1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያዊው የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ በሐምቡርግ

ማክሰኞ፣ የካቲት 21 2015

አቶ ታደሰ ከኅብረተሰቡ ጋር በቀጥታ በሚያገናኛቸው በሞያቸው በሰሩባቸው 30 ዓመታት ደስተኛ ናቸው። በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ስራቸውን ያለ እንከን መስራት በመቻላቸው ከምንም በላይ ይረካሉ። ኢትዮጵያውያንን ለማሰባሰብና የምክር አገልግሎት የሚያሻቸውንም ለማገዝ በ1982 በጀርመን የኢትዮጵያውያንን ማኅበር ከመሰረቱት አንዱ ናቸው።

Hamburg 2021
ምስል Juergen Tap/HOCH ZWEI/picture alliance

አቶ ታደሰ ደሳለኝ 30 ዓመታት የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ

This browser does not support the audio element.

አቶ ታደሰ ደሳለኝ ሐምቡርግ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ቢሰሩና ቢኖሩም መጀመሪያ የመጡት የቀድሞው የምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ ቦን ነበር። በቦን ቆይታቸውም ከጓደኞቻቸው ጋር የመሰረቱትና አሁን በመላ ጀርመን ለሚገኙ ልዩ ልዩ የኢትዮጵያውያን ማኅበራት ፈር ቀዳጅ ሊባል ከሚችለው በጀርመን የኢትዮጵያውያን ማኅበር ጋር ስማቸው ይነሳል። 
አቶ ታደሰ ጀርመን ከመጡ 40 ዓመት አልፏቸዋል። ከ16ቱ የፌደራል ግዛቶች አንዷ በሆነችው በሐምቡርግ በሰለጠኑበት ሞያ ከ30 ዓመታት በላይ ሰርተዋል ። የሰሜን ጀርመንዋ የወደብ ከተማ ሐምቡርግ አሁንም መኖሪያቸው ናት። በስደት ይኖሩ ከነበሩበት ከሱዳን ጀርመን ጥገኝነት አግኝተው ወደያኔዋ የምዕራብ ጀርመን ዋና ከተማ ቦን የመጡት በጎርጎሮሳዊው 1980 ነበር፣ ከኢትዮጵያ የወጡት 12 ኛ ክፍል አጠናቀው ቢሆንም ርሳቸውና ሌሎች አብረዋቸው የመጡ ጓደኞቻቸው የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ምስክር ወረቀት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ጀርመን ውስጥ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያዘጋጃቸው ትምህርት ቤት መግባት ግድ ነበር። አቶ ታደሰ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመልሰው መግባታቸው ባይከፋቸውም የቋንቋው ክበድትና የማስተማር ዘዴው ግን አስቸግሯቸው ነበር። የባህል ግጭቱም  ቀላል አልነበረም። 

ምስል Bobby Steven

3 ዓመት ተምረው ከፍተኛ ትምሕርት መቀጠል የሚያስችላቸውን ውጤት ካገኙ በኋላ በሰሜን ጀርመንዋ በሐምቡርግ ከተማ በማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪነት ስልጠና ወሰዱ። እንደጨረሱም በሙያቸው መስራት ጀመሩ። በመንግሥት በሚረዳው በዚህ ድርጅት ውስጥ የመጀመሪያዎቹን አስራ ሁለት ዓመታት እድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ለሆነ እናት አባት ለሌላቸው ስደተኞች የማኅበራዊ ምክር አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩት አቶ ታደሰ፣ በኋላም በዚያ መስሪያ ቤት ውስጥ በሌላ አገልግሎት መስራት ቀጠሉ። 
አቶ ታደሰና አብረዋቸው ጀርመን የመጡት ጓደኞቻቸው፣ ከ40 ዓመት በፊት ቦን እንደመጡ ትልቁ ሀሳባቸው ሱዳን የሚገኙ ጓደኞቻቸውን ጀርመን እንዲመጡ መርዳት ነበር። ይህንኑ ሃሳባቸውን ለማሳካት ብዙ ቢጥሩም አልሆነላቸውም። ይህ ባይሳካም በዚህ መሀል  ጀርመን የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማሰባሰብና የምክር አገልግሎት የሚያሻቸውንም ለማገዝ በጎርጎሮሳዊው 1982 በጀርመን የኢትዮጵያውያን ማኅበር ለመመስረት በቁ።ከማኅበሩ መስራቾች አንዱ  አቶ ታደሰ ማኅበሩን በሊቀመንበርነትና በፀሐፊነትም ለብዙ ጊዜያት ማገልገላቸውን ገልጸውልናል።
አቶ ታደሰ ከኅብረተሰቡ ጋር በቀጥታ በሚያገናኛቸው በሞያቸው በሰሩባቸው 30 ዓመታት ደስተኛ ናቸው ።ከሁሉም በላይ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው ስራቸውን ያለ እንከን መስራት በመቻላቸው ከምንም በላይ ይረካሉ። ለጀርመናውያንም በሚሰጡት በዚህ አገልግሎት በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት የደረሰባቸው ችግር እንደሌለ ነው የሚናገሩት። ከአንድ ዓመት በፊት ጡረታ ቢወጡም በሞያቸው ለወገኖቻቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየሰጡ ነው። አቶ ደሳለኝ ታደሰ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW