ኢትዮጵያዉያኑ ለአዲሱ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት የደስታ መግለጫ አስተላለፉ
ሐሙስ፣ ሰኔ 19 2017
ኢትዮጵያዉያኑ ለአዲሱ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት የደስታ መግለጫ አስተላለፉ -መልዕክትም አላቸዉ
በደቡብ ኮርያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ከግንቦት 27 ቀን 2017 ጀምሮ ስልጣን ላይ ለሚገኙት ለደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት ለሊ ጄ ሚዮን የእንኳን ደስ ያሎት መልዕክት አስተላልፈዋል።
ባለፈዉ የጎርጎረሳዉያን 2024 ዓመት መገባደጃ ላይ ስድስት ስዓታት የቆየ ወታደራዊ ህግ «ማርሻል ህግ» ካወጁ በኋላ በህዝብ ትግል ፤ ከስልጣን የተነሱት የ“ፒፕል ፓወር ፓርቲ”ዉ የቀድሞዉ የደቡብ ኮርያው ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዩልን የተኩት ሊ ጄ ሚዮን ከግንቦት 27 2017 ጀምሮ አዲሱ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚደንት ሆነዉ ስልጣኑን ተረክበዋል።
ከጎርጎረሳዉያኑ 2022 ዓመት ጀምሮ በህዝብ ምርጫ ስልጣን ይዘዉ ደቡብ ኮርያን በፕሬዚደንትነት ሲመሩ የነበሩት ዮን ሱክ ዩል ባለፈዉ ዓመት ነሐሴ ወር መጀመርያ ፤ «ተቃዋሚዎች ፓርላማውን በመቆጣጠር ለሰሜን ኮሪያ ያደላ፣ ፀረ-መንግሥት እንቅስቃሴ በማራመድ አገሪቱን ለማሽመደመድ ጥረት እያደረጉ ነው» ሲሉ በመወንጀል አገሪቱን በወታደራዊ ህግ ለማስተዳደር የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ ወታደራዊ ህግ አዉጀዉ ነበር።
የቀድሞዉ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት ዮን ሱክ ዩል
የቀድሞዉ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት ዮን ሱክ ዩል በቴሌቭዥን መስኮት ቀርበዉም «ሰሜን ኮሪያን የሚደግፉ ኃይሎችን ለማጥፋት እና ህገ መንግሥታዊ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ለማስጠበቅ » ወታደራዊ ህጉን ማወጃቸዉን ተናግረዉም ነበር። ይህን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ሕዝባዊ ቅሪታ ብሎም በተቃዋሚ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ባለው ፓርላማ ተጽዕኖ እና ግፊት ጠነከረባቸዉ። ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚያግደው አዋጅ በፓርላማ አባላት እና በዜጎች ከፍተኛ ተቃውሞ ስለገጠመው በሰዓታት ውስጥ እንዲነሳ ተደርጓል። የቀድሞዉ የደቡብ ኮርያ ፕሬዝዳንት ዮን ሱክ ዩል ከስልጣናቸው እንዲነሱ እና በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚጠይቁ ድምጾችም ተበራከቱ። በኮርያ ሴኡል ከተማ ኮርያ ታይምስ በሚባል ጋዜጣ ላይ የሚሰራዉ የፎቶ ጥበብ ባለሞያ እና የማኅበራዊ ጉዳይ አንቂዉ ጋዜጠኛ በረከት አለማየሁ ባለፈዉ እሁድ ኢትዮጵያዉያን ለአዲስ ተመራጩ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚደንት ለሊ ጄ ሚዮን የእንኳን ደስ ያሎት ሰልፍ በማዘጋጀት መልክቶቻቸዉን ሁሉ በደብዳቤ በኮርያንኛ በእንጊሊዘኛ እና አማርኛ ለፕሬዚዳንቱ አድርሰዋል።
ለጥቂት ደቂቃ የቆየዉ ማርሻል ህግ
ወታደራዊ ህግን ያወጁት የቀድሞዉ የደቡብ ኮርያ ፕሬዚዳንት ከስልጣን ተነስተዉ ያለመከሰስ መብታቸዉ ተገፎ ከአንድ ወር በላይ በእስር ቆይተዋል። በፍርድ ቤት ዉሳኔ መሰረትም ከእስር ተለቀዉ የክስ ሂደታቸዉን እየተከታተሉ ነዉ። በደቡብ ኮርያ ወታደራዊ መንግስት እንዲሰፍን አዉጀዉ የነበሩት የቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ምናልባትም ፤ እድሜ ይፍታህ አልያም እስከሞት የሚያደርስ ብይን ሊተላለፍባቸዉ እንደሚችል እየተነገረ ነዉ። የቀድሞዉ ፕሬዚዳንት ያወጁት ማርሻል ህግ ወይም ወታደራዊ ህግ የተባለዉ ለትንሽ ሰዓታት ብቻ ተግባራዊ ሆኑ መሻሩ ተነግሯል።
የኢትዮጵያዉያኑ መልክት
አዲሱ የኮሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጥዎ እንኳን ደስ አለዎት ያሉት በደቡብ ኮርያ የሚኖሩት ኢትዮጵያዉያኑ ባለፈዉ እሁድ በሲኡል አደባባይ ተሰልፈዉ ለፕሬዚዳንቱ መልክታቸዉን በደብዳቤ አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያዉያኑ በመልክታቸዉ «እኛ በዚህ ሃገር የምንገኝ ኢትዮጲያዊያን በሙሉ 21ኛው የኮሪያ ሪፐብሊክ መሪ ሆነው በህዝብ ድምፅ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም በመመረጥዎ የተሰማንን ልባዊ ደሰታ ለመግለፅ ይህን ደብዳቤ ሰኔ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ስንልክልዎ እንኳን ደስ አለዎ እያልን ነው፤ ሲሉ ጽፈዋል። በመቀጠል፤ እኛ በኮሪያ ሀገር የምንገኘ ኢትዮጵያዊያን ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በስደት: ለትምህርት: ለጥናት እና ምርምር: ለስራና ለንግድ እንዲሁም በጋብቻ ምክንያት የመጣን መሆናችን የታወቀ ነዉ። የኮሪያ ሪፐብሊክ እና ኢትዮጵያ በደም የተሳሰረ የረጅም ጊዜ ወዳጃዊ ግንኙነት አላቸው። ለዚህ ሀገር ነፃነት: ዴሞክራሲ እና እድገት ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችን የከፈሉት የህይወትና የአካል መስዋዕትነት ታሪካዊ እና ዘላለማዊ ትውስታ ያለው ነው። እርስዋም ታሪካዊ በሆነ የህዝብ ምርጫ የዚህ ሀገር መሪ ሆነው ተመርጠዋል እና ሀገርዎ በቅንነት እና እውቀት ወደፊት ያራምዳሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በዚሁ አጋጣሚ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ውስጥ በንቃት ተሳትፎ በሰላማዊ ሁኔታ በሰለጠነ መልኩ መሪውን ለመረጠው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ለሚገኘው የኮሪያ ህዝብ ያለንን ታላቅ አክብሮት ለመግለጽ እንወዳለን፤ ብለዋል፤ኢትዮጵያዉያኑ ለኮርያዉ አዲስ ፕሬዚደንት በጻፉት ደብዳቤ። በመቀጠል « በእርስዎ ክብር ፕሬዚዳንት የሚመራው አዲሱ አስተዳደር ከውድ እናት ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ህዝቦቿ ጋር መልካም ግንኙነቱን ያጠናክራል ብለን ተስፋም እናደርጋለን። ሀገራችን ከደቡብ ኮሪያ ነፃ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታን: የሰለጠነ ህዝባዊ ተሳትፎ: ነፃ እና ገለልተኛ ተቋማት አስተዳደርን: የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅን እንዲሁ ሙሉ ኢትዮጵያዊያን ላይ ያተኮረ ጠንካራ የኢኮኖሚ ዝርጋታ ላይ በሰፊ ልምድ እንድትቀስም እኛ ዜጎቿ እንፈልጋለን። ለዚህም ሰላማዊ: የተረጋጋችና ዜጎቿ የሚተማመኑባት ሀገር እንድትኖረን እንዲያግዙን በትህትና እንጠይቃለን» ሲሉ በደብዳቤያቸዉ አስፍረዋል።
ጋዜጠኛ በረከት በመቀጠል እንደገለፀዉ ይህን የደቡብ ኮርያን ታሪካዊ አጋጣሚን በመጠቀም እኛ በዚህ ሀገር የምንገኝ ኢትዮጵያዊያን በሦስት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ለአዲሱ አስተዳደር በጽሑፍ ወሳኝ መልክት አስተላልፈናል ሲል አጫዉቶናል። በደቡብ ኮርያ ስትኖር ወደ አስር ዓመት ግድም የሆናት እመቤት ባለፈዉ እሁድ በደቡብ ኮርያ መዲና በተካሄደዉ የኢትዮጵያዉያን ሰልፍ ላይ ተሳታፊ ነበረች። በደቡብ ኮርያ የሚገኙ ለረጅም አመታት የመኖርያ ፈቃድ እንዲሰጣቸዉ የሚጠይቁ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ጥያቅያቸዉ እንዲታይላቸዉ መጠየቁን ተናግራለች።
ከደቡብ ኮሪያ እና ከተባበሩት መንግሥታት ኃይሎች ጋር በኮርያዉ ጦርነት ላይ የዘመተዉ የኢትዮጵያ ቃኘው ሻለቃ ጦር በአሁኑ ወቅት በኮርያ በክብር ይታወሳል። ይህ ታሪክ የኢትዮጵያን እና የደቡብ ኮሪያን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ እንዳጠናከረዉ ይታመናል። በዝያን ግዜ በኮርያ ዘምተዉ የነበሩ የኢትዮጵያዉያን ልጅ እና የልጅ ልጆችም በአሁኑ ወቅት በኮርያ የትምህርት እድልን አግኝተዋል። በግምት ወደ አንድ ሺህ አምስት መቶ የሚሆኑ ኢትዮጵያዉያን በአሁኑ ወቅት ኮርያ ዉስጥ እንደሚኖሩ ጋዜጠኛ በረከት አለማየሁ አጫዉቶናል። እንደ ጎርጎረሳዉያኑ ከሰኔ 25 ቀን 1950 እሰከ ነሐሴ 27 1953 ድረስ በተካሄደው የኮርያዉ ጦርነት ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ከአፍሪቃ ወታደሮችን የላከች ብቸኛዋ ሃገር ኢትዮጵያ ስትሆን በፈረቃ 6037 ወታደሮችን መላክዋ የታሪክ ማህደራት ያሳያሉ።
ቃለ-ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ DW ስም በማመስገን ሙሉ ዝግጅቱን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!
አዜብ ታደሰ
ዮሃንስ ገብረግዚአብሔር