1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢራን በእስራኤል ግጭት ለተገደሉ ወታደራዊ መኮንኖች ብሔራዊ ሥርዓተ ቀብር አካሔደች

ቅዳሜ፣ ሰኔ 21 2017

የኑክሌር ሳይንቲስቶች እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ ኢራን ከእስራኤል ባደረገችው ውጊያ የተገደሉ 60 ሰዎች ብሔራዊ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ። በሥርዓተ-ቀብሩ የተሳተፉ ኢራናውያን የሟቾችን ፎቶግራፎች ይዘው፣ መፈክር እያሰሙ የኢራንን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

ኢራን በእስራኤል ግጭት ለተገደሉ ወታደራዊ መኮንኖች ብሔራዊ ሥርዓተ ቀብር አካሔደች
ኢራን በእስራኤል ግጭት ለተገደሉ ወታደራዊ መኮንኖች ብሔራዊ ሥርዓተ ቀብር አካሔደችምስል፦ Majid Asgaripour/WANA/REUTERS

የኑክሌር ሳይንቲስቶች እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችን ጨምሮ ኢራን ከእስራኤል ባደረገችው ውጊያ የተገደሉ 60 ሰዎች ብሔራዊ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ።

በማዕከላዊ ተሒራን በተካሔደው ሥርዓተ ቀብር ፕሬዝደንት ማሱድ ፓዤሽኪያን፣ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላሕ አሊ ኻሚኒ ከፍተኛ አማካሪ ሬር አድሚራል አሊ ሻምክኻኒ እና በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ታድመዋል።

ሬር አድሚራል አሊ ሻምክኻኒ ቆስለው በከዘራ ሲንቀሳቀሱ መታየታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። ባለፈው ሐሙስ ኢራን በእስራኤል ላይ ድል መቀዳጀቷን ያወጁት አሊ ኻሚኒ ራሳቸው ግን በመርሐ-ግብሩ ላይ አልተገኙም።

በሥርዓተ-ቀብሩ የተሳተፉ ኢራናውያን የሟቾችን ፎቶግራፎች ይዘው፣ መፈክር እያሰሙ የኢራንን ሰንደቅ ዓላማ ሲያውለበልቡ ታይተዋል። ከሐዘንተኞች መካከል “ሞት ለአሜሪካ” “ሞት ለእስራኤል” የሚል መፈክር ማሰማታቸውን የኢራን ብሔራዊ ቴሌቭዥን ጣቢያ አሳይቷል።

የቀድሞው የኢራን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሞሐመድ ባግሔሪ አብረዋቸው ከተገደሉት ከባለቤታቸው እና ከጋዜጠኛ ልጃቸው ጋር እንደሚቀበሩ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የኑክሌር ሳይንቲስት የነበሩት ሞሐመድ መኸዲ ቴሕራንቺ በተመሳሳይ ሥርዓተ ቀብራቸው ከባለቤታቸው ጋር ይቀበራሉ። 

በማዕከላዊ ተሒራን በተካሔደው ሥርዓተ ቀብር ፕሬዝደንት ማሱድ ፓዤሽኪያን፣ የኢራን መንፈሳዊ መሪ አያቶላሕ አሊ ኻሚኒ ከፍተኛ አማካሪ ሬር አድሚራል አሊ ሻምክኻኒ እና በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢራናውያን ታድመዋል።ምስል፦ Majid Asgaripour/WANA/REUTERS

በውጊያው የመጀመሪያ ቀን የተገደሉት የኢራን አብዮታዊ ዘብ አዛዥ ሑሴይን ሳሊ ሥርዓተ ቀብር ነገ እሁድ ይፈጸማል።

ለ12 ቀናት በዘለቀው ግጭት እስራኤል ከ20 በላይ ከፍተኛ የኢራን ወታደራዊ መኮንኖችን እንደገደለች የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። አንዳንዶቹ የተገደሉት በመኖሪያ ቤታቸው ነበር።

የኢራን እና የእስራኤል ግጭት በዚህ ሣምንት የቆመው ዩናይትድ ስቴትስቁልፍ የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም በቀጥታ ከተሳተፈች በኋላ ነበር።

ኢራን እና እስራኤል በየፊናቸው ግጭቱን በአሸናፊነት እንደተወጡ ይገልጻሉ። በግጭቱ የተሳተፈችው አሜሪካ የኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች መውደማቸውን ገልጻለች።

ኢራን በግጭቱ ምክንያት ተዘግተው ከቆዩት መካከል የማዕከላዊ እና ምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍሎችን ሰማይ ለዓለም አቀፍ በረራዎች ዛሬ ቅዳሜ መክፈቷን የሀገሪቱ መንግሥት የሚቆጣጠረው ኑር ኒውስ ዘግቧል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW