1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“አፍሪካ የሚወነጨፍ ዕድገት ያስፈልጋታል” የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪንዉሚ አዲሺና

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ የካቲት 13 2016

የአፍሪካ ልማት ባንክ በ2024 የአኅጉሪቱ ምጣኔ ሐብት በ3.2% እንደሚያድግ የተነበየበትን ሪፖርት በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል። የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪንዉሚ አዲሺና “አፍሪካ የሚወነጨፍ ዕድገት ያስፈልጋታል” የሚል አቋም አላቸው። የአፍሪካ ኤኮኖሚ በዋጋ ግሽበት፣ የመንግሥታት የበጀት ጉድለት እና በዕዳ ክፍያ መጨመር የታጀበ ነው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ የአኅጉሪቱ ምጣኔ ሐብት በተያዘው ዓመት በ3.2 በመቶ እንደሚያድግ የተነበየበትን ሪፖርት በአዲስ አበባ ይፋ ሲያደርግ
የአፍሪካ ልማት ባንክ የአኅጉሪቱ ምጣኔ ሐብት በተያዘው ዓመት በ3.2 በመቶ እንደሚያድግ የተነበየበትን ሪፖርት ባለፈው ሣምንት በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።ምስል Tolani Alli/AfDB Group

የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት በተያዘው ዓመት የአፍሪካ ኤኮኖሚ በ3.2 በመቶ እንደሚያድግ ይተነብያል

This browser does not support the audio element.

በጎርጎሮሳዊው 2024 የኢትዮጵያ ምጣኔ-ሐብት በ6.7 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የአፍሪካ ልማት ባንክ ተንብይዋል። የባንኩ ትንበያ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ከሚጠብቀው 7.9 በመቶ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ዝቅ ያለ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2024 የአፍሪካ ኤኮኖሚ በ3.2 በመቶ እንደሚያድግ የአፍሪካ ልማት ባንክ የካቲት 8 ቀን 2016 በአዲስ አበባ ይፋ ያደረገው ሪፖርት ያሳያል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት ዶክተር አኪንዉሚ አዲሺና “የኤኮኖሚ ዕድገት መዳከም፣ የዓለም የፋይናንስ አቅርቦት ሁኔታዎች መጥበቅ፣ ያለ ወለድ የሚሰጥ ብድር ማነስ፣ እየጨመረ የመጣ የከባቢ አየር ለውጥ ተጽዕኖ፣ የወረርሽኝ ዳፋ፣ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰቱ ግጭቶች እና ጂዖ ፖለቲካዊ ውጥረት” አኅጉሩን የተፈታተኑ ተግዳሮቶች እንደሆኑ ሪፖርቱ ይፋ ሲደረግ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ “ቆንጠጥ የሚያደርግ ሆኖ ማስተካከል ይጠይቃል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሪፖርቱን በአዲስ አበባ ያብራሩት የአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝደንት እና ዋና ኤኮኖሚስት ፕሮፌሰር ኬቪን ኡራማ “አፍሪካ አሁንም በዓለም ሁለተኛው ፈጣን ኤኮኖሚ ሆኖ ቀጥሏል። ይኸ ብቻ ሳይሆን በአኅጉሩ አስራ አንድ ሀገሮች በ2025 በዓለም በፍጥነት ከሚያድጉ 20 ኤኮኖሚዎች መካከል ይሆናሉ” ሲሉ ተናግረዋል።

በአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት “ጠንካራ ምጣኔ ሐብታዊ አፈጻጸም” ይኖራቸዋል ከተባሉት መካከል ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ ይገኙበታል። ኒጀር በ11.2 በመቶ ከፍተኛው ኤኮኖሚያዊ ዕድገት ይኖራታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ሴኔጋል፣ ሊቢያ፣ ርዋንዳ፣ ኮት ዲቯር፣ ቤኒን፣ ታንዛኒያ፣ ቶጎ እና ዩጋንዳ በዝርዝሩ ተካተዋል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ከመካሔዱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው። ምስል MICHELE SPATARI/AFP

የዋጋ ግሽበት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በአፍሪካ ጭማሪ እያሳየ ሲሆን ብርታቱ የአኅጉሩን ማክሮ ኤኮኖሚያዊ መረጋጋት እንደሚያሰጋ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ይጠቁማል። ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የታየው ኢትዮጵያ በምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ሲሆን ባለፈው ዓመት 30.6 በመቶ ደርሶ ነበር።

“የዋጋ ግሽበት በ3.7 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። በ2022 በአማካይ 14.1 በመቶ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ከ17 በመቶ በላይ ሆኗል” ያሉት የባንኩ ዋና ኤኮኖሚስት ፕሮፌሰር ኬቭን ኡራማ የምግብ ሸቀጦች እና የኃይል ዋጋ ጭማሪ ዋንኛ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል። በበርካታ ግዙፍ የአፍሪካ ኤኮኖሚዎች ለታየው የዋጋ ግሽበት “የዕዳ መጨመር፣ የግብርና ውጤቶች አቅርቦት እጥረት እና በመገበያያ ገንዘቦች መዳከም ሳቢያ ከውጭ የሚገባ የዋጋ ንረት” ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች ናቸው።

የአፍሪካ መንግሥታት ዕዳ የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም የኮቪድ ወረርሽኝ ከመቀስቀሱ በፊት ከነበረበት አኳያ ሲወዳደር አሁንም ከፍተኛ ነው። በአስራ ሁለት ሀገራት የመንግሥት የዕዳ መጠን በጎርጎሮሳዊው 2023 የኮቪድ ወረርሽኝ ከመቀስቀሱ በፊት ከነበረበት ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን የመሰሉ ሀገራት የብድር ክፍያ ማሻቀብ እና ያስከተለው የዕዳ ጫና አፍሪካን የሚፈታተን ሁነኛ ችግር ነው። እስከ ጎርጎሮሳዊው ሕዳር 2023 የዕዳ ክፍያ በመጨመሩ ምክንያት 21 የአፍሪካ ሀገራት የዕዳ ጫና ውስጥ የመውደቅ ሥጋት እንደተጫናቸው አሊያም እንደገቡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት ያሳያል።

በሪፖርቱ መሠረት በጎርጎሮሳዊው ከ2015 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ከመንግሥት ገቢ 6.8 በመቶ የነበረው አማካይ የዕዳ ክፍያ ከ2020 እስከ 2022 ባሉት ዓመታት ወደ 10.6 በመቶ አሻቅቧል። ይኸ የዕዳ ክፍያ ማሻቀብ መንግሥታት እንደ ትምህርት እና ጤና ላሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች በቂ መዋዕለ-ንዋይ እንዳይኖራቸው አድርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 32 በመቶ ድርሻ የነበረው የውጭ ዕዳ በአምስት ዓመታት ገደማ ውስጥ ወደ 17 በመቶ ዝቅ እንዳለ ተናግረዋል። ምስል Eshete Bekele/DW

“አፍሪካ የከሰረ ኤኮኖሚ አይደለም። አሁን በምናየው የገንዘብ እጥረት ሊቸገር የሚገባው አኅጉር አልነበረም” የሚሉት የደቡብ አፍሪካው ኬፕ ታውን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር አበበ ሽመልስ በአፍሪካውያን የኤኮኖሚ አስተዳደር ችግር እና በዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት አሠራር ምክንያት የዕዳ ክፍያ ማሻቀቡን ገልጸዋል። ፕሮፌሰር አበበ እንደሚሉት “ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት የተበጀበት እና የሚሠራበት መንገድ የአፍሪካን ጥቅም የሚያስጠብቅ አይደለም።”

የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርት በ2023 የሳዖ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ፣ አንጎላ እና ኢትዮጵያ የዕዳ መጠናቸው በከፍተኛ ደረጃ እንደሚቀንስ የሚተነብይ ነው። በሠነዱ መሰረት የኢትዮጵያ ዕዳ በ17.9 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን “ከፍተኛ የአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን (GDP) ዕድገት” በምክንያትነት ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የምርት መጠን 32 በመቶ ድርሻ የነበረው የውጭ ዕዳ በአምስት ዓመታት ገደማ ውስጥ ወደ 17 በመቶ ዝቅ እንዳለ ተናግረዋል። የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ቋት ለተገዳደረው የዕዳ ክፍያ ማሻቀብ መፍትሔ ፍለጋ የኢትዮጵያ መንግሥት በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የተራዘመ ድርድር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዕዳ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ያለው ድርሻ ከሌሎች ሀገሮች አኳያ “በጣም አነስተኛ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር አበበ “ነገር ግን መበደር የሚያስከፍለው ዋጋ እና ተበድረን በሠራንው ያገኘንው ትርፍ እንዳለመታደል ሆኖ አልተጣጣመም” ሲሉ ተናግረዋል።

ከ10 በመቶ በላይ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት የነበራት ኢትዮጵያ “መልሳ ልታገግም እና የመዋዕለ ንዋይ ፍላጎቷን ለማሳካት ከፍተኛ መጠን ያለው ዕዳ ለመሸከም ትችላለች” የሚሉት ፕሮፌሰር አበበ “ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ተስማሚ ቢሆን ኖሮ ሀገሪቱ ራሷን መቀየር ትችል ነበር” ሲሉ ይሞግታሉ። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው “ደሀ ሀገሮችን 9 በመቶ ወለድ ማስከፈል ጥቅሙ ምንድነው?” ሲሉ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት የሚከተለውን አሠራር ተገቢነት ያጠይቃሉ።

አፍሪካ “የረዥም ጊዜ ልማት እና በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር ላይ የተመሠረት የፋይናንስ ስትራቴጂ” እንደሚያስፈልጋት በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የዘላቂ ልማት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ ተናግረዋል። ምስል GIZ/Photothek

በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የዘላቂ ልማት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት አፍሪካን የሚያስከፍለውን የወለድ መጠን ከቅጣት ያመሳስሉታል። ሳክስ የአፍሪካ ሀገራት ቦንድ በዓለም ገበያ ሸጠው የሚበደሩበትን ሥርዓት “ወጥመድ” ሲሉ ገልጸውታል። አሜሪካዊው የምጣኔ ሐብት ባለሙያ እና የፖሊሲ ተንታኝ አፍሪካ ሥር ከሰደደ ድህነት ለመላቀቅ በዓመት ቢያንስ ሰባት በመቶ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት በዘላቂነት ሊኖራት ይገባል የሚል አቋም አላቸው።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ሪፖርቱን በአዲስ አበባ ይፋ ሲያደርግ ሳክስ “የረዥም ጊዜ ልማት በአጭር ጊዜ ብድር” ሊሳካ አይችልም ሲሉ ተደምጠዋል። “የረዥም ጊዜ ልማት እና በረዥም ጊዜ የሚከፈል ብድር ላይ የተመሠረት የፋይናንስ ስትራቴጂ ያስፈልገናል” የሚሉት ፕሮፌሰር ሳክስ የአፍሪካ መንግሥታት በአብዛኛው በውጭ ምንዛሪ የሚበደሩ በመሆናቸው ዕዳ ጎምርቶ ተመልሶ የሚከፈልበት ጊዜ ጉዳይ ቁልፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

 ኢትዮጵያ ለካፒታል ገበያ አገልግሎት አቅራቢዎች ፈቃድ መስጠት ልትጀምር ነው

“የአጭር ጊዜ ብድር ለረዥም ጊዜ ልማት በጣም አደገኛ ነው” የሚሉት የምጣኔ ሐብት ባለሙያው የአፍሪካ ዕድገት ሰባት በመቶ ሆኖ በዘላቂነት መቀጠል ከቻለ የኤኮኖሚው አቅም እንደሚፈረጥም አስረድተዋል። “አሁን ብዙ የሚመስለው ዕዳ ወደፊት ያን ያክል ትልቅ አይሆንም። አፍሪካ ባላት በፍጥነት የማደግ ዕድል ምክንያት ብዙ ዕዳ መሸከም ትችላለች” የሚሉት ሳክስ “ነገር ግን ዕዳው በሰባት እና በአስር ዓመታት የሚከፈል ከሆነ እና ዕድገቱ በአንጻሩ ከ30 እስከ 40 ዓመታት ከፈለገ አሁን ያለው አይነት ችግር መከሰቱ አይቀርም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፕሮፌሰር አበበ ሽመልስም ይሁኑ ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ በዓለም ባንክ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሚመራው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሥርዓት ለአፍሪካ የሚበጅ ሆኖ ሊሻሻል እንደሚገባ ይስማማሉ። ይኸ ብቻውን ግን በቂ አይደለም። የአፍሪካ ልማት ባንክን አቅም ማሳደግ፣ የአኅጉሪቱን ሀገራት የበለጠ ማስተሳሰር፣ ኃይል እና ማጓጓዣ የመሳሰሉ መሠረተ-ልማቶች ማሳደግ ፕሮፌሰር ሳክስ ካቀረቧቸው ጥቆማዎች መካከል ይገኙበታል።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪንዉሚ አዲሺና “አፍሪካ የሚወነጨፍ ዕድገት ያስፈልጋታል” የሚል አቋም አላቸው።ምስል DW

የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪንዉሚ አዲሺና “አፍሪካ የሚወነጨፍ ዕድገት ያስፈልጋታል” የሚል አቋም አላቸው። “ቢያንስ ለአስር እና አስራ አምስት ዓመታት አፍሪካ ቢያንስ በእጥፍ በወጥነት ማደግ ይኖርባታል” ያሉት አዲሺና ቁጥር ብቻውን ግን በቂ እንዳልሆነ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ለመተካት ዝግጁ ነች?

አዲሺና “የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብን ለማጠናከር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ በሀገር ውስጥ የካፒታል ገበያ ዕድገት ላይ የተመሠረተ ነው። እየጨመረ የመጣውን የሀገሮቻችን የወጪ ፍላጎት ለመሙላት የሀገር ውስጥ የካፒታል ገበያዎችን በማጠናከር ረገድ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል” ሲሉ ተናግረዋል።

“በመገበያያ ገንዘቦች መዳከም እየጨመረ የመጣው የበርካታ ሀገራት የዕዳ ክፍያ” ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ የጠቆሙት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት “የሀገር ውስጥ እና የውጭ ዕዳ ሚዛናዊ መሆን ያስፈልገዋል። የገጠመንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመፍታት በሀገር ውስጥ የመገበያያ ገንዘብ የመበደር ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉ መክረዋል።

የአፍሪካ ሀገራት የተፈጥሮ ሐብት አስተዳደርን በማጠናከር እና የዋጋ አተማመንን ግልጽ በማድረግ ላቅ ያለ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ ማመቻቸት እንዳለባቸው አዲሺና መክረዋል። በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ (G20's Common Framework) በኩል ለዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ የሚደረገውን ዘገምተኛ ድርድር ማፋጠን እና እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ካሉ ተቋማት የአፍሪካ ሀገራት ያላቸውን የመበደር ልዩ መብት ፍትኃዊ ማድረግ አዲሺና ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል ካሏቸው የፖሊሲ ጥቆማዎች መካከል ናቸው። አዲሺና የሚመሩት የአፍሪካ ልማት ባንክ የአኅጉሪቱ ሀገራት ፖለቲካዊ መረጋጋትን መፍጠር፣ የሕግ የበላይነትን እና የተቋማትን አቅም ማጠናከር እንደሚገባቸው ጥቆማ ሰጥቷል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW