ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ዉጊያ ነበር፤ ዉጥረትም አይሏል
ማክሰኞ፣ ኅዳር 8 2019
በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር አከባቢ በተለይም በባድመ አቅራቢያ ባለፈዉ ሳምንት አጋማሽ ውጊያ እንደነበር ነዋሪዎች ገለጹ፡፡በያዝነው ሳምንት የተኩስ ልውውጦች እና የከባባድ መሳሪያ ድምጽ የቀነሰ ቢመስልም ውጥረቱ ግን መቀጠሉን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡ግጭትና ዉጥረቱ ያሠጋቸዉ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከአካባቢዉ መሸሻቸዉ ተነግሯልም።የኤርትራ መንግስት ለህዝቡ ጥሪ አድርጓል፡፡፡
በትግራይ ክልል በባድሜ እና ሺራሮ አከባቢ የሚኖሩ አስተያየት ሰጪዎች ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ እና እሮብ እለት ለሁለት ተከታታይ ቀናት በከባባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭትና የተኩስ ልውውጥ በሁለቱ አገራት (ኢትዮጵያ እና ኤርትራ) ድንበር አከባቢ መሰማቱን አመልክተዋል፡፡ እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት ግጭቱና የተኩስ ልውውጡ በስፋት የተካሄደው በሕወሓት እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካከል ነው፡፡ አንድ አስተያየት ሰጪ የአከባቢ ነዋሪ፤ “ባለፈው ሳምንት እሮብ ለታ የኢትዮጵያ ድሮን በባድሜ የኤርትራ ምሽግ መምታቱን ተከትሎ ለሁለት ቀናት በከባባድ መሳሪያ የተደገፈ ውጊ ተካህዶ ነበር” በማለት ከዚያ በኋላ ግን ከተወሰነ አነስተኛ የመሳሪያ ድምጽ ውጪ አከባቢው ጸጥ ያለ መስሏል ነው ያሉት፡፡
የሚካሄደው ውጊያ እና ውጥረት
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና አጋሮቹበስፋት ሽራሮ አከባቢ ቢሆኑም እየተንቀሳቀሱ ከህወሓት ኃይሎች ጋርየተኩስ ልውውት ሲያደርጉ በተደጋጋሚ ይስተዋላል የሚሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ የኤርትራ ሰራዊትም ቢሆን ጠቅልሎ ከኢትዮጵያ ግዛት አለመውጣቱን አመልክተዋል፡፡ “የኤርትራ መንግስት የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሳባቸው የትግራይ ክልል ኢሮፕ እና ባድሜ አከባቢ ጠቅልሎ አልወጣም” በማለት በሁለቱም በኩል ለማይቀር ጦርነት ዝግጅት የተደረገም ይመስላል ብለዋል፡፡
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከዚሁ ከድንበር ጦርነት ውጥረት ጋር ተያይዞ ባወጣው መግለጫ የአገሪቱ ህዝብ በአንድነት እንዲቆም ጥሪ ማሰማቱ ይታወሳል፡፡ ሚኒስቴሩ በመግለጫው የኤርትራ ህዝብ ድንበሩን ለመጠበቅ ከምን ጊዜውም በላቀ እራሱን እንዲያዘጋጅ የሚጠይቅም ነበር፡፡ መግለጫው በኢትዮጵያ በኩል ተከፍቶብኛል ላለው ጦርነት የኢትዮጵያ መንግስትን የአገር ውስጥ አለመረጋጋት ትኩረት ለመቀየር በሚል ከሶታልም፡፡
የባለፈው ሳምንት የአዲኩልቴ ከባድ ጦርነት
አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የባድሜ ነዋሪ ባለፈው ሳምንት የተፈጠረውን ጉዳይ በማስመልከት ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ባድሜ አቅራቢያ በተለያዩ አከባቢዎች ከባድ ጦርነት ሲካሄድ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ “ጦርነት የነበረው በአዲነብሪ ወደቀኝ አዲኩልቴ በሚባል አከባቢ የሁለት ቃን ጦርነት አንድ ቀን በከባድ መሳሪያ በሁለተኛ ቀን ደግሞ የእግረኛ ጦርነት ነበር” በማለት ባድሜ አከባቢ የትግራይ ሰራዊት በሚገኙበት ድያራ በሚባል ስፍራ ግን ድሮን ተጥሎ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ውጥረትና ስጋት በማየሉ የነዋሪዎች መፈናቀል
እኚህ አስተያየት ሰጪ አክለውም አከባቢው ላይ ከባለፈው እሮብ ወዲህ የሚታይ ጦርነት ባይኖርም አከባቢው ላይ ጎልቶ የተስተዋለው የጦርነት ውጥረት መባባስ እና በሚጣል ድሮን የሚደርሰውን ጉዳት በመስጋት በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ ሽሬ፣ አዲአገራይ እና ሽራሮ ከተሞች እየሸሹ ነው ብለዋል፡፡ “ትናንት ሰኞ ወደ ሰባት ሰዓት አዲሃራ አከባቢ በተጠለ ድሮን አንድ አይሱዚ መኪና ተቃጥሎ አምስት ሰው ቆስሏል” በማለትም አከባቢው ላይ ገብተው የነበሩ ነዋሪዎች ጦርነቱንና የሚጣለውን ድሮን በመፍራት ከአከባቢው እየተፈናቀሉ እየሸሹ ነው ብለዋል፡፡ አከባቢው ላይ በዚህ አመት ከባድ ድርቅ ተከስቶ ከመቆየቱም ጋር ተያይዞ ማህበረሰቡ ከባድ ፈተና ውስጥ ገብቷል በማለትም፤ አሁን ግጭቱን ስጋት ወደ ከተማ እሩቅ መንገድ በእግሩ በሚጓዙበት እናቶች መንገድ ላይ ለመውለድ እየተገደዱም ነው ብለዋል፡፡
ትናንቱ ሰኞ በተጣለው ድሮን መጎዳታቸውን የገለጹት አንድ በህክምና ላይ የሚገኙ አስተያየት ሰጪም፤ “አይኔ ላይ ነው ጉዳት የደረሰብኝ” ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሌላኛው የድንበር ከተማ ዛላንበሳ ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ከስፍራው ቤተሰብ አለኝ ያሉ የመቀሌ ነዋሪ አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ እስከ ትናንት ማታ ይሰራ የነበረ ስልክ ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ግን እንደማይሰራም አመልክተዋል፡፡
ባለፈው ዓርብ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሰራዊት ኢታማዦር ሹም ፊልድማርሻር ብርሃኑ ጁላ ወደ መቀሌ በመጓዝ የጦር ሰራዊት መኮንኖች ጋር መምከራቸው መነገሩ ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
ነጋሽ መሐመድ
እሸቴ በቀለ