1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ አሁንም ችግር ላይ ናቸው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 25 2016

በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በሊባኖስ የነገሰውን ውጥረት ተከትሎ እዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ችግሮች እንደገጠሟቸው ሲገልፁ ቆይተዋል።እዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዶቼ ቬለ እንደገለፁት በሊባኖስ ያለው ሁኔታ በመጠኑ ጋብ ያለ ቢመስልም የኢትዮጵያውያኑ ችግር ግን አሁንም ቀጥሏል።

ሰዎች ከሊባኖስ ለመውጣት ሲሞክሩ
እጎአ ነሐሴ 9 ቀን 2024 በቤይሩት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ እስራኤል የሂዝቦላህን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ከገደለች በኋላ ጦርነት ይፈጠራል በሚል ስጋት ሰዎች ከሊባኖስ ለመውጣት ሲሞክሩ ምስል AFP/Getty Images

የኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ በሊባኖስ

This browser does not support the audio element.


የሐማስ የፖለቲካ መሪ የነበሩትን እስማኤል ሃኒያ በኢራን ከገተደሉ ወዲህ በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በሊባኖስ የነገሰው ውጥረት ከፍተኛ ሆኖ ቆይቷል።በዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን እና በርካታ የሱኒ ዐረብ ሃገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ ው እና በኢራን የሚደገፈው የሊባኖስ የሺዓ ፖለቲካ ፓርቲ እና ወታደራዊ ክንፍ ሄዝቦላ፤ በእስራኤል ላይ ጥቃት መክፈቱ ደግሞ በሀገሪቱ ያለውን ሁኔታ የበለጠ ማባባሱ ይነገራል። በሰላሙ ጊዜም ቢሆን በፈታኝ ሁኔታ ኑሯቸውን የሚገፉት ኢትዮጵያውያን የጦርነት ውጥረት በነገሠባት ሊባኖስ መኖር ደግሞ ተጨማሪ ሸክም ሆኖባቸዋል።

 ውጥረቱ በመጠኑ ጋብ ብሏል

ዶቼ ቬለ ያነጋገራት በሊባኖስ መዲና ቤሩት የምትኖረው ሰላማዊት ተስፋዬ ሰሞኑን ውጥረቱ ጋብ ማለቱን ትገልፃለች።
«ከባለፈው ሳምንት የአሁኑ ሳምንት የተረጋጋ ነው።ያለፈው ሳምንት የአየር የጀት ድምጾች ነበሩ።ሀይለኛ የሚያስፈሩ ድምፆች ነበሩ።ያ አሁን የለም።ህዝቡም ተረጋግቶ ነው ያለው።መረጃዎች ሲኖሩ እዚያ/ውጥረቱ ባየለበት አካባቢ/ ካሉ ልጆች ጋር እየተቀያየርን ነው ያለነው።»ብላለች።
ምንም እንኳ በሊባኖስ ያለው  ውጥረት  በመጠኑ ጋብ ያለ ቢመስልም የኢትዮጵያውያኑ ችግር ግን አሁንም ቀጥሏል ትላለች። በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ሳይዳ የሚባለው አካባቢ ለ16 ዓመታት መኖሯን የገለፀችው ቤቲ ካሳሁን።

«ሁለት ቀን ተረጋግቷል ስልሽ ተኩሱ ምናምን ድምፁ እንዳለ ነው።የኑሮ ሁኔታ ከባድ ነው በተለይ ተመላልሰው ለሚሰሩ ውጭ ላሉት።ማዳም ቤት ያሉት እንኳ እነሱ ይሸፍኑላቸዋል።ስራ የለም ሀገሪቷ ገንዘብ የላትም።ቀጣሪዎች ሶስት መቶ አራት መቶ ዶላር መክፈል አይፈልጉም።ለእነሱ በጣም ከባድ ጊዜ ነው።ከሚሰሩት የማይሰሩት ይበዛሉ።ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም።ተስፋ የሚያደርጉት ነገር የላቸውም።»

ውጥረቱ ባየለበት የደቡባዊ የሊባኖስ ክፍል በእስራኤል የተፈፀመ የአየር ጥቃት ምስል Mohammad Zaatari/AP/picture alliance

«ፍካት ለኢትዮጵያ» የተባለ ማኅበር አባል መሆኗን የምትገልፀው ሰላማዊት ተስፋዬ ፤ ቤሩት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ከእነሱ የበጎ ፈቃድ ማኅበር ጋር መረጃ ይለዋወጣል።ውጥረቱ ባየለበት አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም መረጃ በመስጠት ድጋፍ ያደርጋል ትላለች። የከፋ ሁኔታ ቢመጣ በሚል ቆንስላ ጽ/ቤቱ ቅድመዝግጅት ማድረጉን ገልፃለች።

መመለስም በሊባኖስ መቆየትም ለኢትዮጵያውያኑ ቀላል አይደለም

ነገር ግን ቤቲ እንደምትለው በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገር ቤት መመለስም ይሁን ሊባኖስ የመቆየት ሁኔታ ለኢትዮጵያውያኑ ቀላል አይደለም።በመሆኑም ባሉበት ሆነው እርዳታ ቢያገኙ የተሻለ መሆኑን ታስረዳለች።
«ሌላው ሀገር ለቆ ይወጣል።ኢትዮጵያውያንን ላስወጣ ብትይ አንደኛ በኢትዮጵያ ኢምባሲ ነው የሚወጡት።የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደግሞ ክፍያ አለ ዝምብለው አይወጡም የትኬት ገንዘብ አለ።እጃቸው ላይ ገንዘብ መኖር አለበት።ጌዜ አለ ወረፋ መጠበቅም አለ።ሲደወልልሽ ነው የምትሄጅው። በመሃል አጋጣሚ የሚፈጠረው ነገር አይታወቅም።ግን እሱ አይደም እያሳሰበ ያለው። ወደ ኢትዮጵያ  መሄዳቸው ሳይሆን እዚህ እያሉ መረዳት አለባቸው።አሁን ባሉበት ሁኔታ።ምክንያቱም እምብዛሙ እየሰሩ አይለም።» በማለት ገልፃለች። 

የሊባኖሱ ሂዝቦላ ፉአድ ሹከር የተባሉ ኮማንደር ያለፈው ሀምሌ መጨረሻ ተገድለውብኛል በሚል እስራኤል ላይ የከፈተውን ጥቃት ተከትሎ፤ እስራኤል እና ሄዝቦላ ቀጠናውን ወደለየት ጦርነት ሊያስገቡት ይችላል በሚል ስጋት፤ ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸው ከሊባኖስ ለቀው እንዲወጡ ማሳሰቢያ መስጠታቸው ይታወሳል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW