ኢትዮጵያዊያንን ከሳውዲ አረቢያ የማስመለሱ 4ኛ ዙር ሥራ ተጀመረ
ረቡዕ፣ መጋቢት 3 2017
ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የነበሩ 1050 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ወደ ሀገራቸው ተመለሱ ። ዛሬ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከገቡት ሰዎች መካከል ለዓመታት «በአስከፊ ስቃይ ውስጥ» ነበሩ የተባሉ እንደሚገኙበት ከተመላሾች አንደኛው ለዶቼ ቬለ ተናግሯል ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህ ሥራ ቀድሞ የተጀመረው ኢትዮጵያዊያኑን ከሳውዲ አረቢያ የማስመለሱ ተግባር አራተኛ ዙር መሆኑን ገልጿል ። ሚኒስቴሩ በሚያንማር «በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ» ያላቸው 43 ኢትዮጵያዊያንም ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ መግባታቸው ተገልጧል ።
ዛሬ አንድ ሺህ ሃምሳ ኢትዮጵያዊያን ከሳውዲ ተመልሰዋል
የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በተለይም ወደ ሳውዲ አረቢያ ተጉዘው ካሰቡት ውጪ በከፍተኛ ችግር፣ እሥር፣ እንግልት እና ሥቃይ ውስጥ የቆዩ ኢትዮጵያውያን እንደ ከዚህ ቀደም ተመላሾች ዛሬ ቦሌ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ተንበርክከው መሬት ስመዋል፥ ደስታቸውንም በጩኸት ገልፀዋል ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው እነዚህ ተመላሾች መንግሥት አስቀድሞ የጀመረውና ዜጎችን ከሳውዲ አረቢያ የማስመለሱ ጥረት አራተኛ ዙር መሆኑን ነግረውናል ። እነዚህ ዜጎች "በማቆያ" ሥፍራ ውስጥ የቆዩ ስለመሆናቸውም ተገልጿል። በዛሬው የማስመለስ ሥራ ሴቶችን እና ሕፃናትን ማስመለሱ ላይ ቅድሚያ ስለመሰጠቱም ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።
በተመሳሳይ በሚያንማር "በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ" የተባሉ 43 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብተዋል። ከዚህች ሀገር 32 ኢትዮጵያውያን ከትናንት በስቲያ መመለሳቸውንም መንግሥት አስታውቋል። ይህ የማስመለስ ሥራ እጅግ ፈተና የበዛበት ስለመሆኑ ግን አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው ገልፀዋል።
ሚያንማር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን የማስመለሱ ሥራ ፈታኝ ነው - ውጭ ጉዳይ
ከሚያንማር እና ታይላንድ እስከ አዲስ አበባ የተዘረጋ የደላሎች መረብ ኢትዮጵያውያን ሚያንማር ውስጥ ለችግር እንዲጋለጡ እየዳረጋቸው መሆኑን የዚህ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቤተሰቦች እና ከትናንት በስቲያ ከተመለሱት መካከል አንደኛው መግለፃቸውን መዘገባችን ይታወሳል ። ወንዶችን በበይነ መረብ የማስታወቂያ እና የንግድ፣ ሴቶችን በሆቴል እና መስተንግዶ ሥራዎች ትቀጠራላችሁ የሚለው የደላሎች አሳሳች መረጃ ኢትዮጵያዊያኑ ከሄዱ በኋላ ተገደው የበይነ መረብ የገንዘብ ምንተፋ የወንጀል ድርጊቶች ውስጥ እንዲሰማሩ እና በቀን ከ 18 ሰዓታት በላይ እንዲሠሩ እያስገደዷቸው ስለመሆኑም ተደጋግሞ ተገልጿል ።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም እነዚህ ተመላሾችን ወደ ቤተሰቦቻቸው እንመልሳለን ብለዋል ።
«ከፍተኛ ሥቃይ አሳልፈናል» ከሳውዲ ተመላሽ
ዛሬ ከሳውዲ አረቢያ ከገቡት ሰዎች መካከል ኤርፖርት ውስጥ ቃለ መጠይቅ የምናደርግበት ዕድል አልነበረም። ይሁንና ከተመላሾች መካከል አንዱ "ለሦስት ዓመታት በእሥር ላይ" መቆየቱንና በሕይወቱ "ከፍተኛ ሥቃይ" ማሳለፉን ከአውሮፕላን ከወረደ በኋላ ወደተዘጋጀላቸው ስፍራ ለመሄድ አውቶቡስ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ነግሮናል ።
ሰለሞ ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ