1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አፍሪቃ፦ የጋቡን መፈንቅለ መንግሥት ሌሎችን ሥጋት ላይ ጥሏል

ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 4 2015

የጋቡን ወታደራዊ ሁንታ መፈንቅለ መንግሥት በሌሎ የአፍሪቃ ሃገራትም ሥጋት አጥልቷል ። በሥልጣን ላይ ለዘመናት የቆዩ መሪዎች የደኅንነት እና ወታደራዊ ኃላፊዎቻቸው ላይ አፋጣኝ ሹም ሽር አድርገዋል ።

ጋቦን፤ ፖርት ጌንቲል፤ የመፈንቅለመንግሥት ደጋፊዎች
ጋቦን፤ ፖርት ጌንቲል፤ የመፈንቅለ መንግሥት ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ባንዲራ ይዘው ሲፎክሩ ይታያሉ ። ከዓሊ ቦንጎ ኦንዲምባ የተሻለ መንግሥትም ይመኛሉ ።ምስል REUTERS

በጋቡን ወታደራዊ ሁንታ ሰሞኑን ያካኼደው ሥዒረ መንግሥት በአኅጉሪቱ ሥጋት እንዲያጠላ አድርጓል ። በመዓከላዊ አፍሪቃዊቷ ሀገር ጦር ሠራዊቱ ሥልጣኑን መቆጣጠሩ በአኅጉሪቱ ሌሎች ቦታዎችም ለዘመናት መንበረ ሥልጣን ላይ የቆዩ መሪዎች ተመሳሳይ እጣ እንዳይደርስባቸው አስግቷል ።

በኒዠር ከሦስት ዓመት በፊት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡት ፕሬዚደንት ሞሐመድ ባዞምን ወታደራዊ ኹንታው  ከሥልጣን ካስወገደ አንድ ወር ግድም በኋላ ጋቡን ውስጥም ተመሳሳይ መፈንቅለ መንግሥት መከሰቱበቀጣናው ብሎም በአኅጉሪቱ ሌሎች አካባቢዎችም አለመረጋጋት እንዲሰፍን አድርጓል ።

ጋቦን ውስጥ ከፕሬዚደንታዊ ምርጫውአራት ቀናት በኋላ ወታደሮች የሀገሪቱ የቀድሞ መሪ ፕሬዚደንት ዓሊ ቦንጎ ኦንዲምባን ከሥልጣን አስወግደዋል ። ፕሬዚደንቱ በጋቦን ለ14 ዓመታት መንበረ ሥልጣኑ ላይ ቆይተው ነበር ። ከሳቸው በፊት አባታቸው ዖማር ቦንጎ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ1967 ህይወታቸው እስካለፈበት 2009 ድረስ ከዐርባ ዓመታት በላይ ሥልጣኑን ለብቻቸው ተቆጣጥረው ቆይተዋል ። 

የካሜሩን ፕሬዚደንት የ90 ዓመቱ ፖል ቢያ አሁንም በሥልጣን ላይ ነው ያሉት ።ምስል Jemal Countess/UPI/newscom/picture alliance

ጎረቤት ካሜሩን ተመሳሳይ የመፈንቅለ መንግሥት ሥጋት አጥልቶባታል ። ከዐርባ ዓመታት በላይ በሥልጣን ላይ የቆዩት የ90 ዓመቱ የካሜሩን ፕሬዚደንት ፖል ቢያ የጋቦን መፈንቅለ መንግሥት እንደተሰማ የጦር ሠራዊታቸው ላይ የአመራር ለውጥ ወዲያው ነበር ያደረጉት ። ጋቦንእና ካሜሩንን ጎን ለጎን መመልከት ይከብዳል ያሉት የፖለቲካ ተንታኙ አሌክስ ጉስታቭ ናቸው ።

«እንደ እኔ ያሉ ካሜሩናውያን ጋቡን ውስጥ የሚከናወነውን ያለ አንዳች ብዥታ እጅግ በትኩረት እየተከታተልን ነው ። በሁሉም ጎራ የተሰለፉ የካሜሩን ዴሞክራሲ አቀንቃኞች ጦሩ የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ እንዳይገባ ይከላከላሉ ብለን እናምናለን ።»

የሩዋንዳው ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜም ቢሆኑ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2003 ጀምሮ በሥልጣን ላይ ናቸው ። እሳቸውም ከሳምንት በፊት ከፍተኛ ማእረግ የተሰጣቸው ወታደሮችን በጡረታ አሰናብተዋል ። ጋቦን ውስጥ መፈንቅለ መንግሥቱ ከተፈጸመ አፍታም ሳይቆይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በሥልጣን ላይ የሚገኙት የጊኒ-ቢሳውፕሬዚደንት ዑማሮ ሲሶኮ ኤምባሎ የደኅንነት ጥበቃ አማካሪዎች በሚል ሁለት አዳዲስ ቦታዎች ላይ ሰዎችን ሹመዋል ።

በፒትስበርግ ዩኒቨርሲቲ የካርኔጊ የደኅንነት እና ቴክኖሎጂ ተቋም ተመራማሪው ጆን ቺን መፈንቅለ መንግስት በሚደጋገምባት አፍሪቃ  አንዳቸውም ከሌላኛው አይሻሉም ሲሉ በብርቱ ይተቻሉ ።

«ወደ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ በፍጥነት እንመለሳለን ሲሉ ቃል የገቡ ያን ቃላቸውን አላሟሉም ። ስለዚህ በእነዚህ ሃገራት ውስጥ ወደ ዴሞክራሲ የተሳካ ሽግግር ዐላየንም ።»

በኒዠር የመፈንቅለ መንግሥት ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተው ይታያሉ ። ይህ ሠልፍ ሐምሌ ወር ውስጥ የተነሳ ነው ። ምስል Mahamadou Hamidou/REUTERS

እንደ ጆን ቺን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2007 እስከ 2018 ባሉት 11 ዓመታት በአፍሪቃ አኅጉር አንዳችም መፈንቅለ መንግሥት አልተመዘገበም ። ከ2020 እስከ 2022 ግን የመፈንቅለ መንግስት ድርጊቱ ዐሥራ አንድ ጊዜ ተከስቷል። አሁን በቅርቡ ደግሞ በኒዤርእና ጋቦን የተከሰቱትን ጨምሮ የመፈንቅለ መንግሥታቱ ቁጥር 13 ደርሷል ። አብዛኞቹ መፈንቅለ መንግሥታት የተከሰቱት ደግሞ ምዕራብ አፍሪቃ ውስጥ ባሉ ሃገራት ነው ። ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ብቻ አፍሪቃ ውስጥ ስድስት ፈንቅለ መንግሥታት ታይተዋል ። ሁለቱ ማሊ ውስጥ፤ ሁለቱ ቡርኪና ፋሶ እንዲሁም አንድ በጊኒ እና በኒዤር የተከሰቱ ናቸው ። 

ተመራማሪው ጆን ቺን እንደሚሉት፦ በጋቦን የተከሰተው መፈንቅለ መንግሥት በአኅጉሪቱ የመጨረሻው አይደለም ። በሌሎች ያ,,ፍሪቃ ሃገራት፦ «የመፈንቅለ መንግሥታት እንቅስቃሴዎችን ዕናያለን» ሲሉም ግምታቸውን አኑረዋል ።  

ማርቲና ሽቪኮብስኪ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW