የሱዳን ጎረቤቶች ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውጊያ የሚያቆም ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ተጣለባቸው
ሐሙስ፣ ሐምሌ 6 2015ኢትዮጵያ እና ግብጽን ጨምሮ የሰባት አገራት መሪዎች በሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል የሚደረገውን ውጊያ ለማቆም የሚያደርጉትን ጥረት የማስተባበሩን ኃላፊነት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው ሰጡ። የኢትዮጵያ፣ ግብጽ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻድ፣ ሊቢያ እና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ መሪዎች በካይሮ ዛሬ ሐሙስ ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ባወጡት መግለጫ እንዳሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን በቻድ ዋና ከተማ ንጃሜና ያደርጋሉ።
የሰባቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሱዳንን ውጊያው ለማቆም የሚያስችል ተጨባጭ ዕቅድ የማዘጋጀት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በግብጽ አዘጋጅነት የተካሔደው የሱዳን ጎረቤት አገራት የመሪዎች ጉባኤ በጄኔራል አብዱል ፋታኅ አል-ቡርኻን በሚታዘዘው የሱዳን ጦር እና በብርጋዴየር ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል የሚደረገውን ውጊያ ለማቆም ያለመ ነው።
መሪዎቹን ወደ ካይሮ ለምክክር የጋበዙት የግብጹ ፕሬዝደንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ አገራቱ የሱዳንን ቀውስ በተመለከተ ያላቸውን "ርዕይ እና አቋም" በማጣጣም ለችግሩ አፈታት "ዘላቂ እና ወጥ" አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል። ፕሬዝደንቱ በካይሮ የተሰበሰቡት የሱዳን ጎረቤት አገራት መሪዎች “ሁሉም ወገኖች ግጭቱን ማባባስ አቁመው አፋጣኝ እና ቀጣይ የተኩስ አቁም ላይ ለመድረስ ድርድር እንዲጀምሩ ጥሪ ማቅረብ” እንደሚገባቸው ጉባኤው ሲጀመር ባሰሙት ንግግር ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች “ያለ አንዳች ቅድመ-ሁኔታ ያልተገደበ የተኩስ አቁም” ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቅርበዋል። ዐቢይ በንግግራቸው የካይሮው ጉባኤ ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጥረት ጋር የተጣጣመ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
“የዛሬውን ጉባኤ ጨምሮ እንዲህ አይነት ጥረቶች በኢጋድ ከሚመራው እና የአፍሪካ ኅብረት ከሚደገፈው ጥረት ጋር መጣጣም አለባቸው” ያሉት ዐቢይ “የኢጋድ ጥረት ከግጭቱ መውጪያ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶችን ለይቷል። ለዚህ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ማጠናከሪያ መስጠት አለባቸው” በማለት ለካይሮው ጉባኤ ተሳታፊዎች አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ግጭቶች እና በሱዳን እንደተፈጠረው ያሉ ቀውሶች ሊፈቱ የሚችሉት በተባበረ አካሔድ ብቻ ነው። ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ጥረት እንደሚያደርጉ የጎረቤት አገራት ያለንን ብልሀት ከማጋራት ቸል ልንልም ሆነ ሁኔታውን የበለጠ በማራዘም ልናወሳስበው አይገባም” የሚል ማሳሰቢያም ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ ኢጋድ ለሱዳን ቀውስ መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የሾማቸው የአራት አገራት መሪዎች ባለፈው ሰኞ በአዲስ አበባ ያካሔዱትን ጉባኤ ሲያጠናቅቁ ውጊያ የገጠሙ ኃይሎች “በአፋጣኝ እና ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ግጭት እንዲያቆሙ” ጥሪ አቅርበው ነበር።
በካይሮው ጉባኤ ከሰባቱ አገራት መሪዎች ጋር የተሰበሰቡት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋኪማኅማት በበኩላቸው ግንቦት 19 ቀን 2015 የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት የአፍሪካ ኅብረት ያዘጋጀውን ፍኖተ ካርታ ማጽደቁን አስታውሰዋል። ፍኖተ ካርታው በሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ማለትም፦ በተኩስ አቁም፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እና አካታች ፖለቲካዊ ንግግር ዝግጅት ላይ ያተኮረ እንደሆነ የገለጹት ማኅማት “ለረዥም ዓመታት ለዘለቀው ቀውስ ተገቢውን የመፍቻ መንገድ ለማግኘት አንድ ቀን የሱዳንን ችግር በጥልቀት መመርመር እንዳለብን ለእኛ ግልጽ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ሦስት ወራት በሚሞላው የሱዳን ውጊያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት በውጊያው ከ1,000 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፤ 3 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል። የቻዱ ፕሬዝደንት ጄኔራል ማኅማት ኢድሪስ ኤቢ ኢትኖ እንዳሉት አገራቸው በአንድ ሣምንት ብቻ 150,000 ስደተኞችን ከሱዳን ተቀብላለች። አብዛኞቹ ውጊያ የሚሸሹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው።
“በሱዳን ያለው ግጭት ለሀገሬ እና ሁሉም ጎረቤቶች የከፍተኛ ሥጋት ምንጭ ነው” ያሉት ጄኔራል ማኅማት ኢድሪስ ኤቢ ኢትኖ ቻድ “የሁኔታውን መባባስ፣ የመንግሥት ሕንጻዎችን ውድመት፣ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት እና መሠረታዊ የማኅበራዊ አገልግሎት ተቋማት ዒላማ መሆናቸውን” እንደምታወግዝ ተናግረዋል። “የምግብ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን እጥረት ለመቅረፍ፣ በንጹሐን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ቀውስ ለማስቆም፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አቅርቦት ለማመቻቸት ፈጣን እና ትክክለኛ መፍትሔዎችንበጋራ እና በንቃት እንዲፈለግ” የቻዱ ፕሬዝደንት ጠይቀዋል።
የካይሮው የመመሪዎች ጉባኤ ተሳታፊዎች በሱዳን ቀውስ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኞች ለማስተናገድ የተገደዱ ጎረቤት አገራትን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል። የሰብዓዊ ሁኔታው ማሽቆልቆል እንዳሰጋቸው የገለጹት መሪዎቹ በሰላማዊ ሰዎች፣ የጤና ተቋማት እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችንም አውግዘዋል።
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ