1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ለአንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ መሆን ለምን በቂ አልሆነም?

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 2016

በጎርጎሪዮሳዊው 1950 በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ወጥተው ሉዓላዊነታቸውን አግኝተዋል። ደቡብ ሱዳን፤ ኤርትራና ናሚቢያ ከአፍሪቃ ሃገራት ተጽዕኖ ተላቀው ነጻ መንግሥታት ሆነዋል። እንዲያም ሆኖ ግን የአፍሪቃ ሃገራት ነጻ መንግሥታት መሆን የኤኮኖሚም ብልጽግናም ሆነ የአካባቢ መረጋጋትን ሊያመጣ እንዳልቻለ ነው ተንታኞች የሚገልጹት።

የአፍሪቃ ሃገራት ሰንደቅ አላማ
የአፍሪቃ ሃገራት ሰንደቅ አላማ ፎቶ ከማኅደርምስል Nicolas Maeterlinck/Belga/imago images

የአፍሪቃ ሃገራት ይዞታ

This browser does not support the audio element.

 

የአፍሪቃ ሃገራት ምንም እንኳን ዛሬ ከቅኝ ግዛትነት ተላቀናል ቢሉም በተግባር ግን ሙሉ ለሙሉ ነጻነት እንዳላቸው ማረጋገጥ እንደማይቻል ነው ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው፤ የጸጥታ ጉዳይ ባለሙያው ዶክተር ጀስት ኮጆ የተናገሩት። ጋናዊው የፖለቲካ ተንታኝ ፊደል አማካየ ኦውሱ እንደሚሉት ግን የአፍሪቃውያን ነጻነት ግዛታቸውን ተቆጣጥሮት እንደቆየው እንደቅኝ ገዢው ኃይል ይለያያል። ለምሳሌ ናሚቢያ ነጻነቷን ያገኘችበት ሁኔታ ከደቡብ ሱዳን ነጻ ሀገር የመሆን ሂደት በጣም ይለያል።

የደቡብ ሱዳን ተግዳሮቶች

በቅርቡ ነጻነቷን ያገኘችው የአፍሪቃ ለጋ መንግሥት ደቡብ ሱዳን፤ ነጻነቷን ያወጀችበትን 13ኛ ዓመት ከሁለት ሳምንታት በፊት ዘክራለች። በዚህ አጭር ጊዜም እጅግ የከፋ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ያለፈች ሲሆን የፖለቲካው አለመረጋጋት ያስከተለው ረሀብ መከሰቱን የተመድ ይፋ አድርጓል። የደቡብ ሱዳን ቀውስ ዘርፈ ብዙ ምንጮች እንዳሉት የሚገልጹት የደቡብ ሱዳን ዓለም አቀፍ ልማት ተመራማሪ ጀምስ ቦቦያ ከምንም በላይ ለእርስ በእርስ ግጭቱ ማግለል፣ የነጻነት ማጣት እና የልማት አለመኖር መሠረታዊ መንስኤዎች ናቸው። ጁባ ከኻርቱም የወረሰችው ሥርዓተ አልበኝነት፤ ሙስና፣ የአገልግሎት እጦት እና ሀብትን በአግባቡ የማስተዳደር ጉድለትም ችግሩን ማባባሱንም ያስረዳሉ።

የመሪነት እና የአስተዳደር ሚና

ነጻነታቸውን አውጀው በራሳቸው አስተዳደር በሚኖሩየአፍሪቃ ሃገራት ውስጥ በአብዛኛው መሪዎች ከብሔራዊ ልማት ይልቅ የግል ሥልጣናቸውን ስለሚያስቀድሙ ድህነትን፣ ግጭትንና በልማት ኋላቀርነት በክፍለ ዓለሙ እያስፋፉ ነው የሚሉት ካሜሮናዊው የፖለቲካ ኤኮኖሚ ተንታኝ ኪንግስሌይ ሸቱህ ኖሀ ናቸው። እንዲህ ባለው አውድ ደግሞ መሪነት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ባይ ናቸው።

«የፖለቲካ መሪነት ከቅኝ ግዛት ማግስት በአፍሪቃ በሁለት ወገን የሚቆርጥ ጎራዴ ዓይነት ነው የሆነው። በአንድ በኩል እንደ ኔልሰን ማንዴላ፣ ጁሊየስ ኜሬሬ እና ኩዋኔ ኑኩርማ ማኅበራዊ ልማት እና የኤኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን ብሔራዊ አንድነትን ለማሳደግ ወሳኝ ሚናዎችን ተጫውተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ሙስና የተንሰራፋበት ደካማ አስተዳደር፤ ንቅዘት እና አምባገነንነት ለበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ውድቀት ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል።»

በኬንያ ከተካሄደው ሕዝባዊ ተቃውሞ በከፊልፎቶ ከማኅደርምስል Thomas Mukoya/REUTERS

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ጀምስ ቦቦያም የመሪነት ሚና አፍሪቃ ውስጥ ቀጣይ ተግዳሮት ሆኖ ይዘልቃል ባይናቸው።

«ሁኔታዎችን መጠቀሚያ ያደረጉ በርካታ የጦር አበጋዞች፤ እንዲሁም የፖለቲካ መሪዎች ነበሩ፤ እንዲህ ያሉት እንደውም በደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ውስጥ አመጽን ማበረታታት ጀመሩ። ከዚያም ያ  ተሳካላቸው እና ነጻነት ከተገኘ በኋላ ሁሉም ተናደ።»

ውጪያዊ ምክንያቶች እና ኒዮኮሎኒያሊዝም

ያለፈው የአፍሪቃ ታሪክ ለአሁኑ ወቅታዊ ሁኔታና የተለያዩ በርካታ ሃገራትም ትርጉም ያለው እድገት የማሳየት አቅም ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ተንታኞቹ እንደሚሉትም ችግሩ ሃገራቱ ነጻነታቸውን ካገኙበት ጊዜ ይጀምራል። ለምሳሌም ብሪታኒያ ለደቡብ አፍሪቃ ነጻነቷን የመለሰችበት መንገድ ምዕራብ አፍሪቃ ላይ ከተከተለችው አካሄድ ይለያል። ፖርቱጋልን  ያኔ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው ግፊት የቅኝ ግዛቶቿ ነጻነታቸውን እንዲጎናጸፉ ጫና አድርጓል። በወቅቱ ፖርቱጋል ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ በዋና ምክንያትነት ይነሳል።  

ማዕከላዊ አፍሪቃ የብዙሃኑ ማኅበረሰብ የኑሮ ገጽታፎቶ ከማኅደር ምስል Alexis Huguet/AFP/Getty Images

ወቅታዊው በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራትየሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሰክን አንዳቸው ከሌላቸው ተሞክሮ ለመማር ግድ እንደሚላቸውም ነው ተንታኞቹ ያመለከቱት። በውስጥ ግጭት ጦርነት የሚታመሱ የአፍሪቃ ሃገራት የዘር ፍጅትን ያህል ወንጀል ተሻግራ አሁን የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ከምትገኘው ሩዋንዳ ሊወስዱ የሚችሉት ነገር አለ። ሌላው ቀርቶ መንገዶቿና ጽዳቷ ሩዋንዳን ለምሳሌነት ያበቃታል ባይ ናቸው። እርሻን በሚመለከት ደግሞ ዩጋንዳ ልታበረክት የምትችለው አርአያነት አለ። ሕዝቡን በማክበርና ለጥያቄውም ጆሮ መስጠትንም ባሕር ሳይሻገሩ ከኬንያ መቅሰም እንደሚቻል ነው ቦባያ ያመለከቱት። የአፍሪቃ ሃገራትን ግን ችግራቸው ግጭት ብቻም አይደለም። ባለፈው ወር ነጻነቷን ከተቀዳጀች 60 ዓመታት ያስቆጠረችው ማላዊ ግጭት የለባትም። ግን ደግሞ ከዓለም አራተኛዋ ድሀ ሀገር መሆኗን የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገው መረጃ ያሳያል። ስድስት አስርት ዓመታት ያስቆጠረው የነጻነት ቀን ሲታሰብ ሀገሬው ያን ያህል በድምቀት አላከበረውም። ሥራ አጥነት እና ስር የሰደደው ድህነት የኅብረተሰቡን ቀልብ ወስዶታል።

ምንም እንኳን የበርካታ አፍሪቃ ሃገራት ወቅታዊ ይዞታ በፈተናዎች የተሞላ ቢሆንም ቦቦያ ተስፋ ላለመቁረጥ አዎንታዊ ነገሮች አሉ ነው የሚሉት። እንደ እሳቸው እምነትም ኬንያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት ወጣቶች የመሪነቱን ሀላፊነት ለመያዝ መንቀሳቀስ ጀምረዋል። አዎንታዊውን ተስፋ የሚጋሩት ኖሀም፤ በበኩላቸው በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት የተሻለ ቀን እንዲመጣ አዙሪቱ ያለቀቀው ሙስና፣ ድህነት እና የፖለቲካ አለመረጋጋት መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ይላሉ።

ሸዋዬ ለገሠ / ሚሚ ማፎ ታካምቡ 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW