1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያና ሱዳን ጠላቶች ወይስ ወዳጆች?

ሰኞ፣ ሰኔ 27 2014

አዲስ አበባ፣ ካርቱም፣ መቀሌ ይባል አስመራ ላይ ገዢዎች በተፈራረቁ ቁጥር ከሰላም ይብስ ጦርነት፣ ከመግባባት ይበልጥ-ግጭት፣ከመስከን ይልቅ ሁከት የሚቀጣጠልበት ምክንያት፣ ሕዝብ እንዲያልቅ፣ እንዲሰደድ፣ እንዲራብ የሚፈረድበት ጭካኔ የሚያበቃበት ዘመን በርግጥ ይናፍቃል።ግን ይመጣ ይሆን?

Äthiopien Sudan Premierminister Abiy Ahmed und General Abdel Fattah Al-Burhan Abdelrahman
ምስል፦ Reuters/M. N. Abdallah

የጠብም እንደነበር መረሳት የለበትም።

This browser does not support the audio element.

ከሰሜን ሐላይብ ጫፍ እስከ ደቡብ ሞቃዲሾ ግርጌ የተዘረጋዉ ግዛት የሚያስተናብራቸዉ አብዛኞቹ የምሥራቅ አፍሪቃ ሐገራት አንድም በርስበርስ ጦርነት፣ሁለትም በፖለቲካዊ ቀዉስ፣ ሶስትም በድንበር ግዛት ይገባኛል ጦርነት  እየወደሙ፣ እየተመሰቃቀሉም ነዉ።የኢትዮጵያና የሱዳን፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ፣የሱዳንና የደቡብ ሱዳን፣ የኤርትራና የጅቡቲ፣ የሶማሊያና የኬንያ የድንበር ዉዝግቦች በረድ-ፈላ እያሉ ለዓመታት ሲያዘግሙ ሶማሊያ ለሁለት ተገምሳ በሽብር-ፀረ ሽብር ዉጊያ፣ ኤርትራ መፈናፈኛ ባጣ አገዛዝ፣ ኢትዮጵያ በርስበርስ ጦርነትና በጎሳ ግጭት፣ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በፖለቲካ ቀዉስ ግራ ቀኝ ይላተሙ ገቡ።ጦርት፣ግጭት፣ፖለቲካዊ ቀዉስ፣የጭካኔ አገዛዝ ሺዎችን ማርገፍ፣ሚሊዮኖችን ማፈናቀሉ አልበቃ ያለ ይመስል ረሐብ ሚሊዮኖች እየሸነቆጠ ነዉ።ሰሞኑን ደግሞ ኢትዮጵያና ሱዳን የምዕተ-ዓመት የዉዝግብ መዝገባቸዉን ገልጠዉ አዲስ እስጥ አገባ ገጥመዋል።ይዋጉ ይሆን?  

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የዓብይ አሕመድ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ባለፈዉ ሐሙስ ለጋዜጠኞች እንደነገሩት በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ከእስካሁኑ የከፋ ይሆናል ብለዉ አያስቡም።በሁለት ምክንያት።«የሱዳን  ሕዝብ ለኢትዮጵያዊያን ወድማማችና እሕትማማች ነዉ፤ ወይም ከኢትዮጵያዉያን ጋር እሕትማማቻዊ ግንኙነት አለዉ። ሱዳን ዉስጥ በነበረዉ የሰላም ሒደት መሳተፋችንና ይሕን ግንኙነት የፈጠረዉ ታሪካዊ ትስስር ሊዘነጋ የሚገባ ጉዳይ አይደለም።ስለዚሕ ይሕ ቁርቁስ ያንን ዕዉነታ ያበላሸዋል ብዬ አላምንም።»

አላበሉም።ግን ታሪካዊዉ ትስስር የወዳጅነት ከመሆኑ እኩል የጠብ-ቁርቁስም እንደነበር መረሳት የለበትም።

ምስል፦ Mahmoud Hjaj/AA/picture alliance

የመሕዲዋ ሱዳን ሰሜን ኢትዮጵያን ወርራ ንጉስ ነገስት አፄ ዮሐንስን  ጨምሮ በሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን እንደፈጀች ሁሉ፣ ኢትዮጵያ በፋሺት ኢጣሊያ በተወረችበት ዘመን የብሪታንያዋ ሱዳን አፄ ኃይለስላሴን ጨምሮ ለኢትዮጵያ አርበኞች መሸጋጋሪያ ሆናለች።

የካርቱም ገዢዎች የኤርትራ ነፃ አዉጪ ተዋጊዎችን ከመደገፋቸዉ እኩል የአፄ ኃይለስላሴዋ ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳኖቹን የአንያ ንያ አማፂያንን ረድታለች።ደግሞ በተቃራኒዉ ካርቱሞች የኤርትራና የትግራይ  አማፂንን ከአዲስ አበባ ገዢዎች ጋር ለማደራደር ሞክረዋል።አዲስ አበቦች በተለይ አፄ ኃይለ ስላሴ በ1972 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የደቡብ ሱዳን አማፂያዎችን ከካርቱሞች ጋር አስታርቀዋል።

ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያምና ኮሎኔል ጀዓፈር አል ኑሜሪ ካርቱምና አዲስ አበባ ላይ «አኽዋን፣ አኽዋን ኢትዮጵያ ወ ሱዳንን» እያስዘፈኑ፣እያስጨፈሩ፣ እንደ ጥብቅ ወዳጅ እንደተቃቀፉ ሁሉ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ለመጣል ብዙ አሲረዋል፣ አንዳቸዉ የሌላቸዉን አማፂ ኃይላት ደግፈዋል።ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊና ፕሬዝደንት አልበሽር እየተወዳጁ ሲጣሉ፣እየተወነጃጀሉ ሲፋቀሩ ገዝተዉ በየተራ የካርቱምና የአዲስ አበባ አብያተ መንግስታትን ተሰናብተዋል።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድዋ ኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ቢልለኔ ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት፣ በ2019 የብዙ መቶ ሱዳናዉያንን ሕይወት ያጠፋዉን የሱዳን የጦር ጄኔራሎችንና የፖለቲከኞችን ጠብ ለማርገብ ብዙ ጥራለች።የድርድር ስምምነቱ ሒደትና ዉጤት አምባሳደር ማሕሙድ ድሪሪ የመሩት የኢትዮጵያ የመልዕክተኞች ጓድ ብልሐት፣ዕዉቀትና ትዕግስትን የተፈታተነ ነበር።«እልሕ አስጨራሽና ትዕግስትን የሚጠይቅ» ብለዉን ነበር አምባሳደር ማሕሙድ ያኔ።

 ነበር።

ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ጥላሁን ገሰሰ፣ ሚኒሊክ ወስናቸዉ፣ ዓሊ ቢራ ሌሎችም ኢትዮጵያዉያንና ለኢትዮጵያዉን እንደሆኑት ሁሉ ለሱዳኖችም፣ መሐመድ ወርዲ፣ ሰዒድ ኸሊፋና ሌሎችም ሱዳናዊያንና ለሱዳን ሕዝብ እንደሆኑት ሁሉ ለኢትዮጵያዉንም ተወዳጅ ናቸዉ።ዛሬም ጭምር።

የኢትዮጵያ ጦር የማረካቸዉን 6 የሱዳን ወታደሮችንና አንድ ሰላማዊ ሰዉ ገድሏል የሚሉት የካርቱም ወታደራዊ ገዢዎች ግን የነበረና ያለዉን መልካም ሁሉ ደፍልቀዉ እያቅራሩ ነዉ።የሱዳን ጦር ኃይል ቃል አቀባይ ብርጌድየር ጄኔራል ነቢል አብዱላሒ እንደዛቱትማ ጦራቸዉ «የተሰዉ» ጓዶቹን ደም ይበቀላል።«የተከበርከዉ የሱዳን ሕዝብ ሆይ!የሱዳን ጦር ኃይሎች ለተሰዉት ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ከልብ የመነጨ ሐዘናችንን እንገልፃለን።ይሕ የክሕደት እርምጃ አፀፋ ሳይሰጠዉ አይታለፍም።ለዚሕ የፈሪዎች እርምጃ ተመጣጣኝ አፀፋ እንሰጣለን።»

የኢትዮጵያ ጦር ሱዳናዉያኑን ገድሏል የሚለዉን ዉንጀላ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።ሰባቱ ሰዎች የተገደሉት የሱዳን ጦር ከኢትዮጵያ ሚሊሺያ ጋር በገጠመዉ ዉጊያ እንደሆነ ባለስልጣናቱ አስታዉቀዉ፣ ሕይወት በመጥፋቱም ሐዘናቸዉን ገልፀዋል።«የሱዳን የጦር ጓድ በጫረዉ ጠብ ምክንያት ሕይወት በመጥፋቱ የኢትዮጵያ ወገን ሐዘኑን ይገልፃል።የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በግጭቱ አልተሳተፈም።የተገደለ የጦር ምርኮኛም የለም።ስለዚሕ ጠቡን የጫረዉ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ነዉ የሚለዉ ወቀሳ በኢትዮጵያ በኩል ጨርሶ ተቀባይነት የለዉም»

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድም በአረብኛ ባስተላለፉት መልክት አዲስ ያገረሸዉ ግጭት እንዳይባባስ ተማፅነዋል።

ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ሱዳን ግን በዲፕሎማሲዉም፣ በጦር ግንባሩም መስክ ጥቃትዋን አጠናክራለች።ምርኮኛ ወታደሮችን የኢትዮጵያ ጦር ገደሏል በማለት ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት አቤት ብላለች።ጦር ኃይሏም፣ ጄኔራል ነቢል እንደዛቱት የኢትዮጵያን ግዛት ለተከታታይ ቀናት በከባድ ጦር መሳሪያ ደብድቧል፤ ጀበል አል ለበን የተባለ ሰፈርንና አካባቢዉን  መቆጣጠሩን አስታውቋልም።

ኢትዮጵያና ሱዳን አል ፋሸቅ በተባለዉ አዋሳኝ ለም ግዛት ይገባኛል ሰበብ ከ1902 ጀምሮ እንደተወዛገቡ ነዉ።የካርቱምና የአዲስ አበባ ገዢዎች «ባንድ እንብላ፣ ባንድ---- »በሚል ዓይነት ወዳጅነት በከነፉበት በ2008 ባደረጉት ዉል አወዛጋቢዉ ግዛት የሱዳን እንደሆነ የአዲስ አበባ ገዢዎች ተስማምተዋል።ካርቱሞች ባንፃሩ በዚያ ግዛት የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንን ላለማባረር ቃል ገብተዉ ነበር።

ሰነዶች እንደሚጠቁሙት በ2020 የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግስት ከትግራይ ገዢ ፓርቲ ሕወሓት ጋር ዉጊያ ሲገጥም ሕወሓት በሱዳን ግዛት በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ጦርን እንዳያጠቃ አዲስ አበባ ካርቱምን ጠየቀች።በጥያቄዉ መሰረት የካርቱም ወታደራዊ ገዢ ሌትናንት ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አል ቡርሐን 60 ሺሕ ወታደሮችን ወደ አወዛጋቢዉ ግዛት አዘመቱ።

የሱዳን ጦር በ2008 የተደረገዉን ስምምነት ጥሶ ከታሕሳስ 2020 ጀምሮ ኢትዮጵያዉያኑን እያባረረ፣ የአወዛጋቢዉን ግዛት አብዛኛ አካባቢዎች ተቆጣጠረ።ሰሞኑን ደግሞ የካርቱም ወታደራዊ ገዢዎች የኢትዮጵያ ግዛትን ጭምር እያስደበደቡ፣ ለተጨማሪ ጥቃት እየተጋበዙ፣ አዲስ አበባን እየከሰሱ ነዉ።

አንድ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኝ እንደነገሩን ሱዳኖች ከ2020 ጀምሮ ያደረጉትን ሁሉ ለማድረግ የደፈሩት «የዉስጥ ፖለቲካዊ ቀዉሳቸዉን ለማስተፈንስ፣ የሕዳሴ ግድብን ሙሌት ለማደናቀፍ፣ምናልባትን ለሕወሓት ድጋፋቸዉን ለመግለጥ» ሊሆን-ላይሆንም ይችላል።

«ዋናዉ ምክንያት ግን» አከሉ የፖለቲካ አዋቂዉ «አንድና ግልፅ ነዉ፤ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት መዳከም።የፖለቲካ ተንታኝና የሲቢል ሰርቪስ ኮሎጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ ሌላም ያክሉበታል።«ሱዳኖች በኢትዮጵያ ሥርዓት ላይ «እምነት ማጣት» የሚል።«----ሱዳን ዉስጥ ያለዉ ወታደራዊ  አገዛዝ  የኢትዮጵያ መንግስትን እንደ ተዓማኒ፣ ዘላቂ  ወዳጅነት ለመመስረት የሚያመች ስርዓት እንዳልሆነ እየወሰዱ (እያሰቡ) መጥተዋል የሚል ማሳያዎች አሉ።» 

የመሕዲዎቹ ኸሊፋ አብዱላሕ ኢብን መሐመድ አል ኸሊፋ (ኸሊፋ አል መህዲ) የዛሬይቱን ሱዳን የገዢነት ሥልጣን በ1885 ሲወርሱ ከሐገራቸዉ የተለያዩ አካባቢ ገዚዎች ፍተኛ ተቃዉሞ ገጥሟቸዉ ነበር።ኸሊፋዉ የሐገር ዉስጡን ተቃዉሞ ለመቀነስ ግማደ ግዛትን ወደ ግብፅና ኢትዮጵያን ማስፋፋት የሚል መርሕ ይከተሉ ገቡ።

ምስል፦ Ethiopian News Agency/AP/picture alliance

በዚሕ መርሐቸዉ መሠረት በ1887 አንሳር የተባለዉን 60 ሺሕ ጦር አዝምተዉ ኢትዮጵያን ወረሩ።ጎንደርን አጋዩ።በ1889ኝ መተማ ላይ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ገጥመዉ ንጉሰ ነገስት ዮሐንስ 4ኛን ጨምሮ ብዙ ኢትዮጵያዉያንን አስገደሉ።ጄኔራል ቡርሐን የአብዱላሕ ኸሊፋን መርሕ ይዉረሱ አይዉረሱ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።ይሁንና ልክ እንደ ኸሊፋዉ ሁሉ የካርቱምን ቤተ-መንግስት በኃይል ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ተለይቷቸዉ አያዉቅም።በ2020 ወደ አል ፋሻቅ ያዘመቱት ጦርም 60 ሺሕ ነዉ።ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ አል ፋሻቅ ድረስ ሔደዉ ላካባቢዉ ነዋሪዎች ዛቱም።

«እንደግፋችኋለን።ከጎናችሁ እንቆማለን።ወደዚሕ አካባቢ ከእንግዲሕ ማንም እንዳይደርስ መከላከል እንድትችሉ እናደደርጋለን።የወደቁ (የተገደሉ) ወንድሞቻችንን መብት እኛና እናንተ ማስከበር እንችላለን።ዋዛ እንዳልሆንን ለጠላታችን እናስመሰክራለን።ይሕ ጉዳይ እንደዘበት እንዲቀር አናደርግም።ብዙ አናወራም።አፀፋችን በተግባር ይታያል።»

የሱዳን ጦር ያለምንም ቅድመ ግዴታ አወዛጋቢዉ ግዛት እንዲሰፍር የኢትዮጵያ መንግስት በ2020 የጠየቀና የፈቀደበት ምክንያት በርግጥ ሊያጠያይቅ ይገባል።ሁለቱ መንግስታት ግን የለየለት ጦርነት መግጠም መቻላቸዉ ብዙዎችን እያጠራጠረ ነዉ።የእስካሁኑ ቁርቁስ እንዲቆምም አካባባቢያዊ ማሕበራትና መንግስታት እየጠየቁ፣እያሳሰቡም ነዉ።ዶክተር መከረም እንደሚሉትም የካርቱምና የአዲስ አበባ ገዢዎች ጠባቸዉን ካለረገቡ የለየለት ጦርነት ቢገጥሙ ኪሳራዉ፣ በተለይ ለኢትዮጵያ ሲበዛ ከባድ ነዉ-የሚሆን።«ጦርነት ለማንም፣ ለየትኛዉም ሐገር ቢሆን አያዋጣም።ሱዳን ግን ላለፉት ሶስት ዓመታት ኢትዮጵያ ላይ እንደሆነዉ የባከነ ተጨባጭ ላይ አይደለችም።»

ምስል፦ Mahmoud Hjaj/Anadolu Agency/picture-alliance

አዲስ አበባ፣ ካርቱም፣ መቀሌ ይባል አስመራ ላይ ገዢዎች በተፈራረቁ ቁጥር ከሰላም ይብስ ጦርነት፣ ከመግባባት ይበልጥ-ግጭት፣ከመስከን ይልቅ ሁከት የሚቀጣጠልበት ምክንያት፣ ሕዝብ እንዲያልቅ፣ እንዲሰደድ፣ እንዲራብ የሚፈረድበት ጭካኔ የሚያበቃበት ዘመን በርግጥ ይናፍቃል።ግን ይመጣ ይሆን?

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW