1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሙዚቃ

ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ፤ አለማየሁ እሸቴ  ሲታወስ

እሑድ፣ ነሐሴ 30 2013

በ1955 ዓ/ም ፖሊስ ኦርኬስትራ በመቀጠር ሙዚቃን የጀመረው አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ፤ በሙዚቃ ስራዎቹ ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ የሚል ቅፅል ስም እስከማግኘት ደርሶ ነበር። አንጋፋዉ ሙዚቀኛ የዜማ እና የግጥም ደራሲ እንዲሁም ፒያኖና ጊታር አቀላጥፎ መጫወት የሚችል ሁለገብ የጥበብ ሰው ሲሆን፤ 400 የሚጠጉ ሙዚቃዎችንም ሰርቷል።

Der äthiopische Sänger und Songwriter Alemayehu Eshete
ምስል፦ Pablo Ruiz Holst

ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ፤ አለማየሁ እሸቴ  ሲታወስ

This browser does not support the audio element.


ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ/ም ከኢትዮጵያ የሙዚቃ ሰማይ ስር አንድ ኮከብ ጠፍቷል።አንጋፋው የጥበብ ሰው አለማየሁ እሸቴ። የዛሬው የመዝናኛ ዝግጅታችን ይህንን አንጋፋ ድምፃዊ የሚዘክር ነው።
አንጋፋው ድምፃዊ አለማየሁ እሸቴ ፤ሰኔ 10 ቀን 1934 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት አካባቢ ነበር የተወለደው።ድምፃዊ ዓለማየሁ እሸቴ ገና በልጅነት ዕድሜው እናቱ ወ/ሮ በላይነሽ  የሱፍ   እና አባቱ አቶ እሸቴ አንዳርጌ በፍች በመለያየታቸው ከእናቱ ጋር ወደ ደሴ ሄዶ የነበረ ሲሆን፤ከሶስት አመት ዕድሜው ጀምሮ ግን ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ዕድገቱ በአባቱ ቤት ሆነ። በ1940ዎቹ  እንዳብዛኛው የዘመኑ ሕፃናት  ትምህርት የጀመረው በአብነት ትምህርት ቤት ሲሆን፤ በኋላ ግን አባቱ  ዘመናዊ  ትምህርት እንዲከታተል አድረጉት። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በአብዮት ቅርስ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ  በአርበኞች ትምህርት ቤት እዚያው ተወልዶ ባደገባት አዲስ አበባ ከተማ ነበር የተከታተለው።

ምስል፦ DW/T. Mehretu


በትምህርት ቤት ቆይታው በሲኒማ ያያቸውን ሙዚቀኞች በማስመሰል  ከጓደኞቹ ጋር  ሙዚቃ ያቀረብ የነበረ ሲሆን፤እሱ  የተወነበት “ኪንግ ሪቻርድስ ኤንድ ዘ አኖውን ኪንግ”የተሰኘ የትምህርት ቤት ቲያትርም  ዓለማየሁ ጥሩ ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን ተዋናይ  መሆኑን ጭምር ያሳየበት ነበር። በወቅቱ ዘመነኞቹን ፊልሞች መመልከት ያዘወትር የነበረው አለማየሁ፤ ሳይሳካለት ቀረ እንጅ የወጣትነት ህልሙ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይ መሆን  ነበርና  በ1954 ዓ/ም  ወደ አስመራ በማቅናት በምፅዋ በኩል ከግብፅ መርከበኞች ጋር ወደ አሜሪካ ለመሄድ ሞክሮም ነበር።የኋላ ኋላ ግን ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ፤  በዚያን ዘመን ገኖ የነበረውን የአሜሪካዊውን  የፊልም ተዋናይና የ«ሮክ አንድ ሮል» ሙዚቃ አቀንቃኙን የኤልቪስ ፕሪስሊን ሙዚቃ  እያጠና መድረክ ላይ ይጫወት ጀመር። አለማየሁ በአለባበሱም ሆነ በፀጉር አበጣጠሩ  ኤልቪስን የሚከተል ዘናጭ እና በዘመኑ አጠራር «አራዳ» የሚባል ነበር።የ40 ዓመት የሙያ አጋሩ እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ህብረት ፕሬዚዳንት አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ዳዊት ይፍሩ፤ያንን ዘመን ያስታውሰዋል።
«የፒያሳ አከባቢ የአራዳ ልጅ ነው ።በሚባልበት ዘመን ፒያሳ ላይ ቴክሳስ ሻይ ቤት የሚባል አለ። ወጣቱን በሚዝናናባቸው።በዚህ ዘመን  የተፈጠረ ሰው ነው። የተወለደው አባኮራን ሰፈር ለፒያሳ ቅርብ  ነው። እንግዲህ በዚያን ዘመን በየ ሻይ ቤቱ  ሲሰማ የነበረው  ሸክላ የውጭ ሀገር ሙዚቃ ነበር ። የእንግሊዘኛ የህንድ የሙዚቃ የሱዳን ሙዚቃዎች በየ የሻይ ቤቱ የሚሰማበት ዘመን ነበር። እና ይህንን ተከትሎ ብዙዎቹን ለመሸምደድ ይጥር ነበር ። በርግጥም ተሳክቶለታል እንግሊዝኛም ዘፍኗል አረብኛም  እነዚህን የመሳሰሉትን በሙሉ ይጫወት ነበር።»
 በ1955 ዓ/ ም በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ ውስጥ በመቀጠር ሙዚቃን  የጀመረው አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ፤ በወቅቱ በሚጫወታቸው የሙዚቃ ስራዎቹ ኢትዮጵያዊው ኤልቪስ ፕሪስሊ የሚል ቅፅል  ስም እስከማግኘት ደርሶ ነበር። ይሁን እንጅ አባቱ  በትምህርቱ እንዲ,ገፋ እንጅ ሙዚቃ መጫወቱን አይወዱለትም ነበርና  ወደ ፖሊስ ኦኬስትራ ሸኝተውት ሲመለሱ «አንድ ልጄን ገድየው መጣሁ» ብለው እንደነበር  በአንድ ወቅት ሲናገር ተደምጧል።በዚህ የተነሳ ከአባቱ ጋር የነበረው ቀረቤታ ሻክሮ ስለነበር   የተሰማውን ብቸኝነት ለመግለፅ «ሁኛለሁኝ ብቸኛና ከርታታ ስላጣሁኝ በአንች ፍቅር ምንም ፋታ» በሚል  የመጀመሪያ ሙዚቃውን  ሰራ።ወቅቱ የሙዚቃ ስራ በፍቅር የሚሰሩት የነብስ ስራ እንጅ፤ ብዙም ገንዘብ የማይገኝበት ቢሆንም አለማየሁ ለሙያው ከነበረው ፍቅር የተነሳ ፊቱን ወደ ሌላ ስራ አላዞረም። ቆይቶም  በ1967 ዓ/ም  ገደማ የአባቱን ምክር አስታውሶ ይመስላል «ተማር ልጄ»የሚለውን ተወዳጅ ሙዚቃ ለአድማጭ ጀሮ አድርሷል። 
 ከ1960 ዓ/ም  በኋላ አለማየሁ በግሉ  ለመስራት «ሶሊኮስ» የተሰኘ  ባንድ ያቋቋመ ሲሆን፤ በሸክላ የሙዚቃ ህትመት ታሪክ ውስጥ ሙዚቃውን ለመጀመሪያ  ጊዜ በግሉ በሸክላ  ያሳተመ ዘመናዊ የሙዚቃ ባለሙያም ነበር ።በዚህም የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደረሰ የዘመናዊ ሙዚቃ ፈር ቀዳጅም ነው።አንጋፋው የጥበብ ሰው የዜማ ደራሲና የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችም ነበር።«ለጥበብ የተፈጠረ »ይለዋል። የሙያ  አጋሩ አንጋፋው የሙዚቃ ሰው ዳዊት ይፍሩ ።
 «ዓለማየሁ እሸቴ  ለጥበቡ የተፈጠረ ሰው ነው ማለት እችላለሁ።የዜማ ደራሲ፣ የግጥም ደራሲ፣ የራሱን ሙዚቃ የሚፅፍ በዚህ ላይ ደግሞ ፒያኖና ጊታር አቀላጥፎ መጫወት የሚችል ሁለገብ አርቲስት ነው።»በማለት ነበር የገለፀው።
ይህ አንጋፋ ድምፃዊ በህይወት ዘመኑ «አዲስ አበባ ቤቴ»፣ «ችግርሽ በእኔ አልፏል»«ስቀሽ አታስቂኝ»፣ «እንደ አሞራ» ፣ « ምሽቱ ደመቀ»፣ «የወይን ሃረጊቱ» ፣ «የሰው ቤት የሰው ነው»፣  «ደንየው ደነባ»፤ «ወልደሽ ተኪ እናቴ» እና «ተማር ልጄ»ን  ጨምሮ ወደ 400 የሚጠጉ ሙዚቃዎችን ሰርቷል።በተለያዩ ሀገራት ተዘዋዉሮ የሙዚቃ ስራዎቹን በማቅረብም አድናቆትን አትርፎባቸዋል። በሀገር ውስጥ እና በውጭ የተለያዩ ሽልማቶችንም አግኝቷል። አድናቆት ከተቸረባቸው የሙዚቃ ስራዎቹ  በተጨማሪ አለማየሁ በግሩም  የመድረክ  አቀራረቡም  ከብዙዎች ህሊና የማይጠፋ ታላቅ የሙዚቃ ሰው ነበር።
ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ  በሙዚቃ ስራ ላይ የቆየው ይህ አንጋፋ የጥበብ ፈርጥ ባለትዳርና የ7 ልጆች /የአራት ወንዶችና የሶስት ሴቶች/ አባት ሲሆን፤ያለፈው ሀሙስ  ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ/ም በተወለደ በ79 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።በዘመን ተሻጋሪ ስራዎቹ ግን ሁሌም ሲታወስ ይኖራል።
በአንጋፋው የሙዚቃ ሰው አለማየሁ እሸቴ ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን እየገለፅን ለወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም ለአድናቂዎቹ መጽናናትን እንመኛለን። 

ምስል፦ Pablo Ruiz Holst


ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ፀሀይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ
 

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW