አፍሪካን የሚያሰጋው ዳግም ቅኝ ግዛት
ረቡዕ፣ ጥቅምት 9 2015
አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግሮች በራሳቸው የመፍታት ልምድን እንዲዳብሩ አንድ ታዋቂ ምሁር አሳሰቡ። ኬንያዊ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ «አፍሪካውያን ችግሮቻቸው በሌሎች እንዲፈቱላቸው የሚፈቅዱ ከሆነ ለዳግም ቅኝ ግዛት ራሳቸውን አሳልፈው እየሰጡ እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል» ብለዋል። አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎችም ሥልጣንን እንደ እርስትና ውርስ ከመቁጠር ተላቅቀው ለተተኪ ትውልድ ማስተላለፍ የሚያስችል ሥርዓትና አሰራር ሊዘረጉ እንደሚገባም አመልክተዋል።
በባሕር ዳር በተካሄደው 10ኛው የጣና ፎረም ከተለያዩ አገሮች የተጋበዙ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ተመራማሪዎችና የአገር መሪዎች ተሳትፈውበታል። በመድረኩ ከታደሙ ምሁራን መካከል በፓን አፍሪካ አቀንቃኝነታቸውና በአነቃቂ ንግግራቸው የሚታወቁት ኬንያዊ ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሎች ኦቴኖ ሉሙምባ አንዱ ናቸው። ፕሮፌሰር ሉሙምባ አፍሪካ በርካታ ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉባት አመልክታዋል፣ ምክንቶቹን ዘርዝረዋል።
«በአፍሪካ ለሚነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች በርካታ ምክንያቶች አሉ፣ የሥልጣን ሽኩቻ በስፋት ይታያል። የአፍሪካ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ለውጪ ሃገራት የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ምንጭ መሆኑ የሰላም እጦት መነሻ ነው፣ ይህ በፍፁም ሊካድ አይችልም፣ ግለሰቦችና ቡድኖች ሀብቱን ለመቀራመት በሚያደርጉት ሩጫ የሚፈጠሩ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ለአህጉሪቱ የሰላም እጦት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ችግሮቹን ለማስወገድነና ለመፍታት እኛ አፍሪካውያን ጊዜ ሰጥተን ልንወያይባቸው ይገባል፣ በአውሮፓና በሌሎች አገሮች በርካታ ተቋማት የአፍሪካን ችግሮች ለመፍታት ተቋቁመዋል። ግን ጠብ ያለ ነገር የለም፣ አሁን ጊዜው ራሳችን ተወያይተን ራሳችን መፍትሄ የምናመጣበት ነው።»
አፍሪካ ችግሮቿን ልትፈታባቸው የምትችልባቸው በርካታ ተቋማት ቢኖራትም፣ የሀሳብ አንድነት አለመኖርና አንድ ቋንቋ መናገር አለመቻል ለበአዳን የቅኝ ተገዥነት እያጋለጠን ነው፣ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባለም ነው ያሉት።በባሕር ዳር የተካሔደው ጣና ፎረም ተጠናቀቀ
«እኛ አፍሪካውያን የተቋማት ችግሮች የሉብንም፣ የአፍሪካ ህብረት(OAU)፣ የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ማህበረሰብ (ECOWAS) የደቡባዊ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (SADC) የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (EAC)፣ የመካከለኛው አፍሪካ ኢኮኖሚክ ማህበረሰብ (ECCAS)፣ ማግሬብ) አሉን፤ እነዚህ ተቋማት አንድ ድምፅ ማሰማት፣ አንድ ቋንቋ መናገር አለባቸው፣ ሁሌም ማስታወስ ያለብን አዲስ የቅኝ ግዛት እሳቤ እንዳለ ነው፣ አፍሪካን እንደገና የመቀራመት ፍላጎትና ምኞት አለ፣ ካልተጠነቀቅን አሁንም አፍሪካ በውጭ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መውደቋ አይቀርም።»
በአፍሪካ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ እንዲሻሻል ጣና ፎረም ለ10 ጊዜ ያክል ውይይት ቢያደርግም የአህጉሯ የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ ብዙም መሻሻል ሳያሳይ ግጭቶች፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ከምርጫ ጋር የተያያዙ ችግሮች ለአህጉሪቱ ፈተና እየሆኑ ነው። ይህ ለምን ሆነ ተብለው በዶይቼ ቬሌ የተጠየቁት ምሁሩ፣ አስከፊው ነገር እሱ ነው ግን ተስፋ መቁረጥ አያሻም ብለዋል።
«ይህ ነው ዋናው ችግር፣ የ2020 የአፍሪካ ህብረት መሪ ቃል «ጥይት የማይሰማበት ዓመት» የሚል ነበር። ግን አሁን የጥይት ድምፅ በአህጉሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚደመጥበት ጊዜ ነው፣ ተስፋ መቁረጥ ግን አይገባም፣ የህመምህን ምክንያት አውቀህ ስትታከም፣ ሌላ ህመም ሊመጠብህ ይችላል፣የሆነ ሆኖ በምንም መልኩም ቢሆን በአፍሪካ ሰላም ለማምጣት የምናደርገውን ትግል ተስፋ ሳንቆርጥ መቀጠል ይኖርብናል።»የጣና መድረክና አፍሪቃ
ፕሮፌሰር ሉሙምባ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች ሥልጣንን ውርስና ቅርስ ከማድረግ ተቆጥበው ለአገራቸውና ለአህጉራቸው የሚበጅ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሊያመጣ የሚችል እቅድና አሰራር ሊኖራቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
«እኔ ሁሌም አቋሜ የአፍሪካ መሪ ምንም ያክል ዴሞክራቲክም ይሁን ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ይኑረው፣ ለሌሎች ዕድል መስጠት የሚያስችል የሥልጣን የሽግግር ስርዓት ሊቀይስ ይገባል። ማንም ቢሆን በሥልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ ሊቀመጥ አይገባውም፣ ለሚመራት አገርና ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ሲል ወንበሩን መልቀቅ ይገባዋል።»
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ