1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያን ጨምሮ በ17 አገሮች የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ሊጀመር ነው

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2015

ኢትዮጵያን ጨምሮ 17 አገሮች የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን በሙከራ ደረጃ ለመጀመር ተስማምተዋል። ገበያው ንብረትነታቸው ሙሉ በሙሉ አፍሪካዊ የሆኑ አየር መንገዶች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው በሚያደርጉት በረራ የነበሩባቸውን ገደቦች የሚያስቀር እንደሆነ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

Äthiopian Airlines
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ኢትዮጵያን ጨምሮ በ17 አገሮች የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር የትራንስፖርት ገበያ ሊጀመር ነው

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ እና ሌሎች አስራ ስድስት አገሮች የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል። በሥምምነቱ መሠረት አስራ ሰባቱ አገሮች ገበያቸውን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ በአፋጣኝ አንዳቸው ለሌላቸው ይከፍታሉ። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአቪየሽን ገበያውን በቅጡ የሚያውቁ ባለሙያዎች እንደሚሉት ይኸ ገበያ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መልካም ዕድል ይዞ የሚመጣ ነው። 

ገበያው በሙከራ ደረጃ መተግበር መጀመሩ ይፋ የሆነው ባለፈው ጥቅምት 25 ቀን 2015 በሴኔጋል ዋና ከተማ ዳካር በተካሔደ መርሐ-ግብር ላይ ነው። ገበያውን በሙከራ ደረጃ ለመጀመር ከተስማሙት መካከል ኢትዮጵያ፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ኮት ዲይቯር፣ ካሜሩን፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ናይጄሪያ፣ ርዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቶጎ፣ እና ዛምቢያ ይገኙበታል።

የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ መሠረት የአኅጉሪቱን የአየር ማጓጓዣ ዘርፍ ለውድድር ክፍት ለማድረግ ከ23 ዓመታት ገደማ በፊት የተፈረመው የያማሱክሮ ሥምምነት ነበር። የያማሱክሮ ድንጋጌም ሆነ የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር የትራንስፖርት ገበያ ባለቤትነታቸውም ሆነ ቁጥጥራቸው አፍሪካዊ ለሆነ አየር መንገዶች በአኅጉሪቱ ውስጥ በሚያደርጓቸው በረራዎች ከዋና መቀመጫቸው ውጪ በሁለት አገራት መካከል መንገደኞች የማጓጓዝ መብት የሚያጎናጽፍ እንደሆነ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

"ብዙዎቹ የአየር አገልግሎት ሥምምነቶች" በሣምንት የተወሰኑ ቀናት ብቻ በረራ እንዲደረግ ወሰን እንደሚያበጁ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ገበያው ለዚህም መፍትሔ እንደሚያበጅ አስረድተዋል። የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የበረራ ብዛት፣ የአውሮፕላን አይነት ገደብ እንደማይኖርበት የገለጹት አቶ ጌታቸው "በተቻለ መጠን የአየር ትራንስፖርቱን ሊገድቡ የሚችሉ" ፖሊሲዎች እና የግብር ክፍያዎች የሚቀንሱበት "በተለይ ደግሞ የዕቃ ጭነት ሙሉ በሙሉ ለውድድር ክፍት የሚሆንበት ሥርዓት" እንደሚሆን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ለመጀመር ከተዘጋጁ መካከል ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቶጎ እና ዛምቢያ ይገኙበታል።ምስል picture-alliance/M. Mainka

ሙከራውን የሚጀምሩት ጥቂት ይሁኑ እንጂ ከአፍሪካ የአቪየሽን ገበያ 80 በመቶ ገደማ ድርሻ ያላቸው 35 አገሮች አኅጉራዊውን አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ተግባራዊ የሚያደርገውን ሥምምነት ፈርመዋል። በዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ስሌት 12 ቁልፍ የአፍሪካ አገሮች ገበያቸውን ለውድድር ከፍተው ግንኙነቱን ቢያሳድጉ ይኸ ገበያ 155,000 የሥራ ዕድል እና 1.3 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ አጠቃላይ የምርት መጠን በአገሮቹ ሊፈጥር ይችላል።

ገበያው ከ1.4 ቢሊዮን በላይ የሚገመት ሕዝብ መኖሪያ የሆነውን አኅጉር ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ልማት ያፋጥናሉ ተብለው ተስፋ ለተጣለባቸው እንደ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና ያሉ ዕቅዶች መሳካት ኹነኛ ጉልበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሲቪል አቪየሽን ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ አዴፉንኬ አዴየሚ ባለፈው ጥቅምት 25 ገበያው በሙከራ ደረጃ መጀመሩ በተበሰረበት መርሐ-ግብር  "አየር መንገዶች ከዋና መቀመጫቸው ውጪ በሁለት አገሮች መንገደኞች የሚያጓጉዙበትን ዕድል በማሳደግ ብቻ ለአፍሪካ 5 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ አጠቃላይ አገራዊ የምርት መጠን ይፈጥራል ብለን እንጠብቃለን" ሲሉ ተናግረዋል። ዋና ጸሐፊዋ እንዳሉት "ከሁለት እስከ ሶስት ባሉ ዓመታት የመንገደኞች እና የጭነት በረራዎች በ51 በመቶ ያድጋል።"

በዓለም አቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር ስሌት 12 ቁልፍ የአፍሪካ አገሮች ገበያቸውን ለውድድር ከፍተው ግንኙነቱን ቢያሳድጉ ይኸ ገበያ 155,000 የሥራ ዕድል እና 1.3 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ አጠቃላይ የምርት መጠን በአገሮቹ ሊፈጥር ይችላል።ምስል picture-alliance/dpa

ገበያው ይፈጥራል ተብሎ በሚጠበቀው ላቅ ያለ ምጣኔ ሐብታዊ ጠቀሜታ የሚስማሙት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ እንደሚሉት ቀሪው ሒደት በሥምምነት ተወስኖ የቆየውን ገበያ በተጨባጭ ተግባራዊ ማድረግ ነው። አስራ ሰባቱ አገሮች "ከዚህ ቀደም በመዳረሻ ገደብ ከነበረው፤ በበረራ ድግግሞሽ ገደብ ከነበረው፤ በመጫን አቅም ገደብ ከነበረው ሥምምነት ወጥተው በያማሱክሮ ድንጋጌ እና በአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ማዕቀፍ መሠረት ይፈራረማሉ" ሲሉ አቶ ጌታቸው ቀሪውን ሒደት አስረድተዋል።

በ17 አገሮች ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ አቶ ጌታቸው ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሶስት የኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች ባለቤቶች እና ኃላፊዎችም የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ የሚመለከታቸው እንደማይሆን ገልጸዋል።

ይኸ ገበያ በተለይ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ በሌሎች የአፍሪካ ገበያዎች የተሻለ የመወዳደር ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ግን ዘርፉን በቅርብ የሚያውቁ ባለሙያዎች እምነታቸው ነው። አየር መንገዱ ቶጎ፣ ማላዊ እና ቻድን በመሳሰሉ አገራት ሽርክና አበጅቶ ሥራውን ለማከናወን የተገደደው የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የአፍሪካ ሰማይ ለአኅጉሪቱ አየር መንገዶች ነጻ የገበያ ውድድር ክፍት ሳይሆን በመቅረቱ ነው።

ከአስር ዓመታት በላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ያገለገሉት አቶ አሚር አብዱልዋሀብ ተቋሙ የአፍሪካ ገበያ ለነጻ ውድድር ክፍት እንዲሆን ግፊት ሲያደርግ መቆየቱን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የአፍሪካን ሰማይ ለአፍሪካ አየር መንገዶች ነጻ የገበያ ውድድር ለመክፈት ሲደረጉ የቆዩ ውይይቶችን በቅጡ የሚያውቁት የትራንስ ኔሽን አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሚር የአየር መንገዱን ግፊት ውድድር የሰጉ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሲቃወሙ እንደቆዩ ገልጸዋል።

አቶ አሚር የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያን ተግባራዊ ለማድረግ በተስማሙ አስራ ሰባት አገሮች የሚበር አውሮፕላን በእያንዳንዱ መዳረሻው መንገደኛ የመጫን መብት እንደሚያገኝ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ ዕድሉን የመጠቀም አቅም እና ዝግጁነት አለው። 

በ17 አገሮች ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ዓለም አቀፍ በረራዎችን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል።ምስል Wolfgang Minich/picture alliance

የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር የትራንስፖርት ገበያ ተግባራዊ ሊያደርጉት በቆረጡ የአፍሪካ ኅብረት እና በሥሩ የሚገኙ ተቋማት ዘንድ ከፍ ያለ ተስፋ ቢጣልበትም ከአንዳንድ አገራት እና አየር መንገዶች ዘንድ ተቃውሞ ሊገጥመው እንደሚችል ይጠበቃል። ገበያው ከፍ ያለ አቅም ያላቸውን የአፍሪካ አየር መንገዶች ለይቶ ተጠቃሚ ያደርጋል የሚል ሥጋት ያላቸው የናይጄሪያ ኩባንያዎች ከአሁኑ ጥርጣሪያቸውን እየገለጹ ነው።

"ታንዛኒያ ሰርቺያለሁ። ናይጄሪያ ብዙ ዓመት ሰርቺያለሁ" ያሉት አቶ አሚር አብዱልዋሀብ "እዚያ አገር ያሉ አየር መንገዶች ትልቅ አየር መንገድ ሲመጣ እንደሚውጣቸው እና እነሱን ከጨዋታ ውጪ እንደሚያደርጋቸው ስለሚያውቁ የአገሮቻቸውን ፖለቲከኞች አባብለው ይኸን ነገር ተቀባይነት እንዳያገኝ ያደጋሉ" ሲሉ ሊገጥም የሚችለውን እንቅፋት ተናግረዋል። እንዲህ አይነት ተቃውሞ በሚፈጠርባቸው አገራት የመሥራት ፈቃድ እንኳ ቢገኝ አየር መንገዶቹ በዚያው አገር በተመዘገበ ኩባንያ ሥር እንዲገቡ በማድረግ ከገበያው የሚገኘውን ትርፍ እንዲያጋሩ ይገደዳሉ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴም ቢሆኑ ይኸ ገበያ ፈተና ሊገጥመው እንደሚችል ይስማማሉ። አየር መንገዶቻቸውን ከውድድር ለመጠበቅ ሲሉ ገበያቸውን ከሚዘጉ አገራት በተጨማሪ "አየር መንገድ የለንም። የያማሱክሮ ድንጋጌ ለእኛ ትርጉም የለውም" የሚል አቋም ያላቸው ሊኖሩ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ዋናው ሥጋት በአፍሪካውያኑ አየር መንገዶች መካከል የሚደረግ ውድድር አይደለም የሚል አቋም አላቸው።

"ከገበያ አኳያ ሥጋት አለ ከተባለ ሥጋቱ የሚመጣው አፍሪካዊ ካልሆኑ አየር መንገዶች ነው" ሲሉ አቶ ጌታቸው አስረድተዋል። "ማንም ይሁን ማን ነጻ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት መኖሩ ከፍተኛ የሆነ ፋይዳ እንዳለው" የተናገሩት አቶ ጌታቸው "በሒደት የአፍሪካ አገሮች የራሳቸውን ብሔራዊ አየር መንገድ ማቋቋማቸው እና ማጠናከራቸው ተገቢነት አለው። ኢትዮጵያ በዚህ በኩል ሁሌም ተባባሪ ነች። እንደ ሥጋት አትመለከተውም" በማለት የሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግሥቴ የአገራቸውን አቋም ገልጸዋል። የአፍሪካ አንድ ወጥ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ችግሮት ሊገጥሙት የሚችል ቢሆንም "ቁርጠኛ ሆነን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመርን እና ይኸም ጥቅም እያስገኘ መሆኑን ሌሎቹ ከተረዱት ሊከተሉን እና የዚሁ አካል ሊሆኑ ይችላሉ" በማለት አቶ ጌታቸው ተስፋቸውን ገልጸዋል። 

እሸቴ በቀለ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW