ኢትዮጵያዊያንን ለአደገኛ የፍልሰት ጉዞ የሚዳርጓቸው ገፊ ምክንያቶች ምንድናቸው ?
ረቡዕ፣ ሐምሌ 30 2017
ወደ ተለያዩ አገራት ለመሻገር በሚሞክሩ ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ላይ የሚደርሰው አሰቃቂ አደጋ ዛሬም ማብቂያ ያገኘ አይመስልም ፡፡ ባለፈው እሁድበየመን የባሕር ዳርቻ ላይ 157 ፍልሰተኞችን አሳፋራ በመጓዝ ላይ የነበረች ጀልባ መገልበጧ ከተሰማ ወዲህ የፍልሰት ጉዳይ አጀንዳ እየሆነ ይገኛል ፡፡ እስከአሁን ህይወታቸው ማለፉ ከተረጋጋጠ 68 ፍልሰተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ደግሞ የዜጎች ሞት መቼ ያበቃል የሚል ጥያቄን መስነሳቱ አልቀረም ፡፡
«ወጣቱ አይሰማህም»
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ከንባታ ዞን ሀደሮ ከተማ ነዋሪ የሆነው የ29 ዓመቱ ወጣት በረከት አበበ በሕገ ወጥ ፍልሰት ሳቢያ በዛምቢያ ከሰባት ዓመት እሥር በኋላ ወደ አገሩ መመለሱን ይናገራል ፡፡ አሁን ላይ ከዓለም አቀፉ የፍልሰቶች ድርጅት / IOM / ጋር በመሆን የሕገ ወጥ ፈልሰትን አስከፊነት ለማስተማር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ፡፡
ወጣቶች ስለስደት ያላቸው አመለካከት አስደንጋጭ እንደሆነ ከሚያገኛቸው ወጣቶች ለመገንዘብ መቻሉን ለዶቼ ቬለ የተናገረው በረከት “በሕገ ወጥ ፍልሰት ምክንያት የደረሰብኝን የሰባት ዓመት የእሥርና የመከራ ጊዜ መነሻ በማድረግ ለብዙዎች መረጃ ለመስጠት ሞክሪያለሁ ፡፡ በተለያዩ የሥልጠና መድረኮችም በቻልኩት መጠን ግንዛቤ ለመፍጠር ሰርቼያለሁ ፡፡ ነገር ግን ወጣቱ አይሰማህም ፡፡ ሥራ ከሌለ ምን እንሁን ብሎ ይጠይቅሃል ፡፡ በዚህም ብዙዎች ተስፋ ቆርጠው ይገኛሉ ፡፡ ወንድሙ እዛ ታስሮ እያለ ሁለተኛውም ወደእዚያው ሲሄድ ታገኘዋለህ ፡፡ ለምን ብለህ ስትጠይቅ እሱ የራሱን ዕድል ነው የሞከረው ፡፡ እኔም ልሙት እንጂ የራሴን እሞክራለሁ ይልሃል “ ብሏል ፡፡
ገፊ ምክንያቶች
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ከከምባታ እና ሃድያ ዞኖች የሚነሱ ፍልሰተኞች በአብዛኛው በሞያሌ የደቡብ አፍሪካ መስመሮችን የሚጠቀሙ ቢሆንም አልፎ አልፎም በሱዳን በኩልም እንደሚወጡ ከከምባታ ዞን ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል ፡፡ አቶ ዓለማየሁ አቡዬ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከምባታ ዞን ሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ የማህበራዊ ጉዳዮች ባለሙያ ናቸው ፡፡
ለኢመደበኛ ፍልሰት መባባስ ዋነኛው ገፊ ምክንያት የሥራ ዕድል አለመኖር መሆኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት አቶ ዓለማየሁ “ በእርግጥ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋወሪዎችም የራሳቸው ሚና አላቸው ፡፡ ዋናው እና ትልቁ አደጋ ግን ወጣቱ ያለው አመለካከት ነው ፡፡ አብዛኛው ወጣት ከትንሽ ሥራ ተነስቼ በሂደት አለወጣለሁ የሚል ግንዛቤ የለውም ፡፡ ይህም ህገ ወጥ ፍልሰት እንዲበራከት ምክንያት ሆኗል “ ብለዋል ፡፡
የሥራ ዕድል እንዴት ?
የሕገ ወጥ ፍልሰትንአስከፊነት ከማስተማር ጎን ለጎን ለሥራ ዕድል ትኩረት መሰጠት እለበት የሚሉት የማህበራዊ ጉዳዮች ባለሙያው ለዚህ በመንግሥት በኩል ጥረቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል ፡፡ አቅም በፈቀደ መጠን ወጣቶችን በማህበር በማደራጀት፣ የመሥሪያ ቦታ እና የብድር አቅርቦት በማመቻቸት በሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮጀክቶች ለማሳተፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ያብረሩት ባለሙያው “ ነገር ግን ይህ ከሥራ ፈላጊው ቁጥር አንጻር ሲታይ ኢምንት ነው ፡፡ በቀጣይ ሰፊ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ ነው “ ብለዋል ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ዜጎች በተለያዩ አገራት በሕጋዊ መንገድ ተንቀሳቅሰው መሥራት እንዲችሉ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን በማከናወን በርካታ ዜጎችን የዕድሉ ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል ሲል አደጋውን አስመልቶ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አማካኝነት ባወጣው የሀዘን መግለጫ ላይ ጠቅሷል ፡፡
ሚንስቴሩ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ብቻ የውጭ አገራት የሥራ ሥምሪት ተጠቃሚ እንዲሆኑና ከሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ሲልም አሳስቧል ፡፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ፀሐይ ጫኔ