1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢሰመኮ - አርሲ ዞን የተፈፀመዉን ጥቃት ክትትል እና ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገለፀ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ሰኔ 1 2018

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ከሳምንት በፊት የተፈጸመው የንጹሃን ግድያን በተመለከተ መንግሥት ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡ ኢሰመኮ መንግስት ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባልም ብሏል፡፡

ፎቶ ከማኅደር ፤ በቆጂ አርሲ ዞን
ፎቶ ከማኅደር ፤ በቆጂ አርሲ ዞን ምስል፦ Seyoum Getu/DW

ኢሰመኮ - አርሲ ዞን የተፈፀመዉን ጥቃት ክትትል እና ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገለፀ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ከሳምንት በፊት የተፈጸመው የንጹሃን ግድያን በተመለከተ መንግሥት ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ፡፡ ኢሰመኮ መንግስት ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን ሊወስድ ይገባልም ነው ያለው፡፡ የኢትዮጵያሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ግንቦት 23 እና 24 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ክትትል እና ምርመራ እያከናወነ መሆኑን በመግለጽ፤  እሁድ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው “በተለምዶ ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን በፈጸመው ጥቃት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላትና ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል፡፡

በጥቃቱ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ የንብረት ውድመት እና ቃጠሎ መድረሱን ለማረጋገጥ መቻሉንም የገለጸው ኢሰመኮ፤ የጥቃቱ ቦታው ላይ በአካል በመገኘት ከዐይን እማኞች፣ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ እና ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት መረጃ ማሰባሰቡን አስታውቋል። በዚህ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ስልጠና ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ፤ “ምርመራውን ከሩቅ ሆነን ሳይሆን በቦታው ላይ ሆነን ከሚመለከታቸው ትክክለኛ ምንጭ በማጣራት ነው እገለ ጥቃቱን ፈጽሟል ልንል የቻልነው” ብለዋል፡፡

በጥቃቱ የደረሰው ውድመት

እንደ ኢሰመኮ የምርመራ ውጤት በአሰኮ ወረዳ ደለታ ጫፋ ቀበሌ ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በአከባቢው በመስተዋሉ የአካባቢው ሚሊሻዎችና የኦሮሚያ ጸረ-ሽምቅ ተዋጊዎች በስፍራው ተሰማርተው ነበር፡፡ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎቹ እና “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል ግጭት መፈጠሩንም ተከት የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ላይ ታጣቂ ቡድኑ ባደረሰው ጥቃት ከአካባቢው መሸሽ ባልቻሉ ሦስት ሲቪል ሰዎች ላይ የሕይወት ማለፍ አደጋ ሊያጋጥም ችሏል ነው ያለው፡፡ “ሦስት ሰዎች በሃይማኖት ሁለት ክርስቲያኖች እና አንድ የሙስሊም ሃማኖት ተከታይ፤ በአጠቃላይም ሶስት ወንዶች በጥቃቱ ተገድለዋል” ያሉት አቶ በዳሳ፤ ከ2 ሺህ 500  በላይ ደግሞ በጥቃት ምክንያት መፈናቀላቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢሰመኮ ቁጥራቸው ለጊዜው በውል ባልታወቁ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶች ላይ ቃጠሎ መድረሱን፣ የጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን መቃጠሉን፤ ቢዮ ቡጡሌ የሼክ ሙስጠፋ መስጅድ አጥር ላይ ጉዳት መድረሱን፣ በደለታ ጫፋ ጤና ጣቢያ፣ በነዋሪዎች መኖሪያ ቤቶችና የንግድ መደብሮች ላይ በመደዳ ዘረፋ መፈጸሙን እንዲሁም ከ2,650 በላይ የሚገመቱ የአካባቢው ነዋሪዎች መፈናቀላቸውንም አረጋግጧል።

በሰው ሕይወት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን

ኢሰመኮበጥቃቱ የደረሰውን የግድያ መጠን ሦስት ብልም፤ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ እና ለሌሎችም መገናኛ ብዙኃን የሰጡ የአከባቢው ነዋሪዎች ብያንስ ዘጠን ሲቪሎች መገደላቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ ምዕመኖቼ ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት እየተፈጸመብኝ ነው ያለችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በተለይም በሀገረስብከቱ ስራ ኃላፊዎች በኩል እንዳሳወቀችውም ቢያንስ ሰባት ንጹሃን የሃይማኖቱ ተከታዮች በእሁድና ሰኞው ጥቃት ሕይወታቸው ማለፉን ጠቁማለች፡፡ ይሄን አንስተን ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ በዳሳ ለሜሳ እዳሉት ግን፤ “የእኛ ምርመራ ሌሎች ተቋማት ያወጡትን ምርመራ ለማረጋገጥ ወይም ለማስተባበል የሚሰራ አይደለም” በማለት ኮሚሽኑ በራሱ የምርመራ ስርዓት በቦታው በመገኘት ያረጋገጠው የሶስት ሰዎች ህልፈት መሆኑን ነው ያስገነዘቡት፡፡

ተደጋጋሞ  ስለሚፈጸመው ጥቃት የኢሰመኖ ጥሪ

ኢሰመኮ በአርሲ ዞን በሽርካ፣ በአሰኮ፣ በአንቆሎ ዋቤ፣ ጉና እና መርቲ ወረዳዎች ላይ በታጣቂዎቹ ሲፈጸሙ የነበሩ ጥቃቶች ዳግም እንዳይከሰቱ ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ እና ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ደጋግሞ ማሳሰቡን አስታውሶ፤ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች አሳሳቢ በሆነባቸው በነዚህ አከባቢዎ፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሰማሩና ነዋሪዎችን ወደ ተረጋጋ ሕይወት እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡

ብርኃኑ አዴሎ - የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዳይሬክተር ምስል፦ Solomon Muche/DW

በመንግሥትና በሌሎች አጋር አካላት በጥቃቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ነዋሪዎች በቂ የሆነ የአስቸኳይ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲቀርብና ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ተመልሰው በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻች ኢሰመኮ አሳስቧል።  ኮሚሽኑ እንዳለው፤ የተፈጸሙ ጥቃቶችን በአግባቡ ሳያረጋግጡ የሚሰነዘሩ ፍረጃዎችና ቅስቀሳዎች ተጨማሪ ግጭት እንዲፈጠር የማነሳሳት ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ማናቸውም ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሲል ጥሪ አቅርቧልም።

በኮሚሽኑ የሰብአዊ መብቶች ትምህርት እና ስልጠና ኮሚሽነር በዳሳ ለሜሳ እንዳሉትም፤ “በተለያዩ ግለሰቦች ከተሰራጪ የምስል እና የአሃዛዊ ቁጥሮች መረጃዎች አንዳንዶቹ ትክክል ሳሆኑ ቀርተው ተገኝተዋል”፡፡ በአርሲ የተፈጸመውና በርካቶችን ያነጋገረው ጥቃት ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በኮሚዪኒኬሽን ቢሮው ኃላፊ በኩል እንዲሁም፤ የፌዴራል መንግስት በሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር በኩል ድርጊቱን አውግዘው ተጨማሪ ማጣራቶች እንደሚደረጉ ፍንጭ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ መንግስት የነዋሪዎች በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት እና የንብረት መብቶች ለአደጋ እንዳይጋለጡ፣ ተገቢውን ምርመራ በማካሄድ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እና ተጎጂዎችን ለመካስና ለማቋቋም የሚያስችሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ እንዲሁም ሁሉም አካላት የተፈጠሩ ችግሮችን ከማውገዝ ባሻገር ግጭት ቀስቃሽ ከሆኑ መግለጫዎች እና ድርጊቶች እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW