ኢሰመኮ፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ እንዲሻሻል ያደረገዉ ግፊት ውጤት ማምጣቱን አስታወቀ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6 2017
የሲቪክ ድርጅቶችን ሥራ ይገድባል በሚል ከዘርፉ ተዋንያን ትችት የቀረበበት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ አንዳንድ ድንጋጌዎች እንዲስተካከሉ ያደረገው ውትወታ ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለፀ።ኮሚሽኑ የፍትሕ ሚኒስቴር መጀመርያ ላይ ያረቀቀው ማሻሻያ ረቂቅ አሁን "ተስፋ በሚሰጥ መልኩ" ተስተካክሏል ብሏል። ሕግ ሆኖ ገና በፓርላማው ያልፀደቀው ይህ ረቂቅ አዋጅ ደረጃው የሚለያይ ቢሆንም ግን አሁንም "የሲቪክ ምህዳሩን ያጠባል" ሲሉ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ተናግረዋል።
ሒዩማን ራይትስ ዎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንሥራ ይገድባል ያለው እና "ለሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ እና የሲቪክ ምኅዳር ብርቱ ጉዳት ያመጣል" ያለው፣ የተለያዩ የሲቪክ ድርጅቶች ረቂቁ "የቀድሞውን አፋኝ የሕግ መንፈስ መልሰው ይዘው የመጡ ድንጋጌዎችን ያካተተ እና ያለ ጊዜው የመጣ" ነው ያሉት፤ አርቃቂው ፍትሕ ሚኒስቴር በፊናው "ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር፣ የድርጅቶች እንቅስቃሴ የሕዝብ እና የሀገርን ጥቅም ባረጋገጠ መልኩ" እንዲፈፀም ለማድረግ በሚል የተዘጋጀ ነው ያለው የሲቪል ድርጅቶች ረቂቅ ማሻሻያ ሕግ ላይ ያደረጉት ውትወታ ውጤት ማምጣቱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ ሰሞኑን የኢትዮጵያን ዓመታዊ የመብቶች አያያዝ ኹኔታ ሲያቀርቡ ገልፀዋል። ምንም እንኳን አሁንም ለዘርፉ አደጋ የያዙ አንቀጾች እንዳሉ በመግለጽ።
"ለውጥ አለ። በሰጠነው ምክረ ሀሳብ እና ውትወታ ውጤት ያመጣ ይመስለኛል።"
ረቂቅ ማሻውያ የውጭ ድርጅቶች እና ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች የተመሰረቱ ሀገር በቀል [ሲቪክ] ድርጅቶች የፖለቲካ ፓርቲዎችን በማግባባትም ሆነ ግፊት በማድረግ ተፅዕኖ መፍጠር፣ በመራጮች ትምህርት ወይም በምርጫ መታዘብ ሥራ ላይ መሠማራት አይችሉም" የሚል ሀሳብም ይዟል። አቶ ብርሃኑ አዴሎ እርምት ከተደረገባቸው ማሻሻያዎች አንዱ ይህ ስለመሆኑ ጥቆማ ሰጥተዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ግን በዓመቱ የመብት ጥሰት ከደረሰባቸው ዘርፎች አንዱ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ መሆኑን፣ የጋዜጠኞች እሥር "እየቀነሰ መጥቷል" ያሉት ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ "ዛሬ አዲስ በአበባ እሥር ቤት ውስጥ ያለ ጋዜጠኛ የለም" ሲሉም ገልፀዋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ረቂቅ ማሻሻያው በመያዶች ላይ "ሰፊ ገደቦችን፣ የአስተዳደራዊ መሰናክሎችን፣ ከባድ የወንጀል ቅጣቶችን እና ጣልቃ ገብነትን ጭኖ የቆየውን የቀድሞውን ሕግ የሚመልስ፣ ለመንግሥት ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት በር የሚከፍት ነው" በማለት ሥጋቱን መግለፁ ይታወሳል። ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች - በኢትዮጵያ የተባለው የሲቪክ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መብርሂ ብርሃነ በዚሁ ረቂቅ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።
"የተወሰኑ [ምህዳሩን] የሚያጠቡ ነገሮች እንዳሉ የሚያሳይ ነገር አለ።"
በረቂቁ ማሻሻያ ሲቪክ "ድርጅት ለሀገር ደህንነት ሥጋት መሆኑ በባለሥልጣኑ የሚታመንበት ከሆነ" የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር የሀገር ደህንነት ሥጋት መሆኑን ይወስናል" በሚል ሰፍሯል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሰ