ኢትዮጵያን ጨምሮ በ39 ሀገሮች ከፍተኛ ድሕነት በፍጥነት እያደገ መሆኑን ዓለም ባንክ ገለጸ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 21 2017
ግጭት እና አለመረጋጋት ኢትዮጵያ ን ጨምሮ በ39 ሀገራት ኢኮኖሚዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ የዓለም ባንክ አስታወቀ። በሀገራቱ ግጭት እና አለመረጋጋት ከየትኛውም የዓለም ክፍል በባሰ ሁኔታ ድሕነት እና አስከፊ ረሐብ ማባባሱን እና በርካታ ቁልፍ የልማት ግቦች ወደ ማይደርሱበት ደረጃ መግፋቱን የዓለም ባንክ ይፋ ባደረገው ጥናት አሳይቷል።
ጥናቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተቀሰቀሰበት ከጎርጎሮሳዊው 2020 ወዲህ “ደካማ” ወይም “fragile” እና “በግጭት የተጎዱ” የተባሉ 39 ሀገራት የሚገኙበትን አጠቃላይ ኹናቴ የገመገመ ነው። ከእነዚህ 39 ኢኮኖሚዎች መካከል 21 አሁንም ግጭት ወይም አለመረጋጋት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በጥናቱ ኢትዮጵያ ግጭት ከበረታባቸው ሀገራት ጎራ የተመደበች ሲሆን የዕዳ ጫና ውስጥ የገባች ናት። ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ጎረቤቶቿ ሱዳን፣ ሶማሊያ እና ደቡብ ሱዳን በተመሳሳይ ምድብ ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
ኤርትራ በዓለም ባንክ “ደካማ” ወይም “fragile” ተብለው ከተመደቡ ሀገራት አንዷ ስትሆን ቡሩንዲ፣ ቻድ፣ ሊቢያ እና ዚምባብዌን የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ እንደሆኑ የዓለም ባንክ ጥናት ያሳያል።
ለኢትዮጵያ በጥናቱ የትንታኔ መነሻ የተደረገው “ከፍተኛ ግጭት” የተቀሰቀሰበት የጎርጎሮሳዊው 2020 ነው። ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ዩክሬን ዌስት ባንክ እና ጋዛን በመሳሰሉ “ደካማ እና በግጭት የተጎዱ ኢኮኖሚዎች በቅርብ ዓመታት የተከሰቱ እጅግ አስከፊ ግጭቶች በአስር ሺሕዎች የሚቆጠሩ” ሰዎች እንደተገደሉ ጥናቱ አትቷል።
ከ2020 ወዲህ ባሉት ዓመታት “ግጭቶች ተደጋጋሚ እና ገዳይ እየሆኑ ሲሔዱ” ኢትዮጵያን ጨምሮ “ደካማ እና በግጭት የተጎዱ” የተባሉ 39 ኢኮኖሚዎች ከሌሎች አኳያ በዋና ዋና የዕድገት ጠቋሚዎች ወደ ኋላ መቅረታቸውን የዓለም ባንክ ትንታኔ አመልክቷል።
በትንታኔው መሠረት ከ2020 ጀምሮ የነፍስ ወከፍ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት (per capita GDP) በማደግ ላይ በሚገኙ በሚባሉ ሌሎች ኢኮኖሚዎች በ2.9 በመቶ ሲያድግ በእነዚህ ሀገሮች ግን በዓመት በአማካኝ በ1.8 በመቶ ቀንሷል።
ግጭት ወይም አለመረጋጋት በበረታባቸው ሀገራት በዚህ ዓመት 421 ሚሊዮን ሰዎች በዓለም ባንክ የከፋ ድሕነት መገለጫ በሆነው ከ3 ዶላር በታች ዕለታዊ ገቢ ሕይወታቸውን ይገፋሉ። ይህ በተቀረው ዓለም ካለው አጠቃላይ ድምር የበለጠ ነው።
ከዚህ ባሻገር ቁጥሩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ወደ 435 ሚሊዮን ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ መተንበዩን የዓለም ባንክ ሰነድ አሳይቷል። ይህ ማለት በጎርጎሮሳዊው 2030 ከዓለም የመጨረሻ ድሖች 60 በመቶ ድርሻ ይይዛል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት የዓለም ትኩረት በዩክሬን እና በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭቶች ላይ እንደሆነ የገለጹት የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት ኢንደርሚት ጊል “ይሁንና በግጭት እና አለመረጋጋት ከሚሰቃዩ ሕዝቦች 70 በመቶው አፍሪካውያን ናቸው” ብለዋል።
እነዚህ ቀውሶች “መፍትሔ ካልተበጀላቸው ሥር ሊሰድዱ” እንደሚችሉ የገለጹት የባንኩ ዋና ኢኮኖሚስት “ዛሬ ግጭት ወይም አለመረጋጋት ካጋጠማቸው ሀገራት ግማሾቹ ለ15 ዓመታት እና ከዚያ በላይ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ” ብለዋል። ኢንደርሚት ጊል “በዚህ ደረጃ የከፋ ስቃይ ተላላፊ መሆኑ የማይቀር ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በማደግ ላይ የሚገኙ በሚባሉ ሀገራት የከፋ ድሕነት ወደ ነጠላ አሐዝ ዝቅ ብሎ 6 በመቶ ቢደርስም ግጭት ወይም አለመረጋጋት ባለባቸው ሀገራት 40 በመቶ ደረጃ ላይ ይገኛል። የነፍስ ወከፍ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ባለፉት 15 ዓመታት ከእጥፍ በላይ አድጎ በአማካኝ 6,900 ዶላር ሲደርስ ግጭት ወይም አለመረጋጋት በሚፈትናቸው 39 ኢኮኖሚዎች ግን በአሁኑ ወቅት በዓመት 1,500 ዶላር ገደማ እንደሆነ ዓለም ባንክ በሰነዱ ይፋ አድርጓል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ግጭት ወይም አለመረጋጋት የሚፈትናቸው ሀገራት በአማካኝ ከሕዝብ ቁጥር ዕድገት ጋር የሚመጣጠን በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። በጎርጎሮሳዊው 2022 በሀገራቱ 270 ሚሊዮን ሰዎች መሥራት ከሚችሉበት የዕድሜ ክልል ላይ ቢደርሱም የተቀጠሩት ግን ግማሽ ያክሉ ብቻ ናቸው።
የዓለም ባንክ ምክትል ዋና ኢኮኖሚስት አያን ኮሴ “ከዕድገት ይልቅ ኢኮኖሚያዊ መቀዛቀዝ ግጭት እና አለመረጋጋት በበረታባቸው ኢኮኖሚዎች የተለመደ ሆኗል” ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለእነዚህ ኢኮኖሚዎች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ያሳሰቡት አያን ኮሴ ዕድገት እና ልማትን ግጭት እና አለመረጋጋት በሚፈታተናቸው ሀገራት መልሶ ማስጀመር ቀላል ባይሆንም የሚቻል እንደሆነ ዕምነታቸውን ገልጸዋል።
አርታዒ ታምራት ዲንሳ