ኢትዮጵያና ሩሲያ የብርና የሩብል የቀጥታ የምንዛሪ ልዉዉጥ ማድረግ ጀመሩ
ዓርብ፣ ሐምሌ 4 2017
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የኢትዮጵያን ብር ከሩሲያ ሩብል ጋር በቀጥታ ከሚመነዘሩ ገንዘቦች ዝርዝር ውስጥ ማካተቱን አስታወቀ።ባንኩ እንዳስታወቀዉ ዉሳኔዉ ብርን ወደ ሩብል ሩብልን ደግሞ ወደ ብር መመንዘር የሚያስችል ነዉ። የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ ዛሬ ይፋ ባደረገው የምንዛሪ ተመንም 100 የኢትዮጵያ ብር 57.58 ሩብል ይመነዘራል።ኢትዮጵያና ሩሲያ በብሔራዊ ገንዘባቸው ለመገባየት ይረዳል የተባለለትን ዉሳኔ በተመለከተ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሥዩም ጌቱ ተከታዩን ዘገባ ልኮልናል።
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ የኢትዮጵያን ብር ጨምሮ የ12 ሀገራት ገንዘቦች ከሩሲያ ሩብልስ ጋር ያላቸውን ይፋዊ የምንዛሪ ተመን ለማስቀመጥ ውሳኔ ላይ መድረሱን ከተወሰኑ ቀናት በፊት አስታውቆ ነበር።
ማዕከላዊ ባንኩ ዛሬ ሃምሌ 04 ቀን 2017 ዓ.ም. ማለዳውን ይፋ ባደረገው መረጃም ባንኩ የሩሲያ ሩብል ከብር አኳያ ያለውን ዋጋ ተምኖ አስቀምጧል፡፡ በዚህም ለ100 የኢትዮጵያ ብር 57.58 ሩብል ወይም ለ1 ብር 0.57 ሩብል የምንዛሬ ተመን አስቀምጧል።
ባንኩ ለኢትዮጵያ ብር ምንዛሬ ተመን የኮድ ቁጥር 230 የሰጠ ሲሆን በየዕለቱም የምንዛሬ ተመኑን የሚያሳውቅ እንደሆነ ነው የገለጸው።
ከሩሲያ ጋር በቀጥታ የውጪ ንግድ ለመሳተፍ ብቁ የሆኑ አገራት ወደ 40ማደጋቸውን አገሪቱ ከዚህ በፊት ያስታወቀች ሲሆን ከወራት በፊት ከአርጀንቲና፣ ካምቦዲያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሜክሲኮ፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒሲያ እና ላዮስ ተወካዮች ጋር ከስምምነት ተደርሶ መፈረሙ እንደተገለጸም ይታወሳል፡፡
ይህ የዓለማቀፍ ዋነኛ መገበያያ ገንዘብ የሆነውን ዶላር ሳይጠቀሙ በአገራቱ መካከል በብሔራዊ ገንዘባቸው የመገበያየቱ አንድምታ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ አቶ አብዱልመናን መሃመድ ምናልባትም ይህ ሰሞኑን
ባለፈዉ ሳምንት ብራዚል የተደረገዉ የብሪክስ አባል አገራት የመሪዎች ስብሰባ ውጤት ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል፡፡ “ምናልባትም የስብሰባው ውጤት ሊሆን ይችላል” ያሉት አብዱልመናን “አንድ አገር የብሔራዊ ገንዘቧ የመንዛሪ ተመን ማስቀመጥ ማለት ከፍ ያለ ደረጃ ነው” በማለት አሁን ላይ በሁለቱ አገራት መካከል ካለው የንግድና ኢንቨስትመንት ጥንካሬ አኳያ ግን ውጤቱ እዚህ ግባ ሊባልለት የሚችል አይደለም ነው ያሉት፡፡
ከወራት በፊት በሞስኮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገነት ተሾመን ዋቢ አድርጎ የሩሲያው የዜናምንጭ ታስ (TASS) እንደዘገበው ሞስኮ እና አዲስ አበባ በብሔራዊ መገበያያ ገንዘባቸው የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ዝግጅት አጠናቀዋል፡፡ በወቅቱም ሂደቱ ገና እንጭጭ ደረጃ ላይ መሆኑ ተገልጾ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ትብብር ግን በጊዜ ሂድት እንደሚያድግ ተስፋ መኖሩ ተጠቁሟል፡፡ ይህ አሰራር የኢኮኖሚ ግንኙነትን ተገማችና ማዕቀቦችም በሌሉ ጊዜ አድንኳ ፋይዳው ጎልቶ ማስቀጠል የሚቻልም ነው የተባለለት ነው፡፡
የገነዘብ አስተዳደር ባለሙያውአብዱልመናን መሀመድ በዚህም ላይ ባከሉት አስተያየታቸው፤ “ሩሲያ በዚህ በዩክሬን ጦርነት የተነሳ ፊቷን ወደ አፍሪካ እና እንደ ህንድ እና ቻይና ያሉ አገራት ፊቷን እያዞረች ትገኛለች” በማለት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት እድሉን መጠቀም ከቻሉ እምርታ ሊስገኝ የሚችል እድል ነው ብለዋል፡፡
ኢኮኖሚያ ትብብርን መነሻ አድርጎ የተነሳው ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የምገኙበት ብሪክስ የተሰኘው የመንግስታት ጥምረት በጊዜ ሂደት እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገራት ልሰጥ የሚችለው ፋይዳ ከፍ ሊል እንደሚችልም ጠቁመው አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ይብልጥ ወደ ምዕራቡ ዓለም የፋይናንስ ምንጮች ላይ ጥገኛ መሆኗል በአስተያየታቸው ገልጸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ አሁንም በጣም ጥገኛ የሆነችው በምዕራቡ ዓለም ላይ ነው” ያሉት አብዱልመናን ከዓለማቀፉ ገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ እያገኘች ያለውን የገንዘብ ብድርና ድጋፍ የምታገኘውን ያህል ብያንስ እስካሁን ከብሪክስ ማግኘቷ አልተሰማም ነው ያሉት፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ ተክሌ