና መጫወቱን ይቀጥላል።
ሆኖም እንደ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና በግጭት የምትታመሰው ሱዳንን ጨምሮ አንዳንድ አገሮች ከዚህ ተጠቃሚ ላይሆኑ ይችላሉ ሲሉ አሌክስ ቫይንስ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም በአህጉሪቱ ከፍተኛ ጫና ያሳደረው የዋጋ ንረት መሻሻል ሊያሳይ ይችላል። ነገር ግን አንጎላን፣ ናይጄሪያን ፣ ዚምባብዌን ፣ በሞዛምቢክ እና ከፍተኛ የዕዳ ጫና ያለባትን ኢትዮጵያን ጨምሮ የበርካታ አገራት ስጋት ሆኖ ይቀጥላል። 

ሞዛቢካውያን ገዥውን ፓርቲ በመቃወም ያደረጉት ሰልፍ ምስል፦ Bernardo Jequete/DW

በሞዛምቢክ ፤ አፍሪካ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መርሃ ግብሮች አንዱ የሆነው የቶታል ኢነርጂ ጋዝ ፕሮጀክት እንደገና መጀመሩ አበረታች ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ዕዳን መልሶ የማዋቀር  እና የዕዳ ስረዛ  በ2024 ዓ/ም በአፍሪካ ትልቅ ጉዳይ እንደሚሆን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።.

ጂኦፖለቲካዊ ተግዳሮቶች
እንደ ፍሬድሰን ጊሌንጌ የሩስያ እና የቻይና ሁኔታ የአፍሪካ አገራትን በማጠናከር ረገድ እና በዲሞክራሲ ላይም ተጽዕኖ አለው። ከዚህም ባሻገር የምዕራቡን ዓለም የበላይነት ለመግታት  እና በአህጉሪቱ ላይ ኃያላኑ  የበለጠ ተፅዕኖ ለመፍጠር እየተፎካከሩ ነው። ጊሌንጌ እንደሚሉት ይህ ትግል ዴሞክራሲን አደጋ ላይ ይጥላል።

በፕሪቶሪያ የሚገኘው የዓለም አቀፍ የደህንነት ጥናት ተቋም/ISS/  ተንታኝ ፕሪያል ሲንግ እንደሚሉት በዋና ዋና ዓለም አቀፍ ሀይሎች መካከል  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚሄደው ተለዋዋጭ ጂኦፖለቲካዊ ፉክክር አንፃር መጪው ዓመት ለአፍሪቃ ጥሩ አይመስልም።
«በአሁን ባለው ሁኔታ መጪው አመት ለአፍሪካ  ጥሩ አይመስልም።በተለይም በታላላቅ ዓለም አቀፍ ሀይሎች መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚሄደው ተለዋዋጭ ዓለም አቀፍ ጂኦፖለቲካል ፉክክር አንፃር። በአብዛኛው የዓለም ትኩረት በዋናነት  በመካከለኛው ምሥራቅ እና በዩክሬን እየሆነ ባለው ነገር እንዲሁም፤ በታላላቅ ኃይሎች መካከል ባለው ሰፊ የፖለቲካ ፉክክር ላይ ነው።እናም የአፍሪካ ግጭቶች በቂ ትኩረት አያገኙም። በሱዳን እና በዲሞክራቲክ ኮንጎ  ግጭቶች እንዳየነው፤ ለእነዚህ ግጭቶች በቂ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የለም ብዬ አምናለሁ።»

ፀሐይ ጫኔ/ማርቲና ሽዋኮቭስኪ 
ሽዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW