በየመን ስደተኞች የተገደሉበት የአሜሪካ ጥቃት “እንደ ጦር ወንጀል” እንዲመረመር አምነስቲ ጠየቀ
ዓርብ፣ ጥቅምት 21 2018
የ33 ዓመቱ ደስታ በሰሜን ምዕራብ የመን በሚገኘው ሳዓዳ እስር ቤት ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በፍርስራሽ ውስጥ ተቀብሮ ነበር። ከአንድ ሰዓት ገደማ በኋላ ከፍርስራሹ አውጥቶ ወደ ሆስፒታል የወሰደው ወንድሙ ነው። ደስታ ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተናገረው በጥቃቱ ምክንያት ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ደርሶበታል። የአንድ ዐይኑን እይታ አጥቷል።
“በሕይወት መትረፋችን እና ከዚያ ቦታ መውጣታችን ተዓምር ነው” የሚለው ደስታ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሳዓዳ እስር ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት ባከናወነው ምርመራ ቃለ-መጠይቅ ካደረገላቸው 15 ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው።
በየመን ሑቲዎች በሚቆጣጠሩት አካባቢ የሚገኘው ሳዓዳ እስር ቤት ላይ በአሜሪካ ጥቃት የተፈጸመው ሚያዝያ 20 ቀን 2017 ነበር። በወቅቱ ከ100 እስከ 120 የሚሆኑ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በእስር ቤቱ እንደነበሩ የዐይን እማኞች እና ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተናግረዋል።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ በጥቃቱ ላይ ያከናወነውን ምርመራ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ይፋ ሲያደርግ በሳዓዳ እስር ቤት ከነበሩ ስደተኞች መካከል በደርዘን የሚቆጠሩ መገደላቸውን አስታውቋል። የመንን የሚያስተዳድሩት ሑቲዎች በጥቃቱ በሳዓዳ እስር ቤት ውስጥ ከነበሩ 117 ስደተኞች 61 መገደላቸውን ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጸዋል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ሃይማኖት አሸናፊ የዐይን እማኞች እና ቆስለው የተረፉ የጥቃቱ ሰለባዎች “በእስር ቤቱ ውስጥ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ በርካቶቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ” መናገራቸውን ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። በጥቃቱ ዕለት ቆስለው ሆስፒታል ከገቡት መካከል አንድ ኤርትራዊ እና ከ20 በላይ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ መግለጻቸውንም አስረድተዋል።
ጥቃቱ እንደተፈጸመ በጉዳዩ ላይ የወጡ ሪፖርቶች በተለይ ገለልተኛ የሆኑ የመን ውስጥ ጉዳዩን የሚከታተሉ ተቋማትም “ሕይወታቸውን በዚህ ጥቃት ያጡት ሲቪል ሰዎች በርካቶቹ ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ” ገልጸዋል። “ምን አልባት ሙሉ በሙሉ” ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግንዛቤ መኖሩን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተመራማሪ የሆኑት ሃይማኖት አሸናፊ አስረድተዋል።
በሳዓዳ እስር ቤት ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት አምነስቲ ምርመራውን ሲያከናውን ቃለ-መጠይቅ ከተደረገላቸው አስራ አምስት ኢትዮጵያውያን አስሩ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ የላቸውም በሚል በሑቲዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው። ከአስሩ ሰባቱ የታሰሩት ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ሲሞክሩ ድንበር ሊሻገሩ ይችላሉ በሚል ጥርጣሬ ነው።
የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቹ ከጥቃቱ የተረፉ 15 ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ከጥቃቱ በኋላ የሳዓዳ እስር ቤትን፣ በአቅራቢያው የሚገኙ ሆስፒታሎች እና የአስከሬን ማቆያ ክፍሎችን የጎበኙ ሁለት ሰዎች አነጋግሯል።
ከጥቃቱ በሕይወት ከተረፉ እና ቃለ- መጠይቅ ከተደረገላቸው መካከል አስራ አራቱ ከባድ የነርቭ፣ የጭንቅላት፣ የአከርካሪ እና የደረትን ጨምሮ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ሁለቱ በጥቃቱ በደረሰባቸው ጉዳት እግራቸው ሲቆረጥ አንዱ እጁን ደስታ ደግሞ የዐይን ብርሀኑን አጥቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው የዐይን እማኝ ከጥቃቱ በኋላ ሪፐብሊካን በተባለ ሆስፒታል 25፣ በአል ጣልህ ጄኔራል ሆስፒታል ዘጠኝ የቆሰሉ ስደተኞች መመልከታቸውን ተናግረዋል። አንዳንዶቹ በጽኑ የቆሰሉ እና ሁለቱ እግራቸው የተቆረጠ እንደነበር የገለጹት የዐይን እማኝ “የሪፐብሊካን ሆስፒታል የአስከሬን ማቆያ ክፍል ተጨናንቆ ነበር። በሁለተኛው ቀን ከማቆያው ክፍል ውጭ ለተተዉ ከአስር በላይ አስከሬኖች ቦታ አልነበረም” ሲሉ መናገራቸው በምርመራው ሪፖርት ላይ ሠፍሯል።
አምነስቲ “በዘፈቀደ” የተፈጸመው ጥቃት ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግ የሚጥስ በመሆኑ እንደ የጦር ወንጀል ሊመረመር እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል። “በሕግ የሚፈለግባቸውን አስፈላጊ ጥንቃቄ ሳያደርጉ የሲቪል ሰዎች ሕይወት ወይም ንብረት፤ ወይም በጦርነት ውስጥ በሕግ ከለላ የሚደረግላቸውን ሰዎች ወይም ንብረቶች” ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች “የዘፈቀደ” የሚባሉ እንደሚሆኑ ሃይማኖት አስረድተዋል።
“በዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ መሠረት እንደ ወታደራዊ ዒላማ የሚታዩ እና የማይታዩ ቦታዎች አሉ” የሚሉት ተመራማሪዋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሳዓዳ እስር ቤት “ለወታደራዊ ዓላማ ሲውል እንደነበረ ወይም ወታደራዊ ዓላማ ሲካሔድበት እንደነበረ የሚሳይ መረጃ” እንዳላገኘ ገልጸዋል።
እስር ቤቱ የሑቲ አማጺያን “ሕገ-ወጥ” የሚሏቸውን ስደተኞች “የሚይዙበት ቦታ እንደሆነ በጣም በሰፊው የሚታወቅ ነው” የሚሉት ሃይማኖት “የአሜሪካ የአየር ጥቃት ይኸንን ከግምት ውስጥ አስቀድሞ መክተት ያስፈልገው ነበረ። ያንን ባለማድረጉ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የሕግ ክልከላዎችን የጣሰ ጥቃት ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰናል” ሲሉ ይሞግታሉ።
የአሜሪካ መንግሥት የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን የምርመራ ውጤት መሠረት በማድረግ የራሱን ምርመራ አከናውኖ “አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ፤ ለጥቃቱ ሰለባዎች እውቅና እንዲሰጥ፤ እንደ አስፈላጊነቱ ካሳ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበናል” በማለት አስረድተዋል።
በምርመራው ውጤት ላይ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአሜሪካ ጦር የመካከለኛው ምሥራቅ ወታደራዊ ዘመቻዎችን ከሚቆጣጠረው ማዕከላዊ ዕዝ (CENTCOM) እንዲሁም ከጥምር ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ዕዝ (JSOC) ምላሽ ጠይቋል።
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ ውስጥ በተከናወኑ ተልዕኮዎች በሲቪል ሰዎች ላይ ደረሱ ስለተባሉ ጉዳቶች እየገመገመ እንደሚገኝ ምላሽ ሰጥቷል። ሁሉንም መሰል ሪፖርቶች “በቁም ነገር” እንደሚወስድ እና “በጥልቀት” እንደሚመረምርም አስታውቋል።
የመን ሳዑዲ አረቢያን ወደ መሳሰሉ የአረብ ሃገራት ለሚጓዙ ኢትዮጵያውያን እንደ መሸጋገሪያ ታገለግላለች። በጅቡቲ በኩል ተጉዘው ቀይ ባሕርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተደጋጋሚ በደረሰ የጀልባ መስጠም አደጋ ሕይወታቸውን አጥተዋል። መደበኛ ባልሆነው ምሥራቃዊ የስደት መስመር የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የመን ሲደርሱ በሑቲዎች እና ዓለም አቀፍ እውቅና በተሰጠው የየመን መንግሥት ይታሠራሉ።
አርታዒ ሸዋዬ ለገሰ