1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢሬቻ በአዲስ አበባ ሲከበር የታሰሩ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ ተቃዋሚዎች ጠየቁ

ቅዳሜ፣ መስከረም 22 2014

ኢሬቻ ዛሬ በአዲስ አበባ ሲከበር በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እንዲፈቱ የሚጠይቁ ጥሪዎች ተሰምተዋል። በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶችና በጸጥታ አስከባሪዎች መሃል በተፈጠረ አለመግባባት መጠነኛ መረጋገጥ ተስተውሏል። በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባ እንዲፈቱ በዓሉን የታደሙ ተቃዋሚዎች ጠይቀዋል

Äthiopien | Irreechaa Feierlichkeiten der Volkdgruppe der Oromo
ምስል፦ Seyoum Getu/DW

የኢሬቻ አከባበር በአዲስ አበባ

This browser does not support the audio element.

በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ ከእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጀርባ በሚገኘው ደሎሎ ቡዴና የሆራ ስፍራ ኢሬቻ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ሲከበር አባገዳዎች እና ሃዳ ሲንቄዎች ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ታድሟል።

በባህላዊ ልብሶች ያሸበረቁ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች እና በገዳስርዓት ውስጥ ትልቁ ስፍራ የሚሰጣቸው አባገዳ፣ አባመልካ እና አባሙዳ እንዲሁም ሴት እናቶች ( ሃዳሲንቂዎች) ሆ..ያ ማሬዎ… እያሉ የኢሬቻውን ስርዓት አከናውነዋል፡፡

የኢሬቻ አከባበር በአዲስ አበባምስል፦ Seyoum Getu/DW

የቱለማ አባገዳ እና የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ዋና ጸኃፊ አባገዳ ጎበና ሆላ፣ የኦሮሞ አባገዳዎች ህብረት ሰብሳቢ እና የጉጂ አባገዳ ጂሎ መንኦ እንዲሁም ከየአከባቢው ወደ አዲስ አበባ የተጓዙ አባገዳዎች ሆራ (ወንዙን) ባርከው የምርቃት እና የመልካም ምኞች መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዘመናዊነት በተላበሱ ሳቢ ባህላዊ ልብሶች ያሸበረቁ የበዓሉ ታዳሚያንም በየፊናቸው የባህሉን ትውፊት በጠበቀ መልኩ እየጨፈሩ ወደ ሆራው ስፍራ በማቅናት በደስታ እና በአንድነት ስርዓቱን ሲከውኑ ተስተውለዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል ተሳታፊ በአዲስ አበባምስል፦ Seyoum Getu/DW

ከማለዳው 12 ሰዓት ገደማ አባገዳዎች እና ሃዳ-ሲንቂዎች ከመስቀል አደባባይ የኢሬቻ ስርዓት ወደ ሚከበርበት ደሎሎ ቡዴና በሚያመሩበት ወቅት በመግቢያ በሩ አከባቢ ተቃውሞ ባሰሙ ወጣቶች እና በጸጥታ አካላቱ መሃል በተፈጠረ አለመግባባት መጠነኛ መረጋገጥ ተስተውሏል፡፡

አባገዳዎቹ በዚው የኢሬቻ ስፍራ ስርዓቱን አከናውነው ከወጡም በኋላ በጭፈራቸው እና በተቃውሞ ድምጽ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ እና ሌሎች እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡ ወጣቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ ሲያሰሙም ተደምጠዋል። ወጣቶች "ፍትህ ለሃጫሉ" የሚሉ መፈክሮችንም አሰምተዋል።

ስዩም ጌቱ 

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW