1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር አካባቢ በተከሰተ ግጭት 25 ሰዎች ተገደሉ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2017

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑበት የቱርካና አካባቢ በተከሰተ ግጭት 25 ሰዎች ተገደሉ ፡፡ በኢትዮጵያ የዳሰነች ወረዳ ና በኬኒያ የቱርካና ግዛት አመራሮችን ለግጭቱ መነሾ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው ፡፡

የቱርካና ሐይቅ ። ፎቶ፥ ከማኅደር
የቱርካና ሐይቅ ። ፎቶ፥ ከማኅደርምስል፦ CSP_Byelikova/imago images

በቱርካና አካባቢ ግጭት 25 ሰዎች ተገደሉ

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑበት የቱርካና አካባቢ በተከሰተ ግጭት 25 ሰዎች ተገደሉ ፡፡ በኢትዮጵያ የዳሰነች ወረዳ እና በኬንያ የቱርካና ግዛት አመራሮችን ለግጭቱ መነሾ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው ፡፡ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የዳሰነች ወረዳ ከፍተኛ አመራር ግጭቱ የተጀመረው ቅዳሜ ድንበር አቋርጠው የገቡ የኬኒያ ታጣቂዎች 5 ሰዎችን ከገደሉ በኋላ ነው ብለዋል ፡፡ በኬንያ የቱርካና ግዛት ባለሥልጣናት በበኩላቸው የዳሰነች ጎሳ ሚሊሺያዎች እሁድ ቶዶኛንግ ወደ ተባለው የኬኒያ መንደር በመግባት ቢያንስ 20 ዓሳ አጥማጆችን በመግደል በርካቶችን ማቁሰላቸውን ገልጸዋል ፡፡

በቱርካና አካባቢ ግጭት 25 ሰዎች ተገደሉ

ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሚዋሰኑበት የቱርካና አካባቢ ባለፉት ሁለት ቀናት ተፈጽመዋል በተባሉ መጠቃቃቶች በትንሹ 25 ሰዎች መሞታቸው ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል ፡፡ ግጭቱ ባለፈው ቅዳሜ የተጀመረው በዳሰነች ወረዳ ሴፍ ተብሎ በሚጠራው መንደር ውስጥ መሆኑን የመንደሯ ነዋሪዎች ተናግረዋል ፡፡ የሴፍ መንደር  ነዋሪ መሆናቸውን ለዶቼ ቬለ የተናገሩ አንድ የአይን እማኝ " ግጭቱ የተጀመረው ከኬኒያ ቱርካና ግዛት ወደ ኢትዮጵያ መሬት ተሻግረው የገቡ ታጣቂዎች ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ነው ፡፡ ታጣቂዎቹ አምስት የመንደሩን ነዋሪዎች ገድለው ነው የሄዱት  ፡፡ ከዛ በኋላ የመንደሩ ነዋሪዎችም ገዳዮቹን ተከታትለው በመሄድ ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽመዋል ፡፡ በዚህ የተነሳም ግጭቱ ሊሰፋ ችሏል  " ብለዋል ፡፡

የግጭቱ መነሻ 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ባለሥልጣናት  ከኬኒያ ቱርካና ግዛት በሚዋሰነው ድንበር ላይ ግጭት ተከስቶ የሠዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል ፡፡ ለግጭቱ መነሻ ከቱርካና ግዛት ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ መሬት የገቡ ታጣቂዎች  ነዋሪዎችን በመግደላቸው ነው  ሲሉ የዳሰነች ወረዳ ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ መሳይ ለበን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ ታጣቂዎቹ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ወደ ዳሰነች ወረዳ በመግባት ሁለት የአካባቢው ነዋሪዎችን ገደሉ ፡፡ ትናንት እሁድ በተጨማሪ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ሦስት ሰዎችን ገደሉ ፡፡ በቁጣ ውስጥ የገባው የአካባቢው ማህበረሰብ ብድር እንመልሳለን በሚል ተነሳስተው የአጻፋ ጥቃት ፈጽመዋል ፡፡ ከእኛም ከእነሱም ሰዎች ሞተዋል  " ብለዋል ፡፡

የቶዶኛንግ ጥቃት

በኬኒያ የቱርካና ግዛት ባለሥልጣናት በኢትዮጵያ የዳሰነች ጎሳ ሚሊሻዎች ቶዶኛንግ ተብሎ በሚጠራው የኬኒያ መንደር በመግባት ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ይከሳሉ ፡፡ የሚሊሻ ታጣቂዎች ትናንት እሁድ በቱርካና ሐይቅ ዳርቻ ላይ የነበሩ 20 ዓሳ አስጋሪዎችን በመግደል ሌሎች በርካቶችን ማቁሰላቸውን የሰሜን ቱርካና የህዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አባል ኢካዋን ናቡኒ ለኬኒያ የመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የኬኒያ የፀጥታ ይል በአካባቢው ቅኝት እያደረገ እንደሚገኝ የጠቀሱት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ  ሬሞንድ ኦቦሎ «ግጭቱ የተከሰተው  በቱርካና ሐይቅ  የኬኒያ እና የኢትዮጵያ ድንበር ላይ ነው ፡፡ በእኛ በኩል የፀጥታ ቡድኖችን ወደ አካባቢው ልከናል ። የአካባቢው የካውንቴው ኮሚሽንም ሁኔታውን በቅርበት እየቃኙ ይገኛሉ» ብለዋል ።

ግጭቱ የተከሰተው  በቱርካና ሐይቅ  የኬኒያ እና የኢትዮጵያ ድንበር ላይ ነው ፡፡ምስል፦ Dasenech Wereda communication

የዳሰነች ወረዳ  ዋና የመንግሥት ተጠሪ አቶ መሳይ ለበን ግን የዳሰነች ሚሊሺያ ወደ ኬኒያ ድንበር ገብቷል በሚል በቱርካና ባለሥልጣናት የቀረበውን ወቀሳ አይቀበሉትም ፡፡ ራሳቸውን ለመከላከል ከተንቀሳቀሱ ጥቂት አርብቶአደሮች በስተቀር በአካባቢው የታጠቀ ሚሊሺያ አለመኖሩን ነው ዋና የመንግሥት ተጠሪው የጠቀሱት ፡፡

የጋራ ምክክር

በቱርካና አካባቢ የደረሰውን የሰው ሕይወት መጥፋት ተከትሎ  በኬኒያ የቱርካና ግዛት ባለሥልጣናት ግን በኢትዮጵያ የዳሰነች ወረዳ አመራሮች ዛሬ ሰኞ የጋራ ውይይት ማድረግ ጀምረዋል ፡፡ በውይይቱ ቅድሚያ አካባቢውን በማረጋጋትና የግጭቱን መነሻ በመመርመር ከሁለቱም ወገን ሃላፊነት ሊወስዱ የሚችሉ አካላትን የመለየት ሥራ እንደሚከናወን የዳሰነች ወረዳ  ዋና የመንግሥት ተጠሪው አቶ መሳይ  ተናግረዋል ፡፡ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ  ሬሞንድ ኦቦሎ በበኩላቸው በድንበር የተከሰተው ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በትብብር እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW