1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትአፍሪቃ

ኢሰመኮ 5,568 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን ዐሳወቀ

ሰለሞን ሙጬ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 28 2017

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት «በርካታ» ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዐሳውቋል ። «ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀምበት የምትችለው እጅግ ኃያሉ መሣሪያ ነው ።»

Äthiopien | EHRC in Addis Abeba
ምስል Solomon Muchie/DW

«በርካታ» ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ኢሰመኮ ዐሳውቋል

This browser does not support the audio element.

«ትምህርት» አሉ በያኔው የደቡብ አፍሪቃ አሰቃቂ የዘር መድልዎ ፍልሚያ ወቅት ኢትዮጵያ ውለታ የዋለችላቸው የቀድሞው የደቡብ አፍሪቃ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ። «ትምህርት ዓለምን ለመለወጥ ልትጠቀምበት የምትችለው እጅግ ኃያሉ መሣሪያ ነው ።»

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች እና የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት «በርካታ» ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዐሳውቋል ። ኮሚሽኑ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብት ሁኔታዎችን በሚመለከት ባወጣው ዓመታዊ ዘገባ «ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል ።» ኮሚሽኑ ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ድረስ ባደረገው የመረጃ ማጣራት በስምንት ክልሎች ውስጥ 5,568 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን መመልከቱን ይፋ አድርጓል ። 

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በዝርዝር ባስቀመጠው መረጃ «በበርካታ አካባቢዎች ለመምህራንም ሆነ ለተማሪዎች አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ ባለመኖሩ» የትምህርት መብት እጅግ ተጎድቷል ።

በኮሚሽኑ የሲቪል፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ-ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል የዚህ ሁሉ ችግር መነሻው ዋናው በመንግሥት እና በታጣቂዎች የሚደረግ ግጭት ሲሆን የተፈጥሮ አደጋዎችም ቀላል ግምት የሌለው ተጽእኖ አድርሰዋል። ኮሚሽኑ አንዳንድ ባላቸው አካባቢዎች መምህራን ትምህርት ቤት ውስጥ ለመገኘት በተለይም ሴት መምህራን "የመደፈር እና የመዘረፍ ሥጋት" ያለባቸው በመሆኑ ትምህርት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን አመልክቷል።

ሰሞኑን የአጠቃላይ የትምህርት ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ባደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሄው የመምህራን ጉዳይ ተነስቶ ነበር። 

"የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መጀመርያ በመምህራን ሕይወት ላይ መሠራት አለበት"

በዚሁ የምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ በቀረበው ረቂቅ አጠቃላይ የትምህርት አዋጅ ላይ የትምህርት ቤቶች መዘጋት ብቻ ሳይሆን የመማሪያ ቋንቋዎች ጉዳይም መነጋገሪያ ነበር።  ትምህርት ቤቶች ከተዘጉባቸው ስምንት ክልሎች አንዱ በሆነው አማራ ክልል ብቻ 4178 ትምህርት ቤቶች የመዘጋታቸው አሳሳቢነትም ተነስቷል።

«የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ መጀመርያ በመምህራን ሕይወት ላይ መሠራት አለበት» ብሏል፦ ኢሰመኮምስል Solomon Muchie/DW

መንግሥት የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን እንዲሁም ፍትሐዊነትን ለማሳደግ ያስችላል ያለውን የሕግ ማዕቀፍ ያዘጋጀ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ለሚሊየን የቀረበ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት ለምዘና ተቀምጠው ከ40 ሺህ ያልበለጡት ምዘና የሚያልፍበት ሁኔታ ወጣቶችን ወደ ሌላ አቅጣጫ እየመራ መሆኑን አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሰሞኑን ስለ ሰላም በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ ገልፀዋል።

ኢሰመኮ በዓመቱ በተደረገው የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የምርመራ ውጤት "የፀጥታ ሁኔታ አንጻራዊ መሻሻል ባሳየባቸው" በተባሉ አካባቢዎች መምህራን አካባቢውን ለቀው የሄዱ በመሆናቸው አንድም የመምህራን እጥረት ተከስቷል፤ በሌላ በኩል ወላጆች በተጨባጭ ሥጋት ምክንያት ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት አይልኩም ።

ሰለሞን ሙጬ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW